ስኳርን ከኦሞ ገነት…

ለተነሳበት ሀገር ምንም አይነት ጥቅም ሳይሰጥ ለዘመናት ለም አፈር ተሸክሞ ወደ ጎረቤት ሀገር ይጋልብ የነበረው የኦሞ ወንዝ ዛሬ ላይ በኢትዮጵያውያን ተገርቶ ለስኳር ምርት ወሳኝ ሃብት በመሆን እያገለገለ ይገኛል፡፡ በቅርቡ ለተመረቀው የኦሞ ኩራዝ ቁጥር ሦስት እና ለቁጥር ሁለት ስኳር ፋብሪካዎች ግብዓት የሚውል አገዳን በማልማትም አጋርነቱን አስመስክሯል፡፡

ዛሬ በዚህች መጣጥፍ ለመተረክ የፈለግነው ስለኦሞ ወንዝ ሳይሆን ይልቁንም ወንዙን ተገን አድርጎ ስለተገነባው የኦሞ ኩራዝ ቁጥር ሦስት ስኳር ፋብሪካ ይሆናል፡፡ በቅድሚያ ግን የስኳር ኢንዱስትሪ በኢትዮጵያ እንዴት እንደተጀመረ በምናብ ልናስቃኛችሁ ስለወደድን ከዛሬ 65 ዓመት በፊት የነበረውን ታሪክ እነሆ ከብዙ በጥቂቱ አቅርበናል፡፡

በተፈጥሮ ሀብቶቻቸው የቋመጡባቸውን፣ በፀጋዎቻቸው የጎመዡባቸውን አገራት ኃያላኑ መንግስታት በቅኝ ግዛታቸው ሥር ለማዋል መሰናዶዋቸውን ያጠናቀቁበት፤ ባለጸጋዎቹ ጉልበታቸውን የፈተኑበትና የታጠቋቸውን የጦር መሣሪያዎች አቅም የፈተሹበት ወቅት ነበር – ሁለተኛው የዓለም ጦርነት፡፡

የጦር ጀቶች ሰማያዊውን አየር ሠላም የነሱበት፣ ቦንቦች እየተወረወሩ፣ ታንኮችና መድፎች እያጓሩ ፀጥ ባለው ቀዬ ሽብር የሚለቁበት፣ ፍጡራን እዚህም እዚያም ወድቀው የታዩበት፣ መንገዶች በአስከሬን የተሞሉበት፣ ግዙፎቹ ሕንጻዎች፣ ድልድዮችና ማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ወደ ፍርስራሽነት የተቀየሩበት፣ ምድር ሲዖል ሆና የታየችበት ወቅት – ሁለተኛው የዓለም ጦርነት፡፡

ይህን የጥፋትና የእልቂት ክፉ ድግስ ለማስተናገድ ዕጣ ፈንታቸው ከነበሩት አገሮች መሀል ኢንዶኔዥያ አንዷ ነበረች፡፡ በጃፓን ወራሪዎቿ አይሆኑ ሆና ተደቋቁሳለች፡፡ በዚህች አገር አያሌ የሰው ሕይወት ጠፍቷል፤ ሀብትና ንብረት ወድሟል፡፡

በዘግናኝነቱና በአውዳሚነቱ ከሰዎች አዕምሮ ዝንተ – ዓለም የማይጠፋው ይህ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከመካሄዱ ቀደም ባሉት የዋዜማዎቹ ጊዜያት መኖሪያቸውን በኢንዶኔዥያ አድርገው የነበሩ የቀድሞዎቹ ቅኝ ገዥዎቻቸው ይኸኔ ምክር ያዙ፡፡

መጓጓዣ ብስክሌቶቻቸውንና አውቶሞቢሎቻቸውን እያቃጠሉ፣ ይገለገሉባቸው የነበሩ የቤት ውስጥ ቁሳቁሶቻቸውን ሳይቀር እያወደሙ ወደ አገር ቤት ለመመለስ በአንድ ተስማሙ – ሆላንዳውያኑ፡፡ ይህን የፈጸሙት ታዲያ የወቅቱ ወራሪዎቹ ጃፓኖች ንብረታቸውን ወርሰው መልሰው እንዳይጠቀሙባቸው በሚል እሳቤ ነበር – እናም አደረጉት፡፡

በዓለማችን በግዙፍነቱ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ የሆነውና በሆላንዳውያኑ የሚተዳደረው የአምስተርዳም የንግድ ማህበረሰብ ኤች.ቪ.ኤ የተሰኘው ኩባንያም መቀመጫውን በኢንዶኔዠያ አድርጎ ኖሯል፡፡

