የኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት ስኬታማ ጉዞ

  1. መግቢያ

የኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በደቡብ ኦሞ ዞን የሰላማጎና የኛንጋቶም ወረዳዎችን፣ በቤንች ማጂ ዞን የሱርማና የሚኤኒትሻሻ ወረዳዎችን እንዲሁም በከፋ ዞን የዴቻ ወረዳ አንዳንድ የተመረጡ ቦታዎችን ያካተተ ነው።

1.1 ለስኳር ልማቱ የተመረጠው አካባቢ ሁኔታ

በተከለሰው የስኳር ልማት ዘርፍ ዕቅድ መሰረት በቀን እያንዳንዳቸው 12,000 ቶን አገዳ መፍጨት የሚችሉ ሶስት ስኳር ፋብሪካዎችና በቀን 24,000 ቶን አገዳ መፍጨት የሚችል አንድ ስኳር ፋብሪካ እየተገነባበት የሚገኘው ይህ ፕሮጀክት ለአራቱም ፋብሪካዎች በግብዓትነት የሚውል የሸንኮራ አገዳ በ100,000 ሄክታር መሬት ላይ እየለማ ይገኛል፡፡

ፕሮጀክቱ የሚገኝበት አካባቢ ስፍራ ለኬንያ ድንበር ቅርብ ከመሆኑ የተነሳ ኢትዮጵያ ምርቱን ለውጭ አገር ገበያ ለማቅረብ የሚያስችላት ስትራተጂያዊ ቦታ ነው። ለፕሮጀክቱ የሸንኮራ አገዳ ልማት እንዲሆን የተመረጠው መሬት በአብዛኛው ለጥ ያለ ሜዳ በመሆኑ የአገዳ ልማቱን በመስኖ አማካይነት ለማከናወን እጅግ ተስማሚ  ነው።

1.2 ለስኳር ልማቱ የተመረጠው አካባቢ ሕዝብ ብዛት

በ2004 ዓ.ም. በተካሄደ የሕዝብ ቆጠራ መሰረት ፕሮጀክቱ በሚያካልላቸው ሶስቱም ዞኖች የሚኖረው የሕዝብ ብዛት 279,026 ገደማ ነው። በሌላ በኩል የፕሮጀክቱ ክልል  በሚያርፍባቸው አካባቢዎች የሚኖረው ሕዝብ ብዛት ከ53,596 በታች ነው።

1.3 ለስኳር ልማቱ በተመረጠው አካባቢ ያለው የሕዝብ አሰፋፈር ሁኔታ

ለስኳር ልማት ፕሮጀክቱ በተመረጠው አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎች የአሰፋፈር ሁኔታ እጅግ የተበታተነ ሲሆን፣ የተመረጡት ወረዳዎች የሕዝብ አሰፋፈርም 9.6 ሰዎች በአንድ ካሬ ሜትር ስኩዌር ሰፍረው የሚገኙበት ነው። የፕሮጀክቱ ሥራዎች በሚከናወኑባቸው አካባቢዎች  የሚኖረው ሕዝብ አሰፋፈር ሲታይም ከላይ በካሬ ሜትር ስኩዌር ከተጠቀሰው የአሰፋፈር ሁኔታ እጅግ የቀነሰ ሆኖ ይገኛል።

በመሆኑም ባለፉት ስድስት ዓመታት የስኳር ልማቱ በሚካሄድበት የሥራ ክልል (ኮማንድ ፖስት) ውስጥ ይኖር የነበረውን የአካባቢውን ማህበረሰብ በመንደር በማሰባሰብ የማህበራዊና የመሰረተ ልማት አገልግሎቶች እና በመስኖ የለማ የእርሻ መሬት ተጠቃሚ እንዲሆን የተደረገው ጥረት ተስፋ ሰጪ ነው፡፡

1.4 የአካባቢው ተወላጆች ኑሯአቸውን ለመምራት የሚያከናውኗቸው ተግባራት

በፕሮጀክቱ የሥራ ክልል ውስጥና በአካባቢው የሚኖሩ አብዛኛዎቹ ተወላጆች አርብቶ አደሮች ሲሆኑ፣ ኑሮአቸውን የሚገፉት ለከብቶቻቸው የግጦሽ መሬትና ውኃ ፍለጋ ከቦታ ቦታ በመዘዋወር ነው። ከዚህ ባሻገር ቁጥራቸው አነስተኛ የሆነና በእርሻ ስራ የሚተዳደሩ ተወላጆች ደግሞ በአካባቢው በሚከሰት ያልተጠበቀ ዝናብ ሳቢያ በተደጋጋሚ ለምግብ እህል እጥረት ይጋለጡ ነበር፡፡

የኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት  ከመጀመሩ በፊት በጣም በጥቂት አካባቢዎችና ወንዞችን ተከትሎ ከሚካሄድ የሰብል ልማት በስተቀር ፕሮጀክቱ በሚገኝባቸው አብዛኛዎቹ ወረዳዎች ይህ ነው የሚባል ምርት አይመረትም ነበር። በመሆኑም የፕሮጀክቱ ሥራ በተጀመረበት ወቅት በእርሻ ሥራ ተሰማርተው ይኖሩ የነበሩ የአካባቢው ተወላጆች ቁጥር ግምት ውስጥ የሚገባ አልነበረም።

የአካባቢው ተወላጆች ዋንኛ ምግብ ከገበያ የሚገኙ ሰብሎችና የእንስሳት ተዋጽኦዎች (ወተት፣ ስጋና የመሳሰሉት) ብቻ የነበሩ ሲሆን፣ ዛሬ ላይ ግን ይህ ታሪክ ተለውጦ በራሳቸው ማሳ ላይ በቆሎ አምርተው ለመጠቀም ችለዋል፡፡ ይህ የሆነውም በፕሮጀክቱ አማካኝነት በርካታ የአካባቢው ተወላጆች በመስኖ የሚለማ መሬት እንዲያገኙ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ኤክስቴንሽን አገልግሎት ድጋፍ ጭምር እየተደረገላቸው ከእርሻ ሥራ ጋር በመተዋወቃቸው ምክንያት ነው፡፡ በዚህም ብቻ ሳያበቁ የሸንኮራ አገዳ አብቅለው በአሁኑ ወቅት ስኳር ማምረት ለጀመሩት ለኦሞ ኩራዝ ቁጥር 1 እና 2 ስኳር ፋብሪካዎች የሚያቀርቡበት ምእራፍ ላይ ደርሰዋል፡፡

1.5 በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ በፕሮጀክቱ ዙሪያ የሚገኙ አካባቢዎች ሁኔታ

የኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት መካሄድ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ በአካባቢው በብሔራዊም ሆነ በዓለምአቀፍ ደረጃ በቅርስነት ተመዝግበው የሚገኙ ተፈጥሯዊ፣ ባህላዊና  ሃይማኖታዊ ቦታዎች በተገቢው ሁኔታ በእንክብካቤ ተይዘው ይገኛሉ። በዚህም በአገር ውስጥም ሆነ በዓለምአቀፍ ደረጃ ተመዝግቦ በፕሮጀክቱ ሥራዎች ምክንያት ለችግር የተጋለጠ ምንም ዓይነት ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊም ሆነ የቅሪተአካል ጥናት ቦታ የለም።

1.6 ለስኳር ልማቱ የሚውለው የኦሞ ወንዝና የቱርካና ሐይቅ ሁኔታ

ኤስ.ጂ.አይ. ስቱዲዮ ጋሊ ኢንጂጂነሪያ (SGI Studio Galli Ingegneria) የተባለ የኢጣሊያ ኩባንያ በኦሞ ወንዝ ላይ ለ20 ዓመታት ባደረገው ጥናት እንዳረጋገጠው የኦሞ ወንዝ በአንድ ሴኮንድ የሚለቀው የውኃ መጠን 5 ሺህ ሜትር ኩብ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ለኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት የሸንኮራ አገዳ ልማት የሚያስፈልገው የውኃ መጠን የኦሞ ወንዝ በአንድ ሴኮንድ ከሚለቀው የውኃ መጠን 4 በመቶ ያህል ብቻ ሲሆን፣ ከዚሁ ውስጥም 30 በመቶ ያህሉ ለልማቱ ውሎ ተመልሶ ወደ ኦሞ ወንዝ የሚቀላቀል ነው። በመሆኑም ፕሮጀክቱ የኦሞን ወንዝ በመጠቀሙ በቱርካና ሐይቅ ላይ የሚያስከትለው ተጽዕኖ ግምት ውስጥ የሚገባ አይደለም።

