በስኳር ኮርፖሬሽን አማካይነት እየተካሄደ የሚገኝ የስኳር ፋብሪካዎች እና ፕሮጀክቶች የአክስዮን ሽያጭ አለመኖሩ ተገለጸ

የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ አቶ ጋሻው አይችሉህም

በአሁኑ ወቅት በመንግሥትም ሆነ በስኳር ኮርፖሬሽን አማካይነት እየተካሄደ የሚገኝ የስኳር ፋብሪካዎች እና ፕሮጀክቶች የአክስዮን ሽያጭ አለመኖሩን በስኳር ኮርፖሬሽን የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ አቶ ጋሻው አይችሉህም በተለይ ለኢቲቪ ገልጸዋል።

የስኳር ልማት ፕሮጀክቶች እና ፋብሪካዎችን በሙሉ ወይም በከፊል ወደ ግል ይዞታ ለማዘዋወር መንግስት ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ የገንዘብ ሚኒስቴር በስኳር ኢንዱስትሪው ላይ ለባለሃብቶች እና ኩባንያዎች የመረጃ ጥያቄ አቅርበው በርካቶች በዘርፉ ለመሰማራት ፍላጎታቸውን እየገለጹ መሆናቸው ይታወቃል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ መንግሥት ወይም ስኳር ኮርፖሬሽን ከሚያስተዳድራቸው 13 የስኳር ፋብሪካዎች እና ፕሮጀክቶች ውስጥ ተጨማሪ የኢንቨስትመንት ካፒታል የሚጠይቁ እና በግንባታ ላይ የሚገኙ ስድስት ፋብሪካዎች /ፕሮጀክቶች/ በ2012 ዓ.ም ወደ ግል ይዞታ ለማዘዋወር እየሰራ እንደሚገኝም አቶ ጋሻው ተናግረዋል።

ለአፈጻጸምም ይረዳ ዘንድም አለም አቀፍ እውቅና ያለው የውጭ አማካሪ በስኳር ፋብሪካዎች እና ፕሮጀክቶች የዋጋ ግመታና ተያያዥ ጥናት በማድረግ ላይ እንደሆነም ተገልጿል።

መንግሥት ከባለሃብቶች እና ኩባንያዎች ጋር የሚያደርገውን ድርድር እንዳጠናቀቀ በቅድሚያ ወደ ግል ይዞታ የሚዘዋወሩ ፋብሪካዎችና ፕሮጀክቶች የትኞቹ እንደሆኑ ለሕዝብ ይፋ የሚያደርግ ሲሆን፣ አሁን ላይ የወንጂ ሸዋ እና የመተሐራ ስኳር ፋብሪካዎችንም ሆነ ሌሎቹን ወደግል ይዞታ ለማዘዋወር ከየትኛውም ባለሃብት፣ ኩባንያ ወይም ማኅበር ጋር የተደረገ ይፋዊ ድርድርም ሆነ ስምምነት አለመኖሩን አቶ ጋሻው ገልጸዋል።

በመሆኑም በአሁኑ ወቅት በመንግሥትም ሆነ በስኳር ኮርፖሬሽን አማካይነት እየተካሄደ የሚገኝ የስኳር ፋብሪካዎች እና ፕሮጀክቶች የአክስዮን ሽያጭ እንደሌለ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

EBC

Related posts