የጣና በለስ ቁጥር 1 ስኳር ፋብሪካ መጪው ግንቦት ወር የሙከራ ምርት እንደሚጀምር ተገለጸ

* ፕሮጀክቱ በባለድርሻ አካላትና በብዙሃን መገናኛ ጋዜጠኞች ተጎብኝቷል

የጣና በለስ ቁጥር 1 ስኳር ፋብሪካ በመጪው ግንቦት ወር የሙከራ ምርት እንደሚጀምር የስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወዮ ሮባ ገለጹ፡፡ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ይህን ያስታወቁት ኮርፖሬሽኑ በበለስ ስኳር ልማት ፕሮጀክት ለባለድርሻ አካላትና ለመገናኛ ብዙሃን ጥር 15 እና 16/2012 ዓ.ም. ባዘጋጀው የጉብኝት መርሃ ግብር ላይ ነው፡፡

በጉብኝቱ ወቅት ከኮርፖሬሽኑ የሥራ አመራር ቦርድ፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት፣ ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ እንዲሁም የፕሮጀክቱ አጎራባች ከሆኑ ሦስት ወረዳዎች የተውጣጡ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና ከአዲስ አበባና ከአማራ ክልል የመጡ ጋዜጠኞች ተሳትፈዋል፡፡

በግንባታ ላይ ከሚገኙ አዳዲስ ግዙፍ የስኳር ልማት ፕሮጀክቶች ውስጥ አንዱ የሆነው የጣና በለስ ስኳር ልማት ፕሮጀክት በአማራ ክልል አዊ ዞን ጃዊ ወረዳ ይገኛል፡፡ ፕሮጀክቱ በ75 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሚለማን የሸንኮራ አገዳ ተጠቅመው እያንዳንዳቸው በቀን 12 ሺህ ቶን አገዳ የመፍጨት አቅም ያላቸውን ሦስት የስኳር ፋብሪካዎች ለመገንባት ታሳቢ ተደርጎ የተጀመረ ቢሆንም፣ ኋላ ላይ ከፋይናንስ እጥረት ጋር በተያያዘ በመንግሥት ውሳኔ የአንደኛው ፋብሪካ (ጣና በለስ ቁጥር 3 ፋብሪካ) ግንባታ ተሰርዟል፡፡

ስኳር ኮርፖሬሽን ቀሪዎቹን ሁለት ፋብሪካዎች በ18 ወራት አስገንብቶ ወደ ስራ ለማስገባት በ2004 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (METEC) ጋር ውል ገብቶ ነበር፡፡ ይሁንና በከፍተኛ የፋብሪካ ግንባታ መጓተት እና በዚህም ምክንያት በስኳር ኮርፖሬሽን ላይ በደረሰ ከፍተኛ ኪሳራ የጣና በለስ ቁጥር 1 እና 2 ስኳር ፋብሪካዎች የግንባታ ውል እንደ ቅደም ተከተላቸው በ2010 ዓ.ም. እና 2009 ዓ.ም. በመንግሥት ውሳኔ እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡

በመቀጠልም የቁጥር 1 ፋብሪካ ቀሪ የግንባታ እና ተያያዥ ተጨማሪ ሥራዎችን አጠናቆ ወደ ምርት ለማስገባት በስኳር ኮርፖሬሽን እና የወልቃይት ስኳር ፋብሪካን እየገነባ በሚገኘው “ካምስ/China CAMC Engineering Co., Ltd. (CAMCE)” በተባለ የቻይና ኩባንያ መካከል ታህሳስ 2011 ዓ.ም የ95 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የግንባታ ውል ተፈርሟል፡፡

ይሁንና ኮንትራቱ በተፈረመበት ወቅት በውጭ ምንዛሬ እጥረት ለኮንትራክተሩ መከፈል የነበረበት ቅድመ ክፍያ በመዘግየቱ ምክንያት ኩባንያው በፍጥነት ወደ ዋናው የግንባታ ሥራ ውስጥ ሳይገባ ለረጅም ጊዜያት ቆይቷል፡፡

በመጨረሻም ለኮንትራክተሩ ቅድመ ክፍያው ተፈጽሞ ከጳጉሜን 5/2011 ዓ.ም. ጀምሮ የፋብሪካው ቀሪ የግንባታ ሥራ በይፋ ተጀምሯል፡፡ እስከ ታህሳስ 30/2012 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥም የፋብሪካው የግንባታ አፈጻጸም በፊት ከነበረበት 65.79 በመቶ ወደ 68.29 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡

