ወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ

በሀገራችን የስኳር ፋብሪካ ታሪክ ፋና ወጊ የሆነው የወንጂ ስኳር ፋብሪካ በ1946 ዓ.ም. ግንባታው ተጠናቆ ማምረት የጀመረ ሲሆን፣ የሸዋ ስኳር ፋብሪካ ደግሞ እዛው ወንጂ ላይ በ1955 ዓ.ም. ተመርቆ ስራ የጀመረ ሌላኛው ስኳር ፋብሪካ ነው፡፡ ሁለቱም ስኳር ፋብሪካዎች ኤች ቪ ኤ በተባለ የሆላንድ ኩባንያ የተገነቡና በኩባንያውና በመንግሥት የጋራ ባለቤትነት በሽርክና የተቋቋሙ ነበሩ፡፡

በአንድ አስተዳደር ስር እየተዳደሩ ስኳር ያመርቱ የነበሩት ሁለቱ አንጋፋ ፋብሪካዎች በእርጅና ምክንያት ሥራቸውን እስካቆሙበት ጊዜ ማለትም ወንጂ እስከ 2004 ዓ.ም. እንዲሁም ሸዋ እስከ 2005 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ የነበራቸው አማካይ አመታዊ ስኳር የማምረት አቅም 75 ሺ ቶን ወይም 750  ሺ ኩንታል ነበር፡፡

ነባሩን የወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ በአዲስና ዘመናዊ ፋብሪካ ለመተካት የማስፋፊያ ፕሮጀክት በፋብሪካ እና በእርሻ ዘርፍ ተከናውኖ የፋብሪካ ማስፋፊያ ስራው በ2005 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ተጠናቆ በ2006 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ ፋብሪካው ስራ ጀመረ፡፡ አዲሱ ስኳር ፋብሪካ የተገነባው ነባሮቹ በሚገኙበት የኦሮሚያ ክልል ምስራቅ አርሲ ዞን ዶዶታ ወረዳ ቢሾላ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነው፡፡

ከአዲስ አበባ በ110 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኘው ይህ ፋብሪካ በቀን 6 ሺ 250 ቶን አገዳ በመፍጨት በዓመት ከ1 ሚሊዮን 740 ሺ ኩንታል በላይ ስኳር የማምረት አቅም አለው፡፡ ወደፊት የማምረት አቅሙን በሂደት በማሳደግ በቀን ወደ 12 ሺ 500 ቶን አገዳ እየፈጨ ዓመታዊ የስኳር ምርት መጠኑን እስከ 2 ሚሊዮን 227 ሺ ኩንታል እንደሚያሳድግ ታሳቢ ተደርጎ የተገነባ ነው፡፡

ከዚህ ዘመናዊ የስኳር ፋብሪካ ተረፈ ምርት በዓመት እስከ 12 ሚሊዮን 800 ሺ ሊትር የሚደርስ ኤታኖል ለማምረት የሚያስችል የኤታኖል ፋብሪካ ለመገንባት ታቅዷል፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ረገድም 31 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት 11 ሜጋ ዋቱን ለራሱ ተጠቅሞ፣ ቀሪውን 20 ሜጋ ዋት ለብሔራዊ የኃይል ቋት እያስገባ ይገኛል፡፡

የፋብሪካው የአገዳ እርሻ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ዋቄ ጢዮ፣ ሰሜን ዶዶታ እና ወለንጪቲ ተብለው በሚታወቁ አካባቢዎች እየተካሄደ ይገኛል፡፡ የእርሻ ማስፋፊያ ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ አዲሱ ፋብሪካ በአጠቃላይ 16 ሺ ሄክታር የሸንኮራ አገዳ መሬት ይኖረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከለማው 12 ሺ 800 ሄክታር የሸንኮራ አገዳ መሬት ውስጥ 7 ሺ ሄክታሩ በፋብሪካው አካባቢ በሚገኙ በ31 የሸንኮራ አገዳ አብቃይና አቅራቢ ማኀበራት በታቀፉ 9 ሺ 319 አርሶ አደሮች  የለማ ነው፡፡ በዚህም አባላቱ በሚያገኙት ከፍተኛ ገቢ ከልማቱ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ለአብነትም በአንዳንድ ማህበራት በአማካይ በየ18 ወራት በሚደረግ የትርፍ ክፍፍል አባላት እንደየስራቸው መጠን በነፍስ ወከፍ ከ50 ሺ እስከ 240 ሺ ብር ድረስ ገቢ ያገኙበትን አጋጣሚ መጥቀስ ይቻላል፡፡

ፋብሪካው ለአርሶ አደሮቹ በመስኖ የለማ መሬት በማዘጋጀት፣ የምርጥ ዘር አቅርቦት በማመቻቸት፣ ሙያዊና ቴክኒካዊ ድጋፍ በመስጠት አርሶ አደሮቹ ሸንኮራ አገዳ አልምተው ለፋብሪካው በመሸጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሯል፡፡

Related posts

Leave a Comment