  1. የስኳር ልማት ዘርፍ በሁለቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ወቅቶች

2.1 ዘርፉ በአንደኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ወቅት

በአገር አቀፍ ደረጃ የስኳር ልማት ዘርፍን በተመለከተ የተካሄደ ጥናት እንዳረጋገጠው ኢትዮጵያ ከ500 ሺህ ሄክታር በላይ ለሸንኮራ አገዳ ልማት ተስማሚ የሆነ መሬት አላት። አገሪቱ በተትረፈረፈ የውኃ ሀብት፣ ለዘርፉ ተስማሚ በሆነ የአየር ንብረት፣ ድንግልና በመስኖ ሊለማ በሚችል መሬት የታደለች መሆኗም ይህን ሰፊ እምቅ ሀብቷን ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀም የሚያስችላትን ስትራተጂያዊ እቅድ እንድትነድፍ ግድ ብሏታል። በዚህም መሰረት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መንግሥት የነደፈው የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አገሪቷ ለዘርፉ ያላትን እምቅ ሀብት ያገናዘበ ነበር።

የስኳር ልማት ዘርፍ ወደፊት የአገሪቷን ኢኮኖሚ በእጅጉ በማሳደግ መካከለኛ ገቢ ካለቸው አገሮች ተርታ ሊያሰልፉን ይችላሉ ተብለው ከታመነባቸው ቁልፍ የልማት አጀንዳዎች ውስጥ ዋነኛው ነው። ይህ በመሆኑም በዕቅድ ዘመኑ 10 አዳዲስ ስኳር ፋብሪካዎችን በመገንባትና ነባሮቹን የወንጂ ሸዋና የፊንጫአ ስኳር ፋብሪካዎች ማስፋፊያዎችን በማጠናቀቅ የሀገር ውስጥ የስኳር ፍላጎትን ከማሟላት ባለፈ ምርቱን ለዓለም ገበያ በማቅረብ የውጪ ምንዛሬ ለማስገኘት ግብ ተጥሎ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይና የሰለጠነ የሰው ኃይልን የሚጠይቁ ሰፋፊና ግዙፍ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡

ከዚህ አኳያ ዘርፉ አገሪቱ ከድህነት ለመውጣት ከምታደርገው መጠነ ሰፊ የልማት ጥረቶች ሊነጠል የማይችል እንደ መሆኑ መጠን ከጅምሩ የመንግሥትን ቁርጠኝነት አግኝቷል፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ ስኳር ኮርፖሬሽን ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ በኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት ሦስት በቀን 12 ሺህ ቶን አገዳ እንዲሁም አንድ በቀን 24 ሺህ ቶን አገዳ የመፍጨት አቅም ያላቸው አራት ስኳር ፋብሪካዎችን በመገንባት ላይ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 2 ስኳር ፋብሪካ ከመጋቢት 2009 ዓ.ም. አንስቶ ማምረት ጀምሯል፡፡ የቁጥር 1 ስኳር ፋብሪካም ሰኔ ወር መጨረሻ ላይ የሙከራ ምርት አካሂዷል ፡፡

በተጨማሪም በመጀመሪያው የዕቅድ ዘመን በዘርፉ በተደረገው ርብርብ በ2007 ዓ.ም.   ከአዳዲሶቹ ፋብሪካዎች የተንዳሆ፣ የከሰምና የአርጆ ዲዴሳ ስኳር ፋብሪካዎችን ወደ ሥራ ማስገባት ተችሏል፡፡

የፋብሪካ ማስፋፊያ ፕሮጀክቶችን በተመለከተም በዕቅድ ዘመኑ በአገሪቷ የስኳር ኢንዱስትሪ ታሪክ ፋና ወጊ የነበሩትንና ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ዕድሜ ያስቆጠሩትን የወንጂ እና የሸዋ ስኳር ፋብሪካዎች በቀን 6 ሺህ  250 ቶን አገዳ የመፍጨት አቅም ባለው ዘመናዊ ፋብሪካ መተካት ተችሏል፡፡ በእርጅና ምክንያት ሥራቸውን ያቆሙት (ወንጂ በ2004 ዓ.ም.፤ ሸዋ በ2005 ዓ.ም.) ሁለቱ አንጋፋ ስኳር ፋብሪካዎች በአንድ ላይ በቀን የነበራቸው አገዳ የመፍጨት አቅም 3 ሺህቶን ብቻ ነበር።

በተመሳሳይ በፊንጫአ ስኳር ፋብሪካ በተከናወነ የማስፋፊያ ሥራ የፋብሪካውን በቀን አገዳ የመፍጨት አቅም ከ5 ሺህ ወደ 12 ሺህ ቶን ለማሳደግ ተችሏል፡፡

