የኮርፖሬሽኑ የስምንት ወራት የመሰረታዊ ሥራዎች ዕቅድ አፈጻጸም አበረታች መሆኑ ተገለጸ

የስኳር ኮርፖሬሽን የያዝነው በጀት ዓመት የስምንት ወራት የመሰረታዊ ሥራዎች ዕቅድ አፈጻጸም አበረታች መሆኑ ተገለጸ።

ይህ የተገለጸው ከኮርፖሬሽኑ ዋና መስሪያ ቤት፣ ከስኳር ፋብሪካዎችና ስኳር ልማት ፕሮጀክቶች የተውጣጡ አመራር አካላት እና የኮርፖሬሽኑ የመሠረታዊ ሠራተኛ ማኅበር ተወካዮች በቢሾፍቱ ከተማ ከመጋቢት 1 – 3 ቀን 2103 ዓ.ም በተካሄደው የኮርፖሬሽኑ የስምንት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ላይ ነው።

የኮርፖሬሽኑ የስምንት ወራት የመሰረታዊ ሥራዎች ዕቅድ አተገባበር ግምገማ መድረክ ከተወያዬባቸው አጀንዳዎች መካከልም የስኳር ፋብሪካዎች የስምንት ወራት የምርት ዕቅድ አፈጻጸም፣ በለስ ስኳር ፋብሪካን ወደ ስራ በማስገባት ላይ በስፋት ያተኮረ የፕሮጀክት ሥራዎች የስምንት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም፣ የሪፎርም ሥራዎች ዕቅድ አፈጻጸም፣የኮርፖሬሽኑ የፋይናንስ አፈጻጸም፣ የ2013 በጀት ዓመት የስኳር ፋብሪካዎች የክረምት ጥገና እና የ2014 በጀት ዓመት የኮርፖሬሽኑ ዕቅድ ዋና ዋና ትኩረቶች የሚሉት ይገኙበታል።

ኮርፖሬሽኑ በያዝነው በጀት ዓመት ሊያከናውን በዕቅድ በያዛቸው መሰረታዊ ሥራዎች ላይ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ፣ የመለዋወጫ ዕቃዎች ዕጥረት፣ በተለይ በፊንጫኣ ስኳር ፋብሪካ የኦፕሬሽን ስራ ላይ የጸጥታ ችግር ያለው ተጽዕኖ እና ሌሎች መሰል ችግሮች ያሳደሩትን ጫና ለማካካስም ቀሪ የበጀት ዓመቱ ወራት በትኩረት እንዲሰራባቸው የስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወዮ ሮባ አቅጣጫ ሰጥተዋል።

አያይዘውም በተለይ በቀጣይ ቀሪ የበጀት ዓመቱ ወራት የሚሰሩት የሪፎርም ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግ ሁሉም የስራ መሪዎች “ሪፎርም ምንድነው?  ሪፎርም የምናደርገው ምንድነው? እንዲሁም ምን ውጤት ለማምጣት ነው የሪፎርም ሥራ የምናከናውነው?” የሚሉትን መሰረታዊ ጥያቄዎች በይበልጥ ሊመልስ በሚችል መልኩ ማከናወን እንዳለባቸው አቶ ወዮ  አጽንኦት ሰጥተው አሳስበዋል።

በመጨረሻም የኮርፖሬሽኑ አመራር አባላት በበጀት ዓመቱ ቀሪ አራት ወራት ውስጥ የማካካሻ ሥራ በመስራት በዚህ ዓመት የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ መግባባት ላይ በመድረስ የኮርፖሬሽኑ የስምንት ወራት የመሰረታዊ ስራዎች የአፈጻጸም ግምገማ ተጠናቋል።

Related posts