የፋብሪካው ግንባታ ተጠናቆ ሙሉ የማምረት አቅሙ ላይ ሲደርስ በዲዛይኑ መሰረት የተጣራ (ሪፋይንድ) ስኳር ከማምረቱም ባሻገር 45 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያመነጭ ታሳቢ ተደርጓል፡፡ ከዚህ ውስጥ 16 ሜጋ ዋት ለኦፕሬሽን ተጠቅሞ ቀሪውን 29 ሜጋ ዋት ወደ ብሔራዊ ግሪድ በመላክ ገቢ ያስገኛል ተብሎም ይጠበቃል፡፡ በተጨማሪም ከፍተኛ መጠን ያለው ሞላሰስ እና ኤታኖል የማምረት አቅም ይኖረዋል፡፡

የጣና በለስ ቁጥር ሁለት ስኳር ፋብሪካን በተመለከተ በቅርቡ ወደ ግል ይዞታ ከሚዘዋወሩ የስኳር ፋብሪካዎችና ፕሮጀክቶች ውስጥ አንዱ ይሆናል ተብሎ ይገመታል፡፡

የጣና በለስ ስኳር ልማት ፕሮጀክት ከተጀመረበት 2003 ዓ.ም. አንስቶ በ13,147 ሄ/ር መሬት ላይ ሸንኮራ አገዳ ተተክሎ የነበረ ቢሆንም፣ አብዛኛው አገዳ በማርጀቱ ምክንያት የማስወገድ ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡ አሁን ላይ በአገዳ የተሸፈነው መሬት 12,362.37 ሄ/ር ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ በጣም ያረጀ የአገዳ ማሳ ተገልብጦ 2,352 ሄ/ር መሬት በአዲስ መልክ በአገዳ ተሸፍኗል:: ይህ አገዳ ፋብሪካው የሙከራ ምርት በሚጀምርበት ወቅት በግብዓትነት የሚቀርብ ይሆናል፡፡

ለፕሮጀክቱ የሸንኮራ አገዳ ልማት የሚውል የመስኖ ውሃ የተጠለፈው ከበለስ ወንዝ ሲሆን፤ በአጠቃላይ 30 ኪ/ሜ ርዝመት ያለውና 60 ሜ/ኩ (cubic metre)ውሃ በሰከንድ ማስተላለፍ የሚችል የወንዝ መቀልበሻ (ዊር)፣ መቆጣጠሪያ፣ የደለል ማስወገጃ እና የዋና ቦይ ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ ከተወሰኑ ማሳዎች በስተቀር አብዛኛው የእርሻ ማሳ ውሃ የሚጠጣው በኦቨር ሄድ ኢሪጌሽን (በስፕሪንክለር) የመስኖ ዘዴ ነው፡፡

ፕሮጀክቱ ከአገዳ ልማት ጎን ለጎን ተጓዳኝ ምርቶችን በማምረት ላይ ሲሆን፣ እስከአሁን ሙዝ በ20 ሄ/ር፣ ማንጎ በ23 ሄ/ር፣ ብርቱካን በ50 ሄ/ር በድምሩ በ93 ሄ/ር መሬት ላይ ተጓዳኝ ምርቶችን የማልማት ሥራ ተከናውኗል፡፡

በሌላ በኩል 1 ሺህ 689 መኖሪያ ቤቶች እና 24 አገልግሎት መስጫ ተቋማት ተገንብተው አብዛኛዎቹ አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው፡፡

የሥራ ዕድልን በተመለከተም ፕሮጀክቱ ከተጀመረ አንስቶ በፕሮጀክቱ፣ በኮንትራክተሮች እንዲሁም በጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት አማካይነት ለ91 ሺህ 493 የአካባቢው ወጣቶችና ዜጎች ቋሚ፣ ኮንትራትና ጊዜያዊ የሥራ ዕድሎች ተፈጥረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ 1,253 የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማትን በማደራጀትና የሥራ ትስስር በመፍጠር ረገድ በኮርፖሬሽኑ በኩል እገዛ ተደርጓል፡፡

Related posts