በሌላ በኩል በእርሻው ዘርፍ በተካሄደው የማስፋፊያ ፕሮጀክት በመጀመሪያው የዕቅድ ዘመን 65 ሺህ 363 ሄክታር መሬት በአገዳ ለምቷል፡፡ ይህም በእቅዱ መነሻ (2003 ዓ.ም.) ከነበረው 30 ሺህ 397 ሄክታር ጋር ሲነጻጸር የ215 በመቶ እድገት አሳይቷል፡፡

በአጠቃላይ በፋብሪካና በእርሻ ማስፋፊያ ሥራዎች አማካኝነት ዓመታዊ የስኳር ምርት መጠንን በ2002 ዓ.ም. መጨረሻ ከነበረበት 2 ሚሊዮን 903 ሺ 740 ኩንታል በመጀመሪው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን መጨረሻ (2007 ዓ.ም) ወደ 4 ሚሊዮን ኩንታል ለማሳደግ ተችሏል፡፡

2.2 ዘርፉ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ወቅት

አገሪቱ በስኳር ልማት ዘርፍ ስታከናውናቸው የነበሩ ተግባራት በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽ የእቅድ ወቅት ሁለተኛ ዓመት ላይ ያለበት ደረጃ ሲታይ ዘርፉ የሚጠበቅበትን ውጤት እንደሚያመጣ እምነት የሚጣልበት ሆኖ ተገኝቷል።

በሥራ ሂደት የተገኙ ተሞክሮዎችን በመውሰድ ከመጀመሪያው ዕቅድ ዘመን ጀምሮ እስከ 2009 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ የአራት ስኳር ፋብሪካዎችን ግንባታ በማጠናቀቅ ወደ ሥራ ማስገባት  የተቻለ ሲሆን አንድ ፋብሪካም በሙከራ ላይ ይገኛል፡፡

በተጨማሪም በኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት በመገንባት ላይ ከሚገኙት ሌሎች ሶስት ስኳር ፋብሪካዎች ውስጥ የኦሞ ኩራዝ ቁጥር አንድ እና ሶስት ፋብሪካዎች በ2010 ዓ.ም. ወደ መደበኛ የማምረት ስራ የሚገቡ ሲሆን፣ ግንባታቸው እየተከናወነ የሚገኙት የጣና በለስ አንድ እና ሁለት፣ የኦሞ ኩራዝ አምስት እና የወልቃይት ስኳር ፋብረካዎች ደግሞ እስከ 2012 ዓ.ም. ድረስ ግንባታቸው ተጠናቆ ወደ ምርት ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ከመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽ እቅድ ወቅት ጀምሮ እስከ 2009 ዓ.ም. ድረስ  ሲከናወን ከነበረው የፋብሪካ ግንባታ ጎን ለጎንም በዋነኛነት ለሸንኮራ አገዳ እርሻ መስኖ መሰረተ ልማት የሚውሉ ሶስት የግድብ ግንባታዎች (ተንዳሆ፣ ከሰምና ኦሞ ወንዝ ላይ የተገነባው ጊዜያዊ ግድብ) የተጠናቀቁ ሲሆን፣ የሁለት ግድቦች /የወልቃይትና የአርጆ ዲዴሳ/ ግንባታም በመካሄድ ላይ ይገኛል። ከዚህ ባሻገር እስካሁን በ10 ሺዎች የሚቆጠር ሄክታር መሬት ማልማት ያስቻለ  የዋና፣ መካከለኛና ሶስተኛ ደረጃ የመስኖ አውታር ግንባታ ስራ በሁሉም ስኳር ልማት ፕሮጀክቶች የተከናወነ ሲሆን፣ የእነዚህን ፋብሪካዎችና ፕሮጀክቶች የሰው ኃይል እስከ ቤተሰቦቻቸው የሚያስተናግዱ 3ሺህ 363 የመኖሪያና 85  አገልግሎት ሰጪ ቤቶች ተገንብተዋል።

እነዚህን በዘርፉ የተገኙ ስኬቶችን በማጤንም በአሁኑ ወቅት በርካታ ዓለምአቀፍ ተቋማት በዘርፉ በጋራ ለማልማት (በሽርክና) እና በቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ለመሳተፍ ፍላጎት ከማሳየት ባሻገር አንዳንዶች ከስኳር ኮርፖሬሽን ጋር በጋራ ለማልማት የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንድ የውጭ አገር ኩባንያ በወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ የኤታኖል ፋብሪካ ለመገንባት ከኮርፖሬሽኑ  ጋር በጋራ የማልማት ስምምነት ላይ ደርሶ ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጅት እያደረገ ይገኛል፡፡

