የስኳር አካዳሚ

በስኳር ልማት ዘርፍ የዕውቀት፣ የክህሎትና የአመለካከት ክፍተቶችን በመሙላት የቴክኖሎጂና የዕውቀት ሽግግር ለማምጣት ታሳቢ ተደርጎ በ2009 ዓ.ም. ወንጂ ላይ የተቋቋመው ‘የስኳር አካዳሚ’ ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ የተለያዩ የሙያ ሥልጠናዎችን በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

አካዳሚው ሲቋቋም ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ሀገራት ልምድ ተወስዶና የረጅም ጊዜ ስትራቴጂያዊ ሠነዶች ተዘጋጅተው ነው ወደ ሥራ የተገባው፡፡ በተጨማሪም በ12 የሙያ መስኮች የሙያ ደረጃና የሥርዓተ ትምህርት እንዲሁም ለሥልጠናው የሚያገለግሉ የማስተማሪያ ሞጁሎች ከፍተኛ ልምድ ባላቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ተዘጋጅተዋል፡፡ የሚሰጡ ሥልጠናዎችም ከተዘጋጀው የሙያ ደረጃ የብቃት አሃዶች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዲኖራቸውና የጥራት ማረጋገጫ እንዲያገኙ ጥሩ መደላድል ተፈጥሮ መደበኛ የሥልጠና ፕሮግራም ለመጀመር እየተሰራ ይገኛል፡፡

አካዳሚው በአሁኑ ወቅት በስኳር ኢንደስትሪ እና ተያያዥ ዘርፎች ማለትም በእርሻና በፋብሪካ ኦፕሬሽንና ጥገና እንዲሁም በሥራ አመራር ኮርሶች በሰርተፊኬት ደረጃ ሥልጠና እየሰጠ ይገኛል፡፡ በዚህም አሁን ባለበት ደረጃ በዓመት ከ400 እስከ 600 ሠልጣኞችን የማስመረቅ አቅም ላይ ደርሷል፡፡

ወደፊት አካዳሚውን በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የስኳር የልህቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ማዕከል እንዲሆን ለማስቻል ፍኖተ-ካርታ ተዘጋጅቶ የአጭርና የረጅም ጊዜ ስትራቴጅያዊ ግቦችን በማስቀመጥ በመደበኛ (Regular)፣ በቅድመ ሥራ (pre-service) እና በአጭር ጊዜ የክህሎት ማሻሻያ (short term) የሥልጠና ፕሮግራሞች ለማሠልጠን እቅድ ተይዞ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል፡፡

በቀጣይ የቀጠናዊ ትስስር ፎረምን በመጠቀምና ከተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር በረጅም ጊዜ ዕቅድ በመጀመሪያ፣ በማስተርስ እና በዶክትሬት ዲግሪዎች ደረጃ በዓመት ከ2000 በላይ ባለሙያዎችን ለማስመረቅ ግብ ተቀምጧል፡፡

የስኳር አካዳሚው የተግባር ላይ ሥልጠናዎችን ለመስጠት የሚያስችሉ ፋሲሊቲዎች ያደረጀ ሲሆን፣ የቀድሞውን የወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካና ወርክሾፕ በማሻሻል ለተግባር ተኮር ሥልጠና እንዲውል ተደርጓል፡፡ እንዲሁም የቤተ-መጽሐፍት አገልግሎት፣ የመማሪያ ክፍሎችና ፋሲሊቲዎችን ጨምሮ ምቹ የሆኑ የመኝታ ክፍሎችና ዘመናዊ የመመገቢያ አዳራሽ አካቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት አካዳሚው በሀገር አቀፍ ደረጃ የማሠልጠኛ እና የምዘና ማዕከል እውቅና እንዲያገኝ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