ኤች.ቪ.ኤ ኔዘርላንድስ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ቡና፣ የሻይ ቅጠል፣ የጎማ ዛፍ፣ የወይራ ዘይትና ካሳቫን ጭምር የሚያመርቱ ከ36 ያላነሱ ኩባንያዎች ባለቤት ነው፡፡

በስሩም ከ170 ሺህ በላይ ሠራተኞችን ያስተዳድር ነበር – ያኔ፡፡ በተለያዩ አገራት ካቋቋማቸው ኩባንያዎች መካከልም 15ቱ ያመርቱ የነበሩት ስኳር ሲሆን፣ አንደኛው የስኳር አምራች ኩባንያም በኢንዶኔዥያ ነበር የሚገኘው፡፡

ኢንዶኔዥያ በጃፓን የመወረሯ ጉዳይ አይቀሬ መሆኑን ሆላንዶቹ ሲያውቁ በአጭር ቀናት ውስጥ ይህን የስኳር ፋብሪካ ነቃቅለው ረዥም አመታት ከሰሩበት ከዚያች አገር ወጡ፡፡ የፋብሪካውን ግዙፍ ማሽነሪዎችም በትልልቅ መርከቦች ጫኑና መዳረሻቸውን በምሥራቃዊቷ የአፍሪካ አገር ኢትዮጵያ – ወንጂ ላይ አደረጉ፡፡

የሆላንድ ቅኝ ግዛት የነበረችውን ኢንዶኔዥያን ጃፓኖች ሙሉ በሙሉ ሲቆጣጠሩ ደቾቹ የስኳር ፋብሪካውን ነቅለው ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት ከአዲስ አበባ በ110 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ወንጂ ለአገሪቱ የመጀመሪያው የሆነውን ስኳር ፋብሪካ ተከሉ፡፡ በወቅቱ ኤች.ቪ.ኤ. ኔዘርላንድስ ኩባንያ ለሥራው የሚሆነውን የአምስት ሺህ ሔክታር መሬት የሊዝ ስምምነት ከኢትዮጵያ ጋር ፈጸመ – በሽርክና ለመሥራት ጭምር፡፡

የፋብሪካ ተከላና የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ቀጠለ፤ መንገዶችና ድልድዮች፣ አዋሽን በመጥለፍ የማሳ ዝግጅትና የመስኖ ቦዮች ሥራም ተቀላጠፈ፡፡ ይኸኔ ለአካባቢው ነዋሪዎች በመሬት ዝግጅት፣ በሸንኮራ አገዳ ተከላና በአገዳ ቆረጣ የሥራ ዕድል ተፈጠረ – በወንጂ፡፡

የወንጂ ስኳር ፋብሪካ ግንባታ ተጠናቆ መጋቢት 11 ቀን 1946 ዓ.ም. በቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ተመርቆ ማምረት ጀመረ፡፡ “በኢትዮጵያ የተሰራ” የሚል ጽሑፍ ያለበት የስኳር ጆንያ ለመጀመሪያ ጊዜ በመላ አገሪቱ ለእይታ የበቃው ይኼኔ ነበር፡፡

ኩባንያው በመቀጠልም በ1953 የወንጂ ደስታ ከረሜላ ፋብሪካ፣ በ1955 ዓ.ም. በዚያው በወንጂ ሁለተኛውን ሸዋ ስኳር ፋብሪካ እንዲሁም በ1962 ዓ.ም. ደግሞ “ኤች.ቪ.ኤ መተሐራ” በሚል ሥያሜ ሦስተኛውን የስኳር ፋብሪካ ገንብቶ ሥራ አስጀምሯል፡፡ በዚህም ተግባር በወቅቱ በአገሪቷ በሠራተኞች ቅጥር ብዛትና በግብር ክፍያ ትልቁን ሥፍራ ይዞ በመቆየቱ የኢትዮጵያ ዕድገት ተምሳሌት እንዲሆን አስችሎታል፡፡

የሆላንዱ ኤች.ቪ.ኤ ኩባንያ በወቅቱ በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋዩን እንዲያፈስ ካስቻሉት ምቹ ሁኔታዎች መካከል ሠላም አንዱና ዋንኛው ነበር፡፡ ይህንን እውነታም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ ከኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂና ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር በመሆን የስኳር ኢንዱስትሪ ቴክኖሎጂ የደረሰበትን ደረጃ ባሟላ መልኩ ተገንብቶ የተጠናቀቀውን የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 ስኳር ፋብሪካ ጥቅምት 4 ቀን 2011 ዓ.ም. በመረቁበት ወቅት በንግግራቸው ደግመውታል – የሠላም ዋጋ ከፍተኛ መሆኑን፡፡

