የስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ የአዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕከት

በዓለም ገበያ ከፍተኛ ተፈላጊነት ካላቸው 10 የግብርና ምርቶች ወይም ሸቀጦች ውስጥ አንዱ ስኳር ነው፡፡ ለዚህ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ኢትዮጵያ ተስማሚ የሆነ እምቅ የተፈጥሮ ሃብትና ለሥራ ዝግጁ የሆነ የሰው ኃይል አላት፡፡ ለሸንኮራ አገዳ ካላት ምቹ የተፈጥሮ ፀጋ አኳያም በአገዳ ምርታማነት በአለምአቀፍ ደረጃ ከሚታወቁ ጥቂት ሀገራት ተርታ በግንባር ቀደምነት ተሰልፋለች፡፡

ይህንን ሃብት ከግምት ውስጥ ያስገባው የኢፌዲሪ መንግሥት የስኳር ኢንደስትሪ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ የመሪነት ሚና እንዲጫወት ለዘርፉ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ካፒታል በመመደብ መጠነ ሰፊ ሥራዎችን ማካሄድ ከጀመረ ዘጠኝ አመታት ተቆጥረዋል፡፡ ምንም እንኳ በዘርፉ ከተቀመጡ ግቦች አንጻር በእስካሁኑ የልማት ጥረት የተገኘው ውጤት የተጠበቀውን ያህል ባይሆንም የኢንዱስትሪውን ተስፋ ግን አሻግሮ የሚያሳይ ነው ለማለት ይቻላል፡፡

በዘርፉ የታቀዱ ግቦች በሚፈለገው ልክ እንዳይሳኩ ምክንያቶች ናቸው ተብለው ከተለዩት ተግዳሮቶች ውስጥ የአዳዲስ የስኳር ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ከመጀመሩ አስቀድሞ በቂ የአዋጪነት ጥናት አለመደረጉ፣ ልማቱ በሚካሄድባቸው አካባቢዎች ምንም አይነት የመሰረተ ልማት አውታሮች ሳይዘረጉ የፋብሪካ ግንባታዎች መጀመራቸው፣ የመፈጸምና የማስፈጸም አቅም ማነስ፣ የግብዓት አቅርቦት ችግር እንዲሁም የበጀትና የውጭ ምንዛሪ እጥረት በዋነኛነት ይጠቀሳሉ፡፡

ከዚህ አንጻር የአዳዲስ ስኳር ልማት ፕሮጀክቶች አፈፃፀም እንደተጠበቀው ውጤታማ ባለመሆኑ በከፍተኛ ደረጃ እያደገ የመጣውን የስኳር ፍላጐት በሀገር ውስጥ ምርት ለመሸፈን ሳይቻል ቀርቷል፡፡ ይህ ደግሞ አስቀድሞም በፍላጎትና በአቅርቦት መካከል የነበረውን ክፍተት ይበልጡኑ አስፍቶታል፡፡ በመሆኑም መንግሥት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በመመደብ ስኳር ከውጭ ማስገባቱን ቀጥሏል፡፡ ይሁንና ይህ አካሄድ ሀገሪቱ ካለባት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረት አኳያ ዘላቂ መፍትሔ እንዳልሆነ ሁላችንም የምንገነዘበው ጉዳይ ነው፡፡

ስለሆነም መንግሥት የሀገር ውስጥ የስኳር ፍላጎት ለማሟላት፣ የብድር ጫና ለመቀነስ፣ በዘርፉ የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማምጣትና የውጭ ምንዛሪ ለማስገኘት ተጨማሪ ኢንቨስትመንት የሚጠይቁ ስድስት ያህል ፋብሪካዎችና ፕሮጀክቶችን በ2012 ዓ.ም. በከፊል  ወይም  ሙሉ በሙሉ ወደ ግል ይዞታ ለማዘዋወር እየሰራ ይገኛል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ መንግሥት ላልተጠናቀቁ የስኳር ልማት ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያና ለውጭ ዕዳ መክፈያ የሚውል ብድር ፈቅዷል፡፡ በዚህ መሰረት የጣና በለስ ቁጥር አንድ ስኳር ፋብሪካ ቀሪ የግንባታ ስራ ለውጭ ኮንትራክተር ተሰጥቶ ሥራው እየተካሄደ ሲሆን፣ በተመሳሳይ የኦሞ ኩራዝ ቁጥር አንድ የስኳር ፋብሪካ ግንባታን በውጭ ኮንትራክተር ለማጠናቀቅ የሚያስችል እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን በዚህ ዓመት ተጨማሪ የመሬት ዝግጅት፣ የመስኖ መሠረተ ልማት ዝርጋት፣ የአገዳ ተከላና የቤቶች ግንባታ ሥራዎችን ለማካሄድ አቅደን እየሰራን እንገኛለን፡፡

የዘንድሮ በጀት ዓመት ዕቅዳችን ዋና ግብ የሸንኮራ አገዳና የፋብሪካ ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ሲሆን፣ በዚህም በሰባት ስኳር ፋብሪካዎች 4 ሚሊዮን 835 ሺህ 320 ኩንታል ስኳር እንዲሁም በመተሐራና ፊንጫኣ ስኳር ፋብሪካዎች 21 ሚሊዮን 417 ሺህ 140 ሊትር ኤታኖል ይመረታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በሌላ በኩል ኢንደስትሪውን ከውድቀት ለመታደግና ወደቀድሞ የሥራ ባህሉና ዝናው ለመመለስ በዚህ በጀት ዓመት ዘጠኝ አበይት ግቦችን ያካተተ የአሠራር ማሻሻያ/reform በተሟላ መልኩ ለመፈጸምና በሁሉም የሥራ ዘርፎች የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት ትግበራ ውስጥ ገብተናል፡፡