  1. የኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት ስኬታማ ጉዞ

 3.1 ማሕበራዊ ኃላፊነትን ለመወጣት የተደረጉ ጥረቶች

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መንግሥት ከስድስት ዓመታት በፊት የኦሞ ኩራዝንም ሆነ ሌሎች የስኳር ልማት ፕሮጀክቶች ሥራ በይፋ ሲጀምር በሁሉም ፕሮጀክቶች አካባቢዎች ለሚኖሩ ዜጎች ተጠቃሚነት የቅድሚያ ትኩረት በመስጠት ነው።

በመሆኑም ፕሮጀክቱ ከመጀመሩ አስቀድሞ መንግሥት ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ተከታታይ ውይይት በማድረግና የነዋሪዎቹን ይሁንታ በማግኘት ነው ወደ ልማቱ የተገባው። በዚህ ፕሮጀክት ክልል ውስጥ እንዲሁም በአካባቢው ከሚኖሩ ተወላጆች እጅግ አብዛኛዎቹ አርብቶ አደር ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ለከብቶቻቸው ውኃና የግጦሽ መሬት ፍለጋ ከቦታ ቦታ የሚዘዋወሩ በመሆናቸው በፕሮጀክቱ ሳቢያ ነዋሪዎቹን ከቀየ የሚያፈናቅል ምንም ዓይነት መልሶ የማስፈር ሥራ አልተከናወነም። ይልቁንም በዚህ ፕሮጀክት የተከናወነው አርብቶ አደሩን  በመንደር የማሰባሰብ ሥራ ነው ።

በፕሮጀክቱ ክልል ውስጥም ሆነ በአካባቢው የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች እንደ ትምህርት ቤት፣ የሰውም ሆነ የከብት የጤና አገልግሎት፣ የእህል ወፍጮ፣ የንጹሕ መጠጥ ውኃ፣የመንገድ፣ በመስኖ የሚለማ መሬትና የመሳሰሉት አገልግሎቶች ማግኘት የጀመሩት የኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት በአካባቢው ሥራ መጀመሩን ተከትሎ ነው። ለአብነትም ፕሮጀክቱ በተጀመረበት በ2004 ዓ.ም. በደቡብ ኦሞ ዞን ሰላማጎ ወረዳ መንደር 2 የተከፈተው አልጎቢያ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በአሁኑ ወቅት 167 የቦዲ ብሔረሰብ ተወላጅ የሆኑ ተማሪዎች እየተማሩበት ሲሆን፣ የመጀመሪዎቹ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ዘንድሮ የ4ኛ ክፍል ትምህርታቸውን አጠናቀዋል፡፡ ሌሎች የተገነቡ ልዩ ልዩ የማኅበራዊና የመሰረተ ልማት ተቋማትም የእነዚህን ተማሪዎችም ሆነ የአካባቢውን ነዋሪዎች የዕለት ተዕለት ሕይወት ይበልጥ ቀላል እንዲሆን አድርገዋል።

ለአብነትም ስኳር ኮርፖሬሽን አርብቶ አደር የሆኑ የፕሮጀክቱ አካባቢ ተወላጆችን ከእርሻ ሥራ ጋር እንዲተዋወቁ ሥልጠና በመስጠትና በመስኖ የሚለማ መሬት በማመቻቸት በአሁኑ ወቅት የፈለጉትን ሰብል አብቅለው መጠቀም እንዲችሉ ማድረጉን መጥቀስ ይቻላል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን  የአካባቢው ተወላጆች  ሸንኮራ አገዳ አብቅለው ለፋብሪካ ለማቅረብ ልምድ እንዲያገኙና ስለ ዘርፉ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማድረግ ኮርፖሬሽኑ በወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ ተደጋጋሚ የተሞክሮ ጉብኝት በማመቻቸቱ በአካባቢው ተወላጆች ዘንድ የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት ተችሏል፡፡ ይህም በአካባቢያቸው በመገንባት ላይ የሚገኙ ስኳር ፋብሪካዎች ግንባታቸው ተጠናቆ ስኳር ማምረት ሲጀምሩ ለማየት በጉጉት እንዲጠባበቁ አድርጓቸው ቆይቷል።

