ስድስት የስኳር ፋብሪካዎች ከወራት በኋላ ወደግል ይዞራሉ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 17 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የገንዘብ ሚኒስቴር ስድስት የስኳር ፋብሪካዎች ከወራት በኋላ ወደ ግል እንደሚዞሩ አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ በኢትዮጵያ የስኳር ኢንዱስትሪ ማሻሻያ ላይ ትኩረት የሚያደርግ የውይይት መድረክ ይፋ አድርጓል።

የገንዘብ ሚኒስትር ዲኤታው ዶክተር እዮብ ተካልኝ በጉዳዩ ዙሪያ በሰጡት መግለጫ፥ አሁን ላይ በመንግስት ስር ያሉ 13 የስኳር ፋብሪካዎች የቴክኒክ፣ የዋጋ፣ የማህበራዊና የአካባቢ ጥበቃ ጥናቶች እየተከናወነላቸው ይገኛል ብለዋል።

ጥናቱ በመጭው ታህሳስ ወር ይጠናቀቃል ያሉት ሚኒስትር ዲኤታው፥ ከዚህ ውስጥ ስድስቱ ወደግሉ እንደሚዞሩ ተናግረዋል።

ከዚህ አንጻርም ከገዥዎች የማዞር ሂደቱን መጀመር በሚያስችል መልኩ ጠቃሚ ግብዓት መሰብሰቡንም አስረድተዋል።

ሚኒስቴሩ ግልጽና ሁሉን አሳታፊ የሆነ የጨረታ ሂደት ይፋ እንደሚያደርግም አስረድተዋል።

የግሉ ዘርፍ በስኳር ፋብሪካዎች ላይ የሚያደርገው ተሳትፎ የፋብሪካዎቹን ምርታማነት ለማሳደግና፥ ያለውን የስኳር ፍላጎት በማሟላት ለውጭ ገበያ ተደራሽ የመሆን እድልን ይፈጥራልም ነው ያሉት።

ሚኒስትር ዲኤታው እስካሁን በመንግስት በኩል የስኳር ፋብሪካዎችን ለማስፋት የተደረው ጥረት ጫና ከማሳደር ያለፈ ጠቀሜታ እንዳላስገኘም አውስተዋል።

ዛሬ ይፋ የሆነው የውይይት መድረክ በርካታ ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት ሲሆን በሃገሪቱ ረቂቅ የስኳር ፖሊሲና ደንብ ዙሪያ ይመክራል።

የኢትዮጵያ መንግስት የግሉ ዘርፍ በሃገሪቱ ኢኮኖሚ ያለውን ሚና የሚያጎለብት የኢኮኖሚ ማሻሻያ በማካሄድ ላይ ይገኛል።

Related posts