“ከ65 ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ የስኳር ኢንዱስትሪ የአጀማመር መነሻ በምስራቅ ኤዥያ የነበረው ጦርነት በአካባቢው ኢንቨስት ያደርጉ የነበሩ የሆላንድ ባለሀብቶች ጦርነቱንና ግጭቱን ሸሽተው ሰላም ወደ ሰፈነባት ኢትዮጵያ በመምጣት ለመጀመሪያ ጊዜ ከስኳርና ከኢንዱስትሪው ጋር እንድንተዋወቅ አደረጉን፡፡ ለማንኛውም ልማትና ምርጥ ሃሳብ መነሻው ሠላም መሆኑን የስኳር ኢንዱስትሪ አጀማመራችን በራሱ በቂ ትምህርት ሰጥቶናል፡፡” ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 ስኳር ፋብሪካ ግንባታ መጠናቀቅና ወደ ሥራ መግባት ኢትዮጵያውያን በሌሎች አገሮች ያሉ ታላላቅና አስደናቂ ሥራዎችን አይተን የምናደንቅ ብቻ ሳንሆን ትልቅ አስበንና ሰርተን መጨረስ እንደምንችል ጭምር ያረጋገጠ ፋብሪካ መሆኑን በንግግራቸው ጠቅሰዋል፡፡

በኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት የተጠናቀቁትን ሁለት ፋብሪካዎች ጨምሮ በመገንባት ላይ የሚገኙት ሌሎች ሁለት የስኳር ፋብሪካዎች የአገሪቱን ስኳር የማምረት አቅም በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጨምሩም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ የተናገሩት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም በፕሮጀክቱ ያልተነካ እምቅ የልማት አቅም ስለመኖሩ ሲያስረዱም “በዚህ ፕሮጀክት ለልማት ሊውል የሚችል ሰፊ መሬት፣ ውሃ፣ በተግባር ተምሮና ሰልጥኖ የተዘጋጀ የሰው ኃይል                              አለ፡፡ በመሆኑም የስኳር ፍላጎት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ እና በሌላውም ዓለም እያደገ በመሆኑ ያለንን አቅም አስፍተን ስኳር፣ ሰሊጥ፣ ሩዝ፣ በቆሎና ስንዴ የመሳሰሉትን በማምረት የምግብ ፍጆታችንን ለማሟላት እንሰራለን፡፡ ከውጭ የምናስገባቸውን የምግብ ግብአቶች በማስቀረትም በምትኩ ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመቀነስ ሰፊ እድል መፍጠር ይቻላል፡፡” ብለዋል፡፡

በንግግራቸው ማጠቃለያም ከ100 ኪሎ ሜትር በላይ የዋና መስኖ ቦይ (Main canal) የተዘረጋበትና በሺዎች ሄክታር የሚቆጠር መሬት በመስኖ ማልማት የተቻለበት ይህን የመሰለ ግዙፍና ዘመናዊ ፋብሪካ ገንብቶ ውጤታማ ማድረግ መቻሉ ብዙ ትምህርት የተቀሰመበትና ለቀጣይ ጉዞም በር የከፈተ ነው ብለዋል፡፡

በፋብሪካው የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ በእንግድነት የተገኙት የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በበኩላቸው “እናንተ ኢትዮጵያውያን ይህንን ግዙፍ ፕሮጀክት ማሳካት በመቻላችሁ እንኳን ደስ አላችሁ” ብለዋል፡፡

“የኦሞ ኩራዝ 3 ስኳር ፋብሪካ ለምረቃ መብቃት ኢትዮጵያ ያላትን የልማት፣ የማደግና የመለወጥ አቅም ያሳየችበት ዐብይ ተግባር ነው” ያሉት ፕሬዚዳንቱ አገራቸው ከዚህ የምትቀስማቸው በርካታ ቁም ነገሮች እንዳሉም ነው የተናገሩት፡፡ ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉም በምረቃው ላይ ተጋብዘው ይህንን ታላቅ ፕሮጀክት ለማየት በመብቃታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡

የስኳር ኮርፖሬሽን የቀድሞ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ እንዳወቅ አብቴም የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸውን ሲጀምሩ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ከ65 ዓመታት በፊት ለኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን የወንጂ ስኳር ፋብሪካ አመሰራረትን በዳራነት በመጥቀስ ነበር፡፡

እንደእሳቸው ገለጻ በዚህ ሁኔታ በኢትዮጵያ መመረት የጀመረው የስኳር ምርት አገሪቷ በተከታታይ እያስመዘገበች ከመጣችው የምጣኔ ሃብት እድገት፣ እያደገ ከመጣው የሕዝብ ብዛትና የዘመናዊ አመጋገብ ባህል እንዲሁም ስኳርን በግብአትነት ተጠቅመው ሌሎች ምርቶችን የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች መበራከት ጋር ተዳምሮ የስኳር ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መጥቷል፡፡