በአሁኑ ወቅት የፕሮጀክቱ አካባቢ ተወላጆች በሸንኮራ አገዳ አብቃይ ማኅበራት ተደራጅተው ሸንኮራ አገዳ እያለሙ ሲሆን፣ ምርታቸውን ለኦሞ ኩራዝ ቁጥር 2 ስኳር ፋብሪካ ለማቅረብ እየተጠባበቁ ይገኛሉ፡፡ በቀጣይም በፕሮጀክቱ ስር ለሚገኙ ሌሎች ስኳር ፋብሪካዎች አገዳ አልምተው ማቅረብ እንዲችሉ በማኅበራት የማደራጀቱ ሥራ ቀጥሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት የአካባቢው ተወላጆች 1 ሺህ 67 አባላት ባሏቸው ሶስት የሸንኮራ አገዳ አብቃይ ማኅበራት ተደራጅተው በ864.75 ሄክታር መሬት ላይ አገዳ በማልማት ላይ ይገኛሉ።

በሌላ በኩል የፕሮጀክቱና የአካባቢው ተወላጆች በትራክተርና በማሽን ኦፕሬተርነት እንዲሁም ከስኳር ልማት ዘርፉ ጋር ተያያዥ በሆኑ ሌሎች የቴክኒክ ክህሎቶች ሰልጥነው የሥራ ዕድል እንዲያገኙ በማድረግም ኮርፖሬሽኑ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት ላይ ይገኛል። በመሆኑም በፕሮጀክቱ የተፈጠሩ ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ሰፊ የሥራ ዕድሎች የአካባቢው ተወላጆችን በእጅጉ ተጠቃሚ አድርጓቸዋል። በዚህም እስከ ሰኔ 2009 ዓ.ም. በፕሮጀክቱ አማካይነት በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ተደራጅተው የሥራ ዕድል ያገኙት 50ሺህ 692 የህል ዜጎች ሲሆኑ በፕሮጀክቱ የቋሚ፣ ጌዜያዊና የኮንትራት የሥራ ዕድል ያገኑት ደግሞ 81ሺህ 661 ናቸው፡፡

የኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት በአካባቢው መካሄዱ በተለይ ለደቡብ ኦሞ ዞን ዋና ከተማ ጂንካ ዘርፈ ብዙ የልማት እንቅስቃሴዎች እንዲካሄዱባት ያስቻለ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል ለበርካታ የአካባቢው ተወላጆች ሰፊ የስራ ዕድል የፈጠረውና በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የተገነባው የከረጢት ፋብሪካ እና በከተማዋ የተከፈተው የቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ተጠቃሾች ናቸው።

ለስኳር ልማት ዘርፍ ቁልፍ የሆኑ እንደ መንገድ የመሳሰሉ የመሰረተ ልማት አውታር ግንባታዎች መከናወናቸው ለአካባቢው ተወላጆች የፈጠሩት የገበያ ትስስርና ተወላጆቹ እንደ ማር፣ የእንስሳት ሀብትና ሌሎች ምርቶቻቸውን በተሻለ የገበያ ዋጋ እንዲሸጡ ማስቻሉ ሌላው በፕሮጀክቱ ምክንያት ያገኙት ትሩፋት ነው።

ከዚህ ባሻገር ፕሮጀክቱ ዘርፈ ብዙ ልማቶችን ለደቡብ ኦሞ ዞን መስተዳድር አምጥቷል። ይህ በመሆኑም በርካታ ሆቴሎች፣ አገልግሎት መስጫ ተቋማት፣ የቴክኒክና ሙያ ት/ቤት እና እንደ ከረጢት ፋብሪካ የመሳሰሉ ተቋማት በጂንካ ከተማ እንዲገነቡ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ እንዲሁም በከተማዋ በግንባታ ላይ የሚገኙት የአውሮፕላን ማረፊያ እና የሪፈራል ሆስፒታል  የኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት ፍሬዎች ናቸው፡፡

