ለንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ማዘጋጃ የሚያገለግል ከ3 ሚሊዮን ሊትር በላይ ቴክኒካል አልክሆል አለ

ለንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ማዘጋጃ የሚያገለግል ከ3 ሚሊዮን ሊትር በላይ ቴክኒካል አልክሆል በፊንጫአ እና በመተሐራ ስኳር ፋብሪካዎች ይገኛል፡፡ ፋብሪካዎቹ በቀን 100 ሺህ ሊትር የሚጠጋ ቴክኒካል አልክሆል በማምረት ላይ ናቸው፡፡

በአሁኑ ወቅት በአለም ደረጃ የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስ/COVID 19 ወረርሽኝ ሥርጭትን ለመከላከል የሚያገለግሉ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ለማዘጋጀት በግብዓትነት የሚውለውን  ቴክኒካል አልክሆል የምርት መጠን ለማሳደግ ስኳር ኮርፖሬሽን ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡

በቂ ቴክኒካል አልክሆል በመኖሩም በተፈቀደላቸው ኮታ መሰረት ምርቱን እየወሰዱ ከሚገኙ ፋርማሲዎችና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ አምራች ፋብሪካዎችና ድርጅቶች በተጨማሪ ስኳር ኮርፖሬሽን ከንግድና ኢንደስትሪ ሚኒስቴር እና ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ተጨማሪ ሰባት አዳዲስ ድርጅቶች ቴክኒካል አልክሆል እንዲወስዱ ፈቅዷል፡፡ ድርጅቶቹም ምርቱን ለመውሰድ በግዢ ሂደት ላይ ናቸው፡፡

ከስኳር ተጓዳኝ ምርቶች አንዱ የሆነውና 96 በመቶና ከዚያ በላይ የአልክሆል ይዘት ያለው ቴክኒካል አልክሆል ከንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ጋር በተያያዘ ለሳኒታይዘር፣ ለደረቅና ፈሳሽ ሳሙና እንዲሁም ለዲቶል (ለመጸዳጃ ቤት ማጽጃ) መስሪያ በግብዓትነት ያገለግላል፡፡

 

Related posts