የኮርፖሬሽኑ ሕግና ኢንሸራንስ ጉዳዮች አለአግባብ በሥር ፍ/ቤት የተወሰነ የ18 ሚሊዮን ብር ክፍያን አስሻረ

የኮርፖሬሽኑ ሕግና ኢንሸራንስ ጉዳዮች የሥራ ክፍል ስኳር ኮርፖሬሽን በአዳማ ከተማ ተከራይቶት የነበረን መጋዘን  አስመልክቶ አለአግባብ በሥር ፍ/ቤት የተወሰነበትን የ18 ሚሊዮን ብር ክፍያ አስሻረ፡፡

​የስኳር ኮርፖሬሽን ግብይት ዘርፍ ከውጪ  ላስገባው ስኳር  ማከማቻ እንዲሆን በአዳማ ከተማ ተከራይቶት የነበረው የግለሠብ መጋዘን በሌሊት ተደርምሶ በመገኘቱ የመጋዘኑ ባለቤት በኦሮሚያ ጠቅላይ ፍ/ቤት አዳማ ምድብ ችሎት የፍትሐብሔር ክስ  በመመስረቱ ፍ/ቤቱ ጉዳዩን ተመልክቶ ለግለሠቡ ጠቅላላ ወጪን ጨምሮ 18 ሚሊዮን ብር እንዲከፈል ወስኖ ጉዳዩ በአፈጻጸም ሒደት ላይ የነበረ እንደነበር ታውቋል።

ይሁንና የኮርፖሬሽኑ ሕግና ኢንቩራንስ የሥራ ክፍል  ለፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ በማቅረብና አፈፃፀሙን በማሣገድ ከሁለት ዓመት ክትትል በኋላ ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት ውሣኔውን ሙሉ በሙሉ እንዲሽረው ማስደረጉን የኮርፖሬሽኑ የሕግና ኢንሹራንስ ጉዳዮች ሥራ አስፈፃሚ አቶ ፋሲል ገ/ማርያም ገልፀዋል፡፡

እንደ አቶ ፋሲል ገለፃ  ለይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት ስኳር ኮርፖሬሽን ተከራይቶት የነበረው መጋዘን የግንባታ ፈቃድ የሌለው ስለመሆኑ፣  የጉዳት ግምት መጠኑ እጅግ የተጋነነ መሆኑ እና የመጋዘኑ መፍረስ በስኳር መደርመስ ምክንያት የተከሰተ  ስለመሆኑ በከሳሽ በኩል የቀረበ ማስረጃ እንደማያረጋግጥ እንዲሁም የመጋዘኑ ግንባታ ጥራት ችግር የነበረበት መሆኑን የሚያመላክቱ ሁኔታዎች መኖራቸው ለውሣኔው መሻር  ምክንያት የሆኑ ኮርፖሬሽኑ ያቀረባቸው ዋና ዋና ክርክሮች መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

የሥራ ክፍሉ ባለፉት ሦስት አመታት ከ424 ሚሊዮን ብር በላይ የያዙ የፍትሐብሔር ክሶችን ማሸነፉን አቶ ፋሲል  ጠቅሰው ለአብነትም ለናሩስ ቲሹ ካልቸር ኃ/የተ/የግ/ማህበር ዘር አገዳ ለማቅረብ የተከፈለው 22 ሚሊዮን ብር በውሉ መሠረት ባለመፈፀሙ ፋብሪካውን በማሣገድ ለኮርፖሬሽኑ እንዲከፍል ማስደረጉን፣ የ71 ሚሊዮን ብር ከተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ጋር የተያያዘ የመሬት ካሣ ክስ ጥያቄ በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት አለአግባብ የቀረበ ክስ ተብሎ ውድቅ እንዲሆን ማድረጉን አቶ ፋሲል ገልጸዋል።

በተጨማሪም የኦሮሚያ ውሃ ሥራዎች በኮርፖሬሽኑ ላይ ያቀረበው የ62 ሚሊዮን ብር ክስ ውድቅ እንዲሆን መደረጉን፣  በኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት ሥራ ተቋራጭ የነበረው የኢትዮ-ካናዳ ኃ/የተ/ማኅበር ማሽን አለአግባብ ለቆመበት ያቀረበው  የ13 ሚሊዮን ብር ክስ ውድቅ መደረጉን እና እንዲሁም በአርጆ ዲዴሣ ስኳር ፋብሪካ የሀረር ተነሺ አርሶ አደሮች ከሌሎች ተቋማት ጋር በመሆን የቀረበበት የ200 ሚሊዮን ብር የመሬት ካሣ ክስ ኮርፖሬሽኑ ነፃ እንዲሆን በረጅም የክትትል ስራ ከተከናወኑ  መካከል በምሣሌነት የሚጠቀሱ ሥራዎች መሆናቸውን አመልክተዋል።

Related posts