የስኳር ኢንደስትሪውን ወደ ለውጥ ምዕራፍ ማሸጋገር እንደሚቻል ተገለጸ

ዘንድሮ በዝግጅት ምዕራፍ የታየው የስኳር ፋብሪካዎች የክረምት ጥገና አፈጻጸም በታቀደው የምርት መጠን ከታገዘ ኢንደስትሪውን ወደ ለውጥ ምዕራፍ ማሸጋገር እንደሚቻል እምነታቸው መሆኑን የስኳር ኮርፖሬሽን የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ገለጹ፡፡

የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተርና የኮርፖሬሽኑ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ በየነ ገብረመስቀል ይህንን የተናገሩት በኮርፖሬሽኑ የአምስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ላይ ዛሬ ታህሳስ 1/2012 ዓ.ም. ተገኝተው በሰጡት የሥራ መመሪያ ነው፡፡

ፋብሪካዎች የክረምት ጥገና አጠናቀው በተያዘላቸው ጊዜ ወደ ምርት መግባታቸው በቀጣይ በዘርፉ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ትልቅ አቅም እንዳለ አመላካች ነው ብለዋል፡፡

የስኳር ኢንደስትሪው ዕድገትም ሆነ ወድቀት በተቋሙ አመራር እጅ ነው ያሉት አቶ በየነ የሥራ መሪዎች አርአያ በመሆን ሠራተኛውን በይቻላል መንፈስ ከመሩት የኢንደስትሪውን ለውጥ ማረጋገጥ የሚቻል መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

አክለውም ለሀገር ኢኮኖሚና ለሠራተኛው የሥራ ዋስትና መረጋገጥ ዘንድሮ የታቀደውን የምርት ግብ ማሳካት የግድ መሆኑን ከአደራ ጭምር አስታውቀዋል፡፡ ግቦችን ማሳካት ከተቻለም በዘመነ መንገድ ኢንደስትሪውን ቀድሞ ወደሚታወቅበት የሥራ ባህልና ውጤታማነት ለማሸጋገር ዕድል ይኖራል ነው ያሉት፡፡

የሸንኮራ አገዳ ምርታማነትን ከማሳደግ አኳያም ሀገሪቱ ለሸንኮራ አገዳ ልማት ያላትን ተስማሚ የተፈጥሮ ሀብት የበለጠ ለመጠቀም የመሬት ዝግጅት፣ የአገዳ እንክብካቤ፣ የውሃና የግብአት አጠቃቀምን ማሻሻል እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

በፕሮጀክቶች የታቀዱ የልማት ሥራዎች በጊዜ መፈጸም እንዳለባቸው ያስታወቁት አቶ በየነ፣ የስኳር ፋብሪካዎችና ፕሮጀክቶች ትክክለኛውን ገጽታቸውን የሚያሳይ የተጠቃለለ የፋይናንስና የኦዲት ሪፖርት ማቅረብ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

በማጠቃለያቸው ከኮርፖሬሽኑ አቅም በላይ የሆኑ ጉዳዮችን በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ እንዲሁም በኮርፖሬሽኑ የሥራ አመራር ቦርድ አማካይነት ለመፍታት እየሰሩ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

Related posts