የስኳር ልማት ዘርፍን ካለበት ችግር ለማላቀቅ የድርሻውን ኃላፊነት እንደሚወጣ የስኳር ኮርፖሬሽን ሥራ አመራር ቦርድ ገለጸ

  • አዲስ የተሾሙት የቦርድ ሰብሳቢና ሌሎች ሦስት አባላት ከተቋሙ ማኔጅመንት ጋር ተዋውቀዋል

የስኳር ልማት ዘርፍን ካለበት ችግር በማውጣት ኢንዱስትሪው ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ በአዲስ መልክ የተሰየመው የስኳር ኮርፖሬሽን የሥራ አመራር ቦርድ ገለጸ፡፡

ቦርዱ በኮርፖሬሽኑ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ሰኔ 13/2011 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ ኢንደስትሪውን ካለበት ችግር ለማላቀቅና በዘርፉ የታለሙትን ግቦች ለማሳካት አዲስ ስትራተጂ በፍጥነት ነድፎ ተግባራዊ ማድረግ ይገባል ብሏል፡፡

የእለቱን ስብሰባ የመሩት አቶ በየነ ገብረመስቀል የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር እና የስኳር ኮርፖሬሽን የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ እራሳቸውን እና ሌሎች ሦስት አዳዲስ የቦርድ አባላትን ካስተዋወቁ በኋላ የስብሰባውን አጀንዳዎች ለቤቱ አቅርበዋል፡፡

በዚህ መሰረት የተቋሙ የሪፎርም እቅድ በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ፣ የስኳር ልማት ፕሮጀክቶች የፊዚካልና የፋይናንስ አፈጻጸም፣ ሂሳብ የመዝጋት ሁኔታ፣ የውስጥና የውጭ ኦዲት ያለበት ደረጃ፣ ከሚያዝያ 2011 ዓ.ም. እስከ ህዳር 2012 ዓ.ም ድረስ ያለው የስምንት ወራት እና የቀጣዮቹ አምስት አመታት የገንዘብ ፍሰት፣ ከሀገር ውስጥና ከውጭ የተገኘው ብድርና የክፍያ ሁኔታ እንዲሁም የ2012 በጀት ዓመት ዕቅድ ዝግጅት በኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወዮ ሮባና በፋይናንስ ዘርፍ ም/ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መላኩ ሰጥአርጌ በማብራሪያ መልክ ቀርበው ቦርዱ ተወያይቶባቸዋል፡፡

ከውይይቱ በኋላ የኮርፖሬሽኑ ዋና መ/ቤት፣ የስኳር ፋብሪካዎችና ፕሮጀክቶች ያልተዘጋ ሂሳብ እስከ ሐምሌ 2011 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ ተጠናቆ ለቦርዱ ሪፖርት እንዲደረግ ተወስኗል፡፡ በተጨማሪ ቦርዱ የሰጠውን የሥራ መመሪያና አስተያየት ያካተተ የኮርፖሬሽኑ የ2012 በጀት ዓመት እቅድ ተዘጋጅቶ በቅርብ ቀናት ውስጥ እንዲቀርብ አቅጣጫ ተሰጥቷል፡፡

በስብሰባው ማጠቃለያም አቶ ተፈራ ደርበው ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ ሆነው እንዲያገለግሉ ተመርጠዋል፡፡

በአዲስ መልክ የተደራጀው የስኳር ኮርፖሬሽን የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢና አባላት ዝርዝር

  1. ክቡር አቶ በየነ ገብረመስቀል………………ሰብሳቢ (አዲስ የተሾሙ)
  2. ክቡር አቶ ተፈራ ደርበው……………….. ም/ሰብሳቢ (በፊትም የነበሩ)
  3. ክቡር አቶ ካይዳኪ ገዛኸኝ……………….. አባል  (በፊትም የነበሩ)
  4. ፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው……………….. አባል  (በፊትም የነበሩ)
  5. አቶ ጋሼ የማነ…………………………… አባል  (በፊትም የነበሩ)
  6. ደ/ር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ…………………… አባል (አዲስ የተመደቡ)
  7. ወ/ሮ ትዕግስት አባተ……………………… አባል (አዲስ የተመደቡ)
  8. አቶ ብርሃኑ ጂጆ………………………….. አባል (አዲስ የተመደቡ)

Related posts

Leave a Comment