በስኳር ምርምርና ልማት ረቂቅ ፍኖተ-ካርታ ላይ አውደ ጥናት ተካሄደ

  • በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ድጋፍ የሚካሄዱ ሁለት የስኳር ቴክኖሎጂ የምርምር ፕሮጀክቶችም ቀርበዋል
  • በምርምር የተገኙ አራት ሀገር በቀል የሸንኮራ አገዳ ዝርያዎችም ተመርቀዋል

በስኳር ልማት ዘርፍ የተቀመጡ ግቦችን ማሳካት አላማው ያደረገ የስኳር ምርምርና ልማት ፍኖተ-ካርታ ረቂቅ ዝግጅት ላይ ግንቦት 30/2011 ዓ.ም በአዳማ ከተማ አውደ ጥናት ተካሂዷል፡፡

በስኳር ኮርፖሬሽን የምርምርና ልማት ዋና ማዕከል አዘጋጅነት በተካሄደው በዚህ አውደ ጥናት ላይ ከረቂቅ ፍኖተ ካርታው ሰነድ በተጨማሪ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የገንዘብ ድጋፍ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ የሚተገበሩ ሁለት የስኳር ቴክኖሎጂ ምርምር ፕሮጀክቶች ስራ በይፋ መጀመሩ ተበስሯል፡፡

በአውደ ጥናቱ ላይ የተገኙት የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወዮ ሮባ ባደረጉት ንግግር፣ የተዘጋጀው ረቂቅ ፍኖተ ካርታ ለስኳር ኢንደስትሪው ትራንስፎርሜሽን ወሳኝ ከመሆኑም ባሻገር በኮርፖሬሽኑ እየተካሄደ ለሚገኘው የሪፎርም አካል በመሆኑ ወቅታዊ ትኩረት የሚሰጠው አጀንዳ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አክለውም በሪፎርሙ አማካይነት ከዚህ ቀደም በሀገር ውስጥና በውጪ ሀገራት ከሚገኙ ከፍተኛ የምርምር ተቋማት፣ ግብዓት አቅራቢዎችና ሌሎች መሰል ድርጅቶች ጋር ኮርፖሬሽኑ የነበረበትን ተቀናጅቶ የመስራት ክፍተት ለማጥበብና ኢንዱስትሪውን በጋራ ለማሳደግ ትኩረት ሰጥተን እንሰራለን ብለዋል፡፡

አውደ ጥናቱን በንግግር የከፈቱት በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የሰላም ሚኒስትር አማካሪ እና የስኳር ኮርፖሬሽን የሥራ አመራር ቦርድ አባል አቶ ካይዳኪ ገዛኸኝ በበኩላቸው ፍኖተ-ካርታው ስኳር ኢንደስትሪው በዓለም ተወዳዳሪ እንዲሆን ከፍተኛ ድርሻ አለው ካሉ በኋላ፣ ረቂቅ ሰነዱ የበለጠ እንዲዳብር የባለድርሻ አካላት ልምዳቸውንና እውቀታቸውን እንዲያካፍሉ ጥሪ አድርገዋል፡፡

በንግግራቸው ማጠቃለያም የስኳር ልማት ዘርፍ በምርምር ከተደገፈ በእስካሁኑ የልማት ጥረቶች የተገኙ አበረታች ውጤቶችን በማሳደግና የዘርፉ ቀሪ ሥራዎችን በማጠናቀቅ የኢንዱስትሪውን ብሩህ ተስፋ ሩቅ በማይባል ጊዜ ውስጥ ማረጋገጥ ይቻላል ብለዋል፡፡

የአውደ ጥናቱ አንዱ አካል የነበረው አውደ ርዕይም በክብር እንግዶችና ተሳታፊዎች ተጎብኝቷል፡፡ በዚህ ወቅት በምርምርና ልማት ዋና ማዕከል ባልደረባና ከፍተኛ ተመራማሪ በዶ/ር ኢሳያስ ጠና አማካይነት በምርምር የተገኙ አራት ሀገር በቀል የሸንኮራ አገዳ ዝርያዎች በአውደ ርዕዩ ቀርበው በስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወዮ ሮባና በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የሰላም ሚኒስትር አማካሪ እና የስኳር ኮርፖሬሽን የሥራ አመራር ቦርድ አባል አቶ ካይዳኪ ገዛኸኝ ተመርቀዋል፡፡

 እነዚህ ዝርያዎች ከነባር ዝርያዎች በተሻለ ሁኔታ ከ20-30 በመቶ አብላጫ ከፍተኛ የስኳር ምርት የሚሰጡ መሆናቸውም በምርቃቱ ወቅት በተመራማሪው ተገልጿል፡፡ አክለውም አዳዲሶቹ ዝርያዎች ከከፍተኛ የስኳር ምርታቸው በተጨማሪ ነባር የሸንኮራ አገዳ ዝርያዎች ለአጨዳ ከሚወስድባቸው ረጅም ጊዜ (ከ18-22 ወራት) ጋር ሲነጻጸር የተሻሻሉት ዝርያዎች ከ13-14 ወራት ጊዜ ውስጥ ይደርሳሉ ብለዋል፡፡

አራቱ ዝርያዎች ግንቦት 23/2011 ዓ.ም ለብሔራዊ ዝርያ አጽዳቂ ኮሚቴ ቀርበው  ለመጀመሪያ ጊዜ በኢንደስትሪው ታሪክ የተለቀቁሀገር በቀል የሸንኮራ አገዳ ዝርያዎች ሆነው መመዝገባቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በአውደ ርዕዩ መዝጊያ መርሃ ግብር ላይ እነዚህን ሀገር በቀል የሸንኮራ አገዳ ዝርያዎች ተጠቅመው ከፍተኛ የስኳር መጠን እንዲያመርቱ የኮርፖሬሽኑ የፋብሪካ ኦፕሬሽንና የእርሻ ኦፕሬሽን ዘርፎች ኃላፊዎች አገዳዎቹን ተረክበዋል፡፡

በእለቱ ረቂቅ ፍኖተ ካርታውን የምርምርና ልማት ዋና ማዕከል ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ነጊ ያቀረቡ ሲሆን፣ የስኳር ቴክኖሎጂ ምርምር ፕሮጀክቶች ሰነዶች ደግሞ በከፍተኛ ተመራማሪዎች ቀርበው በሦስቱም ሰነዶች ላይ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

በመጨረሻም ለአውደ ጥናቱ መሳካት የገንዘብ፣ የቁሳቁስና የቴክኒክ ድጋፍ ያደረጉ ተቋማት ከኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወዮ ሮባ እጅ የተዘጋጀላቸውን የምስጋና የምስክር ወረቀት ተቀብለዋል፡፡

Related posts

Leave a Comment