 3.2.  የዘርፉን ዕቅድ ለማሳካት የተከናወኑ ተግባራት

  1. የመሰረተ ልማት ግንባታ

ፕሮጀክቱ ከአካባቢው ከተሞች እጅግ ርቆ የሚገኝ በመሆኑ መንገድ፣ ስልክ፣  ኤሌክትሪክ፣ የኢንተርኔትና የመሳሰሉት የመሰረተ ልማት አውታሮች ሳይገነቡ የፕሮጀክቱን ሥራ ማከናወን ከቶ የሚታሰብ አይደለም። በመሆኑም በዘርፉ የተቀመጡ ዕቅዶችን ለማሳካት የመሰረተ ልማት አውታሮችን የመገንባቱ ሥራ ኮርፖሬሽኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን እንዲከናወኑ ካደረጋቸው አበይት ተግባራት ውስጥ አንዱ ነው።

  1. የግድብና የውኃ መጥለፊያ ስትራክቸሮች ግንባታ

በኦሞ ወንዝ ላይ ጊዚያዊ ውኃ መገደቢያ ኮፈርዳም ከተገነባ በኋላ በግንባታ ላይ የሚገኘው የዊር ስትራክቸር የፕሮጀክቱን 100 ሺህ ሄክታር የሸንኮራ አገዳ መሬት እንዲያለማ ለማድረግ ስኳር ኮርፖሬሽን ከኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ጋር በመተባበር እያከናወነ የሚገኘው ወሳኝ ሥራም በዋነኛነት ይጠቀሳል፡፡ በተጨማሪም ከኦሞ ገባር ወንዞች መካከል አንዱ በሆነው የሻርማ ወንዝ ላይ ተገንብቶ የተጠናቀቀው አነስተኛ ግድብ፣ ውኃ መውሰጃ ስትራክቸርና ቦይ ግንባታ 10 ሺህ ሄክታር የፕሮጀክቱን የሸንኮራ አገዳ መሬት ለማልማት የሚያገልግል በኮርፖሬሽኑና በኦሞ ኩራዝ ቁጥር ሶስት ስኳር ፋብሪካ የውስጥ አቅም የተከናወነ ሌላው ዋነኛ ተግባር ነው።

  1. የዋና ቦይ ግንባታ

ረጅም ኪሎ ሜትሮችን የሚያቋርጡ የዋና፣ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ የውኃ መውሰጃ ቦዮች ግንባታም የፕሮጀክቱን የአገዳ መሬት ለማልማት የተከናወነ ተግባር ነው። እስከ 2009 ዓ.ም. መገባደጃ ድረስም 25 ሺህ ሄክታር ሸንኮራ አገዳ መሬት ማልማት የሚስችል የመስኖ አውታር ግንባታ ተከናውኗል፡፡

  1. የመኖሪያና የአገልግሎት መስጫ ቤቶች ግንባታ

በፕሮጀክቱ ተቀጥረው እየሰሩ ለሚገኙ በሺዎች ለሚቆጠሩ ሠራተኞችና ቤተሰቦቻቸው መኖሪያና አገልግሎት መስጫ የሚሆኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ግንባታ ሌላውና ኮርፖሬሽኑ በዘርፉ ያስቀመጠውን ግብ ለማሳካት ያከናወነው አብይ ሥራ ነው። እስከ ሰኔ 2009 ዓ.ም. ድረስ 1ሺህ 16  ያህል የመኖሪያና 11 ያህል መኖሪያ ያልሆኑ ቤቶች ግንባታ  ተከናውኗል።

5.የሸንኮራ አገዳ ተከላ ስራ

እስከ ሰኔ 2009 ዓ.ም. ድረስ 14 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሸንኮራ አገዳ የለማ ሲሆን፣ በቀጣይ እየተካሄደ ያለው የአገዳ ተከላ ሥራም ከፋብሪካዎች ግንባታ ደረጃ ጋር እየተናበበ እንዲከናወን በመደረግ ላይ ነው።

  1. የስኳር ፋብሪካ ግንባታ ስራ

 6.1 የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 2 ስኳር ፋብሪካ

በኦሞ ኩራዝ በመገንባት ላይ ከሚገኙት አራት ስኳር ፋብሪካዎች መካከል አንዱ የሆነውና በቀን 12 ሺህ ቶን አገዳ የመፍጨት አቅም እንዲኖረው ተደርጎ ኮምፕላንት ተብሎ በሚጠራ የቻይና ኩባንያ የተገነባው የኦሞ ኩራዝ ቁጥር ሁለት ስኳር ፋብሪካ ከመጋቢት ወር 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ስኳር ማምረት ጀምሯል። ይህም ኮርፖሬሽኑ በስኳር ልማት ዘርፍ እስካሁን ካገኛቸው ወሳኝ ስኬቶች ውስጥ የሚደመር ነው፡፡