ይህንን እውነታ የተገነዘበው መንግሥት በ2003 ዓ.ም. የስኳር ኮርፖሬሽንን በአዋጅ በማቋቋም 10 አዳዲስ የስኳር ፋብሪካዎችን በአንደኛውና ሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ለመገንባት እና በ300 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሸንኮራ አገዳ ለማልማት በማቀድ ወደ ስራ ገብቷል ያሉት አቶ እንዳወቅ ከታቀዱት ፋብሪካዎች ውስጥም በተለያዩ አመታት ከሰም፣ ተንዳሆ፣ አርጆ ዲዴሳና ኦሞ ኩራዝ ቁጥር 2 ፋብሪካዎች ከነችግሮቻቸው ተጠናቀው ምርት መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ ዓመታዊ የስኳር ፍላጎት ከ600 ሺህ እስከ 700 ሺህ ሜትሪክ ቶን ገደማ እንደ ደረሰ የጠቆሙት የቀድሞ ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ አሁን በሥራ ላይ ከሚገኙ የስኳር ፋብሪካዎች ምርት አገራዊ የስኳር ፍላጎትን 50% የመሸፈን አቅም ላይ ተደርሷል ብለዋል፡፡ ስኳር ኮርፖሬሽን በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እያስገነባቸው የሚገኙ ሁሉም ፋብሪካዎች ግንባታ ሲጠናቀቅ አመታዊ የስኳር ምርት መጠኑ እስከ 22.5 ሚሊዮን ኩንታል በአመት ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው የቀድሞ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ያስታወቁት፡፡

በመንግሥት ውሳኔ ከብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ተቀምቶ በኮንትራት የተሰጠውን የከሰም ስኳር ፋብሪካ ግንባታ በአጭር ጊዜ ያከናወነው፣ በኦሞ ኩራዝ 2 ግንባታም ይህንኑ አፈጻጸሙን የደገመው እንዲሁም እጅግ ዘመናዊ የሆነውን የኦሞ ኩራዝ 3 ፋብሪካን የገነባው የቻይናው ኮምፕላንት ኩባንያ የኢትዮጵያ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሁ ጂያንሊያንግ በምረቃው ላይ ተገኝተው የኦሞ ኩራዝ 3 ስኳር ፋብሪካ ግንባታ መጠናቀቅና ምርት መጀመር ለኢንዱስትሪው ዕድገት አንድ አጋዥ ኃይል ነው ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ለፋብሪካው ግንባታ የገንዘብ ብድር የሰጠው የቻይናው ልማት ባንክ የኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ቡ ዪ ደማቅ በነበረው የምረቃ ሥነ ስርዓት ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ባንካቸው ለስኳር ኢንዱስትሪው ዋና የገንዘብ ምንጭ ከሆኑ ተቋማት መካከል አንዱ መሆኑን ገልፀው፣ እስካሁን ለከሰም፣ ለኦሞ ኩራዝ 2 እና 3 ስኳር ፋብሪካዎች 703 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር አበድረናል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ በቀጣይ ጊዜያት ዕቅዶቹን በማሳካት በዓለም ዓቀፍ ገበያ ተወዳዳሪና ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ እንደሚሆን ያላቸውን እምነትም በንግግራቸው ማጠቃለያ ገልጸዋል፡፡

በአጠቃላይ የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 ስኳር ፋብሪካ ግንባታ በስኬት መጠናቀቅ በቀጣይ በአካባቢው ለሚካሄዱ ሰፋፊ የልማት ሥራዎች ፈር ቀዳጅ ነው፡፡ የስኳር ኢንዱስትሪውን ባለሙያዎች ከዘርፉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጋር በማስተዋወቅ ረገድም ጉልህ ሚና ይኖረዋል፡፡ በመሆኑም የፋብሪካው እዚህ ደረጃ መድረስ ለስኳር ኮርፖሬሽንም ሆነ ለመንግሥት ታላቅ ስኬት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡

እንግዲህ በዚህ መልክ የኦሞ ወንዝን መሰረት አድርገው እየተገነቡ ከሚገኙት አራት ስኳር ፋብሪካዎች ውስጥ በኦሞ ኩራዝ ቁጥር 2 የተጀመረው ስኬት እነሆ ወደ ቁጥር 3 ተሸጋግሯል፡፡ የቀሪዎቹን ሁለት ፋብሪካዎች ግንባታም በፍጥነት በማጠናቀቅ ስኳርን ከኦሞ ገነት ለማፈስ ጥረቱ ቀጥሏል፡፡

Related posts

Leave a Comment