የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የወንጂ ሸዋና የመተሐራ ስኳር ፋብሪካዎችን ጎበኘ

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ በክብርት ወ/ሮ ለምለም ሀድጉ የተመራው ቋሚ ኮሚቴ ግንቦት 24 እና 25/2011 ዓ.ም የወንጂ ሸዋና መተሐራ ስኳር ፋብሪካዎችን እና የስኳር አካዳሚን ጎብኝቷል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው በፋብሪካዎቹና በአካዳሚው የመስክ ምልከታ ባደረገበት ወቅት ስለ ፋብሪካዎቹ አመሰራረት፣ ያሉበት ወቅታዊ ሁኔታና ተግዳሮቶች እንዲሁም ስለ ስኳር አካዳሚ ምስረታና ተግባራት በተመለከተ በፋብሪካዎቹ ዋና ሥራ አስኪያጆችና በአካዳሚው የሥራ ኃላፊዎች ገለጻ ተደርጎለታል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው አባላት የሸንኮራ አገዳ ማሳ፣ ፋብሪካ፣ ኢታኖል ፕላንት፣ ቪናስ ከተሰኘው የኢታኖል ተረፈ ምርት የሚዘጋጀውን የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ባዮኮምፖስት) አሰራር፣ የእርሻ ማሽነሪዎች፣ የመስክ መሳሪያዎች ጥገና ወርክ ሾፕ፣ ሆስፒታል እና የሠራተኞች መኖሪያ መንደሮች ጎብኝተዋል፡፡
የኮሚቴው ሰብሳቢ ክብርት ወ/ሮ ለምለም በጉብኝታቸው ወቅት በሠራተኛው የሥራ ትጋት መደሰታቸውን ገልፀው፣ በገንዘብ የማይተመን አቅምና ክህሎት ያካበቱ ታታሪ ሠራተኞች ለህዝባቸውና ለሀገራቸው እየከፈሉ ያሉትን ዋጋ በቦታው ተገኝተው ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል፡፡
ከፋብሪካዎቹ ሠራተኞች፣ ከማኔጅመንቱ እና ከሠራተኛ ማህበር የተነሱትን ጥያቄዎች ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በጋራ ለመፍታት ቋሚ ኮሚቴው በትኩረት እንደሚሰራ ያስታወቁት ሰብሳቢዋ፣ እስከዚያው ሠራተኛው በላቀ የሥራ ተነሳሽነት ሀገር የሚጠብቀውን ስኳር በማምረት ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገት የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ከአደራ ጭምር አሳስበዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው አባላት በፋብሪካዎቹና በአካዳሚው ሲደርሱ በስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወዮ ሮባና በየተቋማቱ ዋና ሥራ አስኪያጆች፣ የሥራ ኃላፊዎች፣ ሠራተኞችና የኪነት ቡድን ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡

Related posts

Leave a Comment