“የወልቃይት ስኳር ፋብሪካ በጦር ጀት ተደብድቧል” ተብሎ የቀረበው መረጃ ከእውነት የራቀ ነው

አዲስ አበባ ህዳር 6/2013 (ኢዜአ) ዘራፊው የህወሓት ቡድን “የወልቃይት ስኳር ፋብሪካ በጦር ጀት ተደብድቧል” በማለት ያናፈሰው ወሬ የሀሰት ፕሮፖጋንዳ መሆኑን የስኳር ኮርፖሬሽን አስታወቀ።

የአጥፊው የህወሓት ቡድን መሪ ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል የወልቃይት ስኳር ፋብሪካ በጦር ጀት ተደብድቧል ሲሉ ትናንት ምሽት የራሳቸው ልሳን በሆነው ሚዲያ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጉዳዩን ለማጣራት የስኳር ኮርፖሬሽን የፕሮጀክት ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አብርሃም ደምሴን አነጋግሯል።

አቶ አብርሃም በወልቃይት ስኳር ፋብሪካ ላይ በመንግስት የጦር ጀት ድብደባ ተፈፅሟል ተብሎ በዘራፊው የህወሓት ቡድን የሚነዛው ወሬ ከእውነት የራቀ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የወልቃይት ስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክት በስኳር ኮርፖሬሽን የሚተዳደርና ንብረትነቱም የፌዴራል መንግስት መሆኑን ጠቅሰው የደረሰበት ጉዳት አለመኖሩን አስታውቀዋል።

የወልቃይት ስኳር ፋብሪካ በዓመት አራት ሚሊዮን 840 ሺህ ኩንታል ስኳርና 41 ሚሊዮን 654 ሊትር ኢታኖል እንዲያመርት ታቅዶ በ2009 ዓ.ም ነው ግንባታው የተጀመረው።

ይሁን እንጂ ፋብሪካው በታቀደለት ጊዜ ባለመጠናቀቁ ከመዘግየቱ ጋር ተያይዞ በአካባቢው ነዋሪዎች ቅሬታ አሳድሯል።

ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚው ፕሮጀክቱ የዘገየበትን ምክንያት ሲያስረዱ የአዋጭነት ጥናት ተጠንቶ ችግሮች እንዳሉበት እየታወቀ በወቅቱ ስልጣን ላይ በነበረው አካል ውሳኔ ተሰጥቶበት ወደ ስራ በመግባቱ መሆኑን ይገልፃሉ።

ኮርፖሬሽኑ በዚሁ ቡድን ተጽዕኖ ውስጥ የነበረ በመሆኑ ለአገዳ ልማት የውሃ አማራጭ ምቹ አለመሆኑ እየታወቀ ወደ ስራ መግባቱና የዲዛይን ችግሩ ለመዘግየቱ ምክንያቶች ናቸው ብለዋል።

የመጀመሪያ ምዕራፍ የፋብሪካው ግንባታ 92 በመቶ፤ የሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ 88 በመቶ መድረሱንም አብራርተዋል።

ይሁን እንጂ በቅርቡ ዘራፊው የህወሓት ቡድን በመከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት ሲያደርስ ፋብሪካውን ይጠብቁ የነበሩ የፌዴራል ፖሊስ አባላትም ቡድኑ ባደራጃቸው ታጣቂዎች ጥቃት ከአካባቢው እንደወጡ ተናግረዋል።

ሌሎች ፋብሪካውን ይጠብቁ የነበሩ ሠራተኞችን ዘራፊው ቡድን ለራሱ ዓላማ ማስፈፀሚያ ስለወሰዳቸው በፋብሪካው የሚገኝ የስራ ተቋራጮች ንብረት እየተዘረፈ እንደሆነም ጠቁመዋል።

አጥፊው የህወሓት ቡድን ሰሞኑን ኅብረተሰቡን ለማደናገር የተለያዩ ሐሰተኛ መረጃዎችን እያሰራጨ ስለመሆኑ መገለፁ ይታወሳል።

የዚህ ቡድን መሪዎች ለፕሮፖጋንዳ በአንድ ጉዳይ ላይ ሁለት የሚጣረሱ ሀሳቦችን ሲሰጡ እየተስተዋለ ነው።

Related posts