የኮርኖ ቫይረስ ሥርጭትን የሚከላከልና የሚቆጣጠር ስትሪንግ ኮሚቴ ሥራ ጀመረ

በስኳር ኮርፖሬሽን ዋና መ/ቤት፣ በስኳር ፋብሪካዎችና ፕሮጀክቶች የኮሮና ቫይረስ [COVID-19] ሥርጭትን የሚከላከልና የሚቆጣጠር ስትሪንግ ኮሚቴ ከመጋቢት 8/2012 ዓ.ም አንስቶ ሥራ ጀመረ፡፡

በኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የበላይ ጠባቂነት እና በኮርፖሬት ሰርቪስ ዘርፍ ም/ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰብሳቢነት የሚመራው ይህ ኮሚቴ ከፋብሪካ ኦፕሬሽን፣ ከእርሻ ኦፕሬሽንና ከፋይናንስ ዘርፎች ም/ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች እንዲሁም ከዋና ሥራ አስፈጻሚ አማካሪ፣ ከኮሚዩኒኬሽንና ከጤና አገልግሎት ኃላፊዎች በተውጣጡ ስድስት አባላትና ጸኃፊ የተዋቀረ ነው፡፡

ኮሚቴው የተሰጠውን ተልዕኮ ለመፈጸም ዝርዝር ተግባርና ኃላፊነት እንዲሁም የድርጊት መርሃ ግብር አዘጋጅቶ ወደ ሥራ ከመግባቱ ባሻገር የመረጃ ልውውጥን ለማሳለጥ፣ ግንዛቤን ለመፍጠር፣ ቁሳቁሶችን በሚፈለገው ደረጃ ለማቅረብ እንዲሁም የክትትልና ቁጥጥር ሥራዎችን በተደራጀ መልክ ለማከናወን ከተለያዩ የሥራ ክፍሎች የተውጣጡ ሰብሳቢና ስድስት አባላት ያሉት የቴክኒክ ኮሚቴም አዋቅሯል፡፡

በተመሳሳይ በስኳር ፋብሪካዎችና ፕሮጀክቶች በዋና ሥራ አስኪያጆች የሚመራ አብይ ኮሚቴና ሥራውን ወደ ታች የሚያወርድ የቴክኒክ ኮሚቴ አቋቁሞ ወደ ሥራ ለመግባት የሚያስችል እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ በዚህ ሂደት በቀጣይ ሁለት ቀናት ውስጥ ኮሚቴዎቹ ተቋቁመው ወደ ሥራ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በስኳር ፋብሪካዎችና ፕሮጀክቶች የኮሮና ቫይረስ (COVID19) በሽታ ምልክቶችን የሚያሳዩ ሰዎች ሲያጋጥሙ በለይቶ ማቆያ ጣቢያ/ማዕከል ውስጥ ለማቆየትና ህክምና ለመስጠት የሚያስችል ሥራ ከወዲሁ ለማስጀመር ከሚመለከታቸው መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ጋር በጋራ መስራት እንደሚገባ የኮርፖሬት ስትሪንግ ኮሚቴ አስታውቋል፡፡

በዋና መ/ቤት ደረጃ ስትሪንግ ኮሚቴ ከመቋቋሙ ቀደም ብሎ በኮርፖሬት ሰርቪስ ዘርፍ አማካይነት የቫይረሱ ሥርጭትን ለመግታት የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል፡፡

በዚህም ተግባር ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና ከጤና ተቋማት ጋር ግንኙነት በማድረግ ቁሳቁሶችን ለማሰባሰብ፤ ከቫይረሱ ጋር የተያያዙ አለማቀፋዊና ሀገራዊ ወቅታዊ መረጃዎችና የጥንቃቄ መልእክቶችን በየጊዜው ለሠራተኛው ለማስተላለፍ፤ በኮርፖሬሽኑ ዋና መ/ቤት ህንጻ መግቢያ በር ላይ ለሠራተኞችና ለደንበኞች ሳሙናና አልኮል ያካተተ የእጅ መታጠቢያ ቦታ ለማዘጋጀት እና ለዘርፎች የእጅ መታጠቢያ ሳሙናና አልኮል ለማመቻቸት ተችሏል፡፡

Related posts