ከሰም ስኳር ፋብሪካ

በአፋር ክልል በዞን ሦሥት አዋሽ ፈንታሌ እና ዱለቻ ወረዳዎች በከሰም ቀበና ሸለቆ ውስጥ ውስጥ የሚገኘው የከሰም ስኳር ፋብሪካ ከአዲስ አበባ 250 ኪ.ሜ፣ ከመተሐራ ስኳር ፋብሪካ ደግሞ 50 ኪ.ሜ. ያህል ይርቃል፡፡

ለመተሐራ ስኳር ፋብሪካ የማስፋፊያ ፕሮጀክት አካል ሆኖ በ2003 ዓ.ም. የግንባታው ቅድመ ዝግጅት የተጀመረው የከሰም ስኳር ፋብሪካ ከመተሐራ ስኳር ፋብሪካ ካለው ርቀትና ከአዋጪነት አንፃር ተጠንቶ ኋላ ላይ ራሱን ችሎ እንደ አንድ የስኳር ፋብሪካ እንዲቋቋም ተደረገ፡፡

ከቻይና ልማት ባንክ በተገኘ 123 ሚሊዮን ዶላር ብድር ኮምፕላንት በተባለ የቻይና ኩባንያ የተገነባው የከሰም ስኳር ፋብሪካ በ2007 ዓ.ም. መጨረሻ የሙከራ ምርቱን አጠናቆ ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ በመደበኛ ሥራ ላይ ይገኛል፡፡

በመጀመሪያው የግንባታ ምዕራፍ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ሲገባ በቀን 6 ሺ ቶን አገዳ የመፍጨት አቅም ያለው ይህ ፋብሪካ፣ በቀጣይ በሚደረግ የማስፋፊያ ሥራ 10 ሺ ቶን ሸንኮራ አገዳ በቀን ወደሚፈጭበት ደረጃ እያደገ ይሄዳል፡፡ ፋብሪካው በመጀመሪያ ምዕራፍ ሙሉ የማምረት አቅሙ ላይ ሲደርስ 1 ሚሊዮን 530 ሺ ኩንታል ስኳር እና 12 ሚሊዮን 500 ሺ ሊትር ኢታኖል በዓመት ያመርታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በተጨማሪም 29 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት እና 16 ሜጋ ዋቱን ለኦፕሬሽን ተጠቅሞ ቀሪውን 13 ሜጋ ዋት ለብሔራዊ የኃይል ቋት (ግሪድ) በማቅረብ ተጨማሪ ገቢ የማስገኘት አቅም አለው፡፡

ወደፊት በሚደረግ የማስፋፊያ ሥራም ፋብሪካው በዓመት 2 ሚሊዮን 600 ሺ ኩንታል ስኳር እና 30 ሚሊዮን ሊትር ኤታኖል የማምረት አቅም ላይ ሊደርስ እንደሚችል የፋብሪካው የዲዛይን አቅም ያመለክታል፡፡

የፋብሪካው አካባቢ 500 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ የመያዝ አቅም ባለው የከሰም ግድብ አማካይነት በ20,000 ሄክታር መሬት ላይ ሸንኮራ አገዳ የሚለማበት ነው፡፡ የአገዳ ልማቱ ከከሰም ሌላ ቦልሀሞን በተሰኘ አካባቢም ይከናወናል፡፡ በፋብሪካው ከሚለማው የሸንኮራ አገዳ በተጨማሪ ከአሚባራ እርሻ ልማት አክሲዮን ማኅበር ጋር በተገባው ውል መሠረት ማኅበሩ በስድስት ሺ ሄክታር መሬት ላይ ሸንኮራ አገዳ እያለማ ለፋብሪካው በማቅረብ ላይ ይገኛል።

የመስኖ መሠረተ ልማት ግንባታ

  • 2,946 ሄ/ር መሬት ውሃ ገብ ተደርጓል፤
  • የ5 ኪ.ሜ የዋና ቦይ ግንባታ ተጠናቋል፤

የአገዳ ልማት

  • በፋብሪካው አማካይነት 2,823 ሄክታር መሬት እንዲሁም በአሚባራ እርሻ ልማት (አውት ግሮወር) 6 ሺ ሄክታር መሬት በአገዳ ተሸፍኗል፤

የቤቶች ግንባታ

  • 648 መኖሪያ ቤቶችና 25 የአገልግሎት መስጫ ብሎኮች ተጠናቀው ለአገልግሎት ቀርበዋል፤

የማኅበረሰብ ተጠቃሚነት

ለአካባቢው ማኅበረሰብ ምጣኔ ሃብታዊና ማኅበራዊ ጠቀሜታ እያስገኘ የሚገኘው የከሰም ፋብሪካ ግንባታው ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ በፕሮጀክቱ፣ በኮንትራክተሮች እንዲሁም በ29 ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች አማካይነት 42,773 ለሚሆኑ የአካባቢው ወጣቶችና ዜጎች ቋሚ፣ ኮንትራትና ጊዜያዊ የሥራ እድሎች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል፡፡

ከዚህ ባሻገር 399 አባላት ያሏቸው አምስት የሸንኮራ አገዳ አብቃይ መሠረታዊ የህብረት ሥራ ማህበራት ከፋብሪካው ጋር በአውትግሮወር ሞዳሊቲ ትስስር በመፍጠርና ሸንኮራ አገዳ አልምተው ለፋብሪካው በማቅረብ የልማቱ ተቋዳሽ በመሆን ላይ ይገኛሉ፡፡

Related posts

Leave a Comment