በወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ አመታዊ የፕላንት ፕሮሰስ ኮንፈረንስ ተካሄደ፡፡

  • የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ የተቋሙ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች እውቅናና የማበረታቻ ሽልማት ተሰጠ

በወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ አመታዊ የፕላንት ፕሮሰስ ኮንፈረንስ ከመስከረም 21-23/2ዐ13 ዓ.ም ድረስ ተካሄደ፡፡

በፋብሪካው የሲኒማ አዳራሽ ለሦስት ቀናት በተካሄደው በዚህ ጉባኤ ላይ የስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ወዮ ሮባ፣ በዋናው መ/ቤት የፕሮጀክት ዘርፍ ም/ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አብርሃም ደምሴና የወንጂ ሸዋ ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ካሳ ተስፋዬን ጨምሮ የፋብሪካው ም/ዋና ሥራ አስኪያጆች፣ የእርሻና የፋብሪካ ኦፕሬሽን ዘርፎች የሥራ ኃላዎችና ሠራተኞች እንዲሁም ከፍተኛ ተመራማሪዎች፣ የሕብረት ሥራ ማህበር ኃላፊዎች፣ የዘርፍ ማህበር አመራሮች እና ሌሎች ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡

መርሃ ግብሩን በንግግር ያስጀመሩት የፋብሪካው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ካሳ ተስፋዬ ለጉባኤው ተሳታፊዎች ባስተላለፉት መልእክት ለበርካታ አመታት ተቋርጦ የቆየው አመታዊ የፕላንት ፕሮሰስ ኮንፈረንስ ዳግም መጀመሩ ለፋብሪካው ችግሮች መፍቻ ቁልፍ ይሆናል ብለዋል፡፡

በጉባኤው ወቅት በፋብሪካና በእርሻ ኦፕሬሽን ዘርፎች ለምርትና ምርታማነት ተግዳሮት የሆኑ ዝርዝር ጉዳዮችን የያዙ ለውይይት መነሻ የሆኑ ጥናታዊ ጽሁፎች በምርምር ማእከል ተመራማሪዎች ቀርበው፣ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

በሌላ ዜና በጉባኤው መዝጊያ ላይ በተደረገው የእውቅና እና የማበረታቻ ሽልማት ሥነ ስርዓት በ2012 በጀት አመት የሞዲፊኬሽን ሥራ በማከናወን ከፍተኛ ወጭ ላዳኑ እና የላቀ የሥራ አፈጻጸም ላስመዘገቡ የፋብሪካው ኃላፊዎችና ሠራተኞች እውቅና እና የገንዘብና የዋንጫ የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

ሽልማቱን የሰጡት የእለቱ የክብር እንግዳ አቶ ወዮ ሮባ ባደረጉት የማጠቃለያ ንግግር ለተሸላሚዎቹ እንኳን ደስ አላችሁ በማለት በስኳር ኮርፖሬሽንና በራሳቸው ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ወደፊትም የላቀ ውጤት ለሚያስመዘግቡ አመራሮችና ባለሙያዎች እውቅናና ሽልማት የመስጠቱ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አክለው ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም በቅርቡ የአዋሽ ወንዝ በፋብሪካው ላይ ሊያደርስ የነበረውን ከፍተኛ ውድመት ለመታደግ በጥብቅ አመራር ለተሰራው ሥራ የፋብሪካውን ማኔጅመንት እና የጎርፍ አደጋውን በመከላከል ረገድ ልዩ ሚና ለነበራቸው ኃላፊዎችና ሠራተኞች እውቅና በመስጠት ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

Related posts