ለስኳር ኮርፖሬሽን ከፍተኛ አመራሮች ሥልጠና ተሰጠ

የክህሎት፣ የአመራር ጥበብና ብቃት እንዲሁም የሥራ ተነሳሽነትን የሚያሳድግ ሥልጠና ለስኳር ኮርፖሬሽን ከፍተኛ አመራሮች ተሰጠ፡፡ ሥልጠናው ከመፈጸምና ማስፈጸም አቅም፣ ከሥልጠና ፍላጎትና ከስኳር ኢንደስትሪው ነባራዊ ሁኔታ ጋር ተገናዝቦ የተዘጋጀ ነው፡፡

በስኳር አካዳሚ አዘጋጅነት በአዳማ ካኔት ሆቴል ከጥቅምት 23-26/2013 ዓ.ም ድረስ የተካሄደው ይህ ሥልጠና በTransformational Leadership፣ Emotional Intelligence፣ Reform Management and Role of leadership፣ Quality Management System & Paradigm Shift እና Finance for Non-Financial Managers የሥልጠና ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ያተኮረ ነበር፡፡

የሥልጠናውን መርሃ ግብር ያስጀመሩት የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወዮ ሮባ ባደረጉት ንግግር፣ ሥልጠናው ኮርፖሬሽኑ በ2012 በጀት ዓመት ያስመዘገበውን አበረታች ውጤትና ይህን ተከትሎ የተፈጠረውን የሥራ መነቃቃት አጠናክሮ ለማስቀጠል ያግዛል ብለዋል፡፡

ሥልጠናው ከክረምት ጥገና በኋላ ፋብሪካዎች ወደ ምርት መግባት በጀመሩበት ወቅት መዘጋጀቱ አመራሩ እራሱን በማየት ያለፈውን አመት ጠናካራ ጎኖች የበለጠ ለማስቀጠል፤ ለታዩ ክፍተቶች ደግሞ የመፍትሔ ሃሳቦች ለማፈላለግ መልካም አጋጣሚ መሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡

ከፍተኛ አመራሩ በሥልጠና ያገኘውን እውቀትና ክህሎት ወደ ታች በማውረድ በሥራ ላይ ማዋል እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

የቡድን ውይይትን ባካተተው በዚህ ሥልጠና የኢንደስትሪውን እድገት ለማስቀጠል የሚያግዙ መሰረታዊ ርዕሰ ጉዳዮችና ገንቢ ሃሳቦች ተነስተው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

ሥልጠናው የዳበረ እውቀትና የረጅም ዓመት የሥራ ልምድ ባካበቱ ተጋባዥ አሠልጣኞች የተሰጠ ሲሆን፣ በሥልጠናው ላይ ከኮርፖሬሽኑ ዋና መ/ቤት፣ ከስኳር ፋብሪካዎችና

ፕሮጀክቶች፣ ከመሰረታዊ የሠራተኛ ማህበር እንዲሁም ከኮርፖሬሽኑ የሥራ አመራር ቦርድ የተውጣጡ 48 ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡ በቀጣይም መካከለኛ አመራሮችና ሌሎች ባለሙያዎች ሥልጠናውን በየተቋማቸው ወይም በስኳር አካዳሚ የሚያገኙበት ሁኔታ እንደሚመቻች ተገልጿል፡፡

በሥልጠናው ማጠቃለያ ሠልጣኞች የተዘጋጀላቸውን የሥልጠና ምስክር ወረቀት ከኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ እጅ ተቀብለዋል፡፡

በተያያዘ ዜና ኮርፖሬሽኑ እየተገበረ በሚገኘው የአሠራር ማሻሻያ መሰረት የባለሙያዎችን ሁለገብ አቅም ለማሳደግ ከአምስት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ባደረገው ስምምነት በመጀመሪያ ዙር 90 የሚጠጉ ባለሙያዎች በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ የከፍተኛ ትምህርት ዕድል አግኝተው በትምህርት ላይ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ ባሻገር በስኳር አካዳሚ ለኢንደስትሪው ነባር ባለሙያዎችና አዲስ ለሚቀጠሩ ሠራተኞች አጫጭር ሥልጠናዎች እየተሰጡ ነው፡፡

Related posts