6.2 የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 1 ስኳር ፋብሪካ

በቀን 12 ሺህ ቶን አገዳ የመፍጨት አቅም እንዲኖረው ተደርጎ በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን እየተገነባ የሚገኘው የኦሞ ኩራዝ ቁጥር አንድ ስኳር ፋብሪካ በሰኔ ወር 2009 ዓ.ም. መጨረሻ የሙከራ ምርት አምርቷል፡፡ ቀሪ ሥራዎቹ ተጠናቀው በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር በቀን 12 ሺህ ቶን አገዳ የመፍጨት አቅም ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

6.3 የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 ስኳር ፋብሪካ

በቻይናው ኮምፕላንት ኩባንያ እየተገነባ የሚገኘውና በቀን 12 ሺህ ቶን አገዳ የመፍጨት አቅም ያለው የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 ፋብሪካ በሰኔ 2009 ዓ.ም. ባለው የግንባታ አፈጻጸም መሰረት 80 በመቶ ላይ የደረሰ ሲሆን፣ በ2010 ዓ.ም. ስኳር ማምረት ይጀምራል፡፡

6.4 የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 5 ስኳር ፋብሪካ

የፋብሪካ ግንባታ ሥራው በ2009 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ የተጀመረውና አገዳ በመፍጨት አቅሙ ከላይ ከተጠቀሱት ሦስት ፋብሪካዎች ከፍተኛ የሆነው የኦሞ ኩራዝ 5 ስኳር ፋብሪካ በቀን 24 ሺህ ቶን አገዳ መፍጨት የሚያስችል ዲዛይን ያለው ሲሆን፣ የፋብሪካውን ግንባታ እያከናወነ የሚገኘው ጄ.ጄ.አይ.ኢ.ሲ. /JJIEC/ የተባለ የቻይና ኩባንያ ነው።

  1. የዘርፉ የወደፊት አቅጣጫ

ስኳር ኮርፖሬሽን ከአገር በቀልና የውጭ ተቋማት ጋር ዘርፉን በጋራ ለማልማት (በሽርክና) እንዲሁም ባለሃብቶች/ኩባንያዎች በዘርፉ በቀጥታ ኢንቨስትመንት መልክ እንዲሳተፉ ለማድረግ በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል፡፡  በዚህ መሰረት ከበርካታ የሀገር ውስጥና የውጪ ተቋማት ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሞ ቀጣይ ሥራዎችን እያከናወነ ነው፡፡ በተመሳሳይ ሌሎችም በዘርፉ ለመሳተፍ ፍላጎት እያሳዩ ናቸው።

በዚህ ረገድ የጀርመኑ ኩባንያ ኡገን ሸሚት /Eugen Schmitt Company/ ከስኳር ኮርፖሬሽን ጋር በሽርክና በወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ የኤታኖል ፋብሪካ ለመገንባት ተስማምቶ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡

ከዚህ አኳያ አገሪቷ በሸንኮራ አገዳ ልማት፣ በስኳር ምርት እንዲሁም የስኳር ተረፈ ምርቶችንና ተጓዳኝ ምርቶችን በግብዓትነት በመጠቀም በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ በሽርክና ወይም በቀጥታ ኢንቨስትመንት መስራት የሚፈልጉ አገር በቀልና የውጭ ተቋማትን ለመቀበልና ለማስተናገድ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ ናት።

በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት በተለይም ምንም ዓይነት የመሰረተ ልማት አውታር ባልነበረበት ሁኔታ በኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት የተጀመረው ጉዞ አንጸባራቂ ውጤቶችን እያስመዘገበ ቀጥሏል።

ልማቱ እየተካሄደበት ያለው የዚህ ፕሮጀክት ክልል ከከተሞች እጅግ ርቆ ተደራሽ በማይሆንበት ቦታ ይገኝ የነበረ በመሆኑም የፕሮጀክቱ ሥራ ውጣ ውረድ የበዛበት እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ይሁንና በመንግሥትና በአካባቢው ማህበረሰብ ያላሰለሰ ጥረት ፕሮጀክቱ ዛሬ ላይ ጣፋጭ ፍሬ ማፍራት ጀምሯል፤ በቀጣይም ፍሬው ይበልጥ ይጎመራል፡፡ በዚህም የኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት የስኬት ጉዞ ይቀጥላል!

Related posts

Leave a Comment