የኮርፖሬሽኑ የአምስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም እየተገመገመ ነው

የስኳር ፋብሪካዎች የክረምት ጥገና የዝግጅት ምዕራፍን ያካተተ የኮርፖሬሽኑ አጠቃላይ የአምስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም እየተገመገመ ነው፡፡

የዋናው መስሪያ ቤት፣ የስኳር ፋብሪካዎች፣ የፕሮጀክቶችና የመሰረታዊ የሰራተኛ ማኅበር አመራሮች በተገኙበት ዛሬ ህዳር 30/ 2012 ዓ.ም የተጀመረው ግምገማ ለቀጣይ ሦስት ቀናት ይቆያል፡፡

የኮፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወዮ ሮባ መድረኩን ሲከፍቱ ፋብሪካዎች የአመቱን እቅድ በማሳካት በገቢ ድርሻቸው መተዳደር እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ በመቀጠልም የተቋሙ የአምስት ወራት የዕቅድ አፈጻጸምና የሪፎርም ሥራዎች ክትትል ሪፖርት በአቶ ሳምሶን ወልቀባ የኮርፖሬት ፕላኒንግ ሥራ አስፈጻሚ ቀርቧል፡፡

በዛሬው የግማሽ ቀን ውሎ የወንጂ ሸዋ፣ የመተሐራ እና የፊንጫኣ ስኳር ፋብሪካዎች ዋና ሥራ አስኪያጆች አጠር ያለ ተጨማሪ የአፈጻጸም ሪፖርት አቅርበው ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ለአራት ቀናት በሚቆየው በዚህ የግምገማ መርሃ ግብር ላይ የፕሮጀክቶች ዕቅድ አፈጻጸም እንዲሁም በዋናው መስሪያ ቤት በሰርቪስ ዘርፍ የተዘጋጁ መመሪያዎች እና ደንቦች ቀርበው ውይይት የሚደረግባቸው ሲሆን፣ የEnterprise Resource Planning (ERP) አስፈላጊነትና ሥራው ያለበት ደረጃን በተመለከተም በአማካሪው ድርጅት ገለጻ ይደረጋል፡፡

 

Related posts