ከዚህ አኳያ አለአግባብ የሚወጡ ወጪዎችን በማስቀረት ገቢን ማሳደግ ላይ ትኩረት የምናደርግ ሲሆን፣ ለአፈጻጸሙም ዝግጅት አድርገናል፡፡ በቅርቡ ከዘጠኝ ዓመት በኋላ ማካሄድ የቻልነው የፕላንትና ፕሮሰስ ጉባኤም/Plant & Process Conference ሌላኛው ቀጣይ የግባችን አካል ተደርጎ የሚወሰድ ይሆናል፡፡

ከዚህ ባሻገር በምርምር ሥራዎች ስኳርን ወደ ቀድሞ ዝናው ለመመለስ ያለመና ለኢንደስትሪው ትራንስፎርሜሽን ወሳኝ የሆነ የ10 ዓመት የስኳር ምርምርና ልማት ፍኖተ-ካርታ አዘጋጅተን እየሰራን እንገኛለን፡፡ በተመሳሳይ ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ አኳያ የሸንኮራ አገዳ ልማት የአምስት ዓመት እንዲሁም የፋብሪካ ኦፕሬሽን የሦስት ዓመት ፍኖተ ካርታዎች ተዘጋጅተው ወደ ትግበራ ተገብቷል፡፡

ከአቅም ግንባታ አኳያም በኢንዱስትሪው በየደረጃው የሚታየውን የአመራርና የባለሙያ የክህሎት ክፍተት በአጫጭር ሥልጠናዎች እንዲሁም በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ ትምህርቶች ለመሙላትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማምጣት የሚያስችል አካሄድ መከተል ጀምረናል፡፡ በዚህ መሰረት በአምስት የእርሻና የፋብሪካ ኦፕሬሽን የትምህርት መስኮች ሥርዓተ ትምህርት ቀርጸን ከኦሮሚያ  የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ኤጀንሲ ከደረጃ 1 እስከ 4 የብቃት እውቅና ማረጋገጫ ፈቃድ አግኝተናል፡፡ ፈቃድ ባገኘንባቸው የትምህርት መስኮችም በኮርፖሬሽኑ የስኳር አካዳሚ ሥልጠና ለመስጠት የሚያስችል ቅድመ ዝግጅቶችን አጠናቀናል፡፡

በተጨማሪም በአምስት ዙር በሰባት የስኳር ኢንደስትሪ የትምህርት መስኮች የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት ለመስጠት የሚያስችል ሥርዓተ ትምህርት አዘጋጅተን ከአምስት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ባደረግነው ስምምነት መሰረት በመጀመሪያ ዙር ከ80 በላይ የሥራ መሪዎችና ከፍተኛ ባለሙያዎች ከ2011 ዓ.ም የክረምት ወራት ጀምሮ የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት እንዲያገኙ ዕድል ፈጥረናል፡፡ በተመሳሳይ ኮርፖሬሽኑ ባመቻቸው የሦስተኛ ዲግሪ የትምህርት ዕድል በ2011 ዓ.ም. ስድስት ተመራማሪዎች ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ይገኛሉ፡፡

ይህ የትምህርት መርሃ ግብር ቀጣይነት ያለው ሲሆን፣ በአምስት ዙሮች ከ600 እስከ 800 የሚሆኑ የዋናው መ/ቤት፣ የስኳር ፋብሪካዎችና ፕሮጀክቶች የሥራ መሪዎችን እና ቋሚ ሠራተኞችን በሁለተኛ ዲግሪ ለማስተማር ዕቅድ ተይዟል፡፡ ይህ ደግሞ ከዚህ ቀደም ባለሙያዎችን ከውጭ ሀገር ለማስመጣት ኮርፖሬሽኑ ያወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ የሚያስቀር ይሆናል፡፡

በአጠቃላይ ከታቀዱ ሥራዎች አንጻርና ዛሬ ላይ መላው የዘርፉ የሥራ መሪዎችና ሠራተኞች የተሻለ ለውጥ ለማምጣት በቁጭትና በአዲስ የሥራ መንፈስ ከመነሳሳታቸው አኳያ የስኳር ኢንደስትሪው ስኬት ሩቅ በማይባል ጊዜ ውስጥ እውን እንደሚሆን መገመት ይቻላል፡፡

በዚህ አጋጣሚ ለዋናው መ/ቤት፣ ለስኳር ፋብሪካዎችና ፕሮጀክቶች የሥራ መሪዎችና ሠራተኞች እንዲሁም ለባለድርሻ አካላት በአዲሱ ዓመት ያለምናቸውን ግቦች በጋራ እንድናሳካ ጥሪዬን እያስተላለፍኩ፤ ዘመኑ የሠላም፣ የሥራና የስኬት እንዲሆን እመኛለሁ፡፡

መልካም አዲስ ዓመት!

Related posts