የኮርፖሬሽኑ ስራ አመራር ቦርድ በስኳር ልማት ዘርፍ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ያተኮረ ስብሰባ አካሄደ

የስኳር ኮርፖሬሽን ስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው በቅርቡ የተሾሙት ክቡር አምባሳደር ግርማ ብሩ “በስኳር ልማት ዘርፍ ወቅታዊ ሁኔታ፣ ችግሮች እና መፍትሔ የሚፈልጉ ጉዳዮች” በሚል ርዕስ ዙሪያ ከኮርፖሬሽኑ ከፍተኛ አመራር አባላት ጋር ሐሙስ መጋቢት 16 ቀን 2013 ዓ.ም የመጀመሪያ ስብሰባቸውን አካሄዱ።

አምባሳደር ግርማ በኮርፖሬሽኑ ሕንጻ ሶስተኛ ፎቅ በሚገኘው የመሰብሰቢያ አዳራሽ ባደረጉት በዚሁ የመጀመሪያ ስብሰባ ከስኳር ኮርፖሬሽን ከፍተኛ አመራሮች ጋር ትውውቅ ያደረጉ ሲሆን አቶ ማሞ ምህረቱ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት እንዲሁም አቶ ፈቃዱ አጎናፍር ከኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ የስኳር ኮርፖሬሽን ስራ አመራር ቦርድ አዲስ አባላት ሆነው ተመድበዋል።

በዚሁ ስብሰባ የስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ወዮ ሮባ ኮርፖሬሽኑ ስለሚገኝበት ወቅታዊ ሁኔታ፣ ስኳር ልማት ዘርፉ ስላጋጠሙት ችግሮችና መፍትሔ ስለሚፈልጉ ጉዳዮች ሰፊ ማብራሪያ አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል።

በመጨረሻም በስኳር ልማት ዘርፉ ዙሪያ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት በኮርፖሬሽኑ ስራ አመራር ቦርድ በኩል ጥረት እንደሚደረግ አምባሳደር ግርማ አመልክተውና ቀጣይ አቅጣጫዎችን ሰጥተው የዕለቱ ስብሰባ ተጠናቋል።

አምባሳደር ግርማ ብሩ ከአስር ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ስኳር ልማት ኤጀንሲ የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው የሰሩ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ከስኳር ልማት ዘርፉ ጋር ያላቸው የረዥም ጊዜ የካበተ ልምድና እውቀት ስኳር ኮርፖሬሽን እያከናወነ ለሚገኘው ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ የበሰለ አመራር በመስጠት ዘርፉን ወደተሻለ ደረጃ ያሸጋግሩታል የሚል ተስፋ ተጥሎባቸዋል።

Related posts