በአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የተመራ የልዑካን ቡድን የጣና በለስ ስኳር ልማት ፕሮጀክትን ጎበኘ

በአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ተመስገን ጥሩነህ የተመራና የክልሉን ከፍተኛ አመራሮች እና ባለሃብቶች ያካተተ የልዑካን ቡድን የጣና በለስ ስኳር ልማት ፕሮጀክት የሥራ እንቅስቃሴን መጋቢት 13/2012 ዓ.ም ጎብኝቷል፡፡

በጉብኝቱ ወቅት የጣና በለስ ቁጥር ሶስት ስኳር ፋብሪካ ስለሚገኝበት ሁኔታ እንዲሁም የፋብሪካ ቁጥር አንድ የግንባታ ሂደትና በፕሮጀክቱ እየተካሄደ ስለሚገኘው የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት በፕሮጀክቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በአቶ አንተነህ አሰጌ አማካይነት ለልዑካን ቡደኑ ገለጻ ተደርጓል፡፡

በዚሁ ወቅት ርዕሰ መሰተዳድሩ አቶ ተመስገን ጥሩነህ ባደረጉት ንግግር የፋብሪካ ቁጥር አንድ ግንባታ እንዲፋጠንና ወደ ምርት እንዲገባ የክልሉ መንግሥት ተገቢውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡

በጉብኝቱ የተሳተፉ ባለሃብቶች በበኩላቸው አካባቢው ለልማት አመቺ መሆኑን ገልጸው፣ በክልሉ መንግሥት በኩል አስፈላጊ ሁኔታዎች ከተመቻቹ በጣና በለስ ቁጥር ሦስት ፕሮጀክት ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

በጉብኝቱ ከ40 በላይ የሚሆኑ የክልሉ የቢሮ ኃላፊዎች፣ የአዊ ዞን አስተዳዳሪና ባለሃብቶች ተሳትፈዋል፡፡

Related posts