የጣና በለስ ቁጥር 1 ስኳር ፋብሪካ ግንባታን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ የሚያስችል ሥራ ተጀመረ

  • በ95 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ቀሪ የግንባታ ሥራው የሚካሄደው ይህ ፋብሪካ በስምንት ወራት ጊዜ ውስጥ ስኳር ያመርታል ተብሎ ይጠበቃል

በስኳር ኮርፖሬሽን እና “ካምስ/China CAMC Engineering Co., Ltd. (CAMCE)” በሚባል የቻይና ኩባንያ መካከል ከወራት በፊት በተፈረመ ውል የጣና በለስ ቁጥር 1 ስኳር ፋብሪካ ቀሪ የግንባታ እና ተያያዥ ተጨማሪ ሥራዎችን በ95 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ የሚያስችል ሥራ በዚህ ሳምንት ተጀምሯል፡፡

በስምምነቱ መሰረትም እስከ ስምንት ወራት ባሉት ጊዜያት ውስጥ የፋብሪካው ግንባታ ተጠናቆ ፋብሪካው ስኳር ወደ ማምረት ይሸጋገራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

መንግሥት ለተጀመሩ የስኳር ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ማስፈጸሚያ በቅርቡ ከፈቀደው ከ5.7 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ውስጥ አብላጫው ገንዘብ ላለፉት ስድስት ዓመታት በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን/“ሜቴክ” ግንባታቸው ሲካሄድ ቆይቶ ላልተጠናቀቁት የጣና በለስ ቁጥር 1 እና የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 1 ስኳር ፋብሪካዎች ቀሪ የግንባታ ሥራዎች ማስፈጸሚያ ይውላል፡፡

የጣና በለስ ቁጥር 1 ስኳር ፋብሪካ ቀሪ ግንባታና አዳዲስ ተያያዥ ሥራዎች ተጨምረው “ካምስ” ሥራውን ለማካሄድ የተስማማበት 95 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር “ሜቴክ” ለዚህ ምዕራፍ ግንባታ ከወሰደው ገንዘብ ጋር በንጽጽር ሲታይ ያነሰ ነው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ግንባታውን በይፋ ለማስጀመር በጣና በለስ ቁጥር 1 ስኳር ፋብሪካ ቅጽር ግቢ መጋቢት 22/2011 ዓ.ም. ለተገኙ የ”ካምስ” ኩባንያ የሥራ ኃላፊዎች በፈንድቃ ከተማ ነዋሪዎችና በአካባቢው ማህበረሰብ፣ በጣና በለስ ስኳር ልማት ፕሮጀክት አመራሮችና ሠራተኞች እንዲሁም በጃዊ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪና አመራሮች አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡

የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 1 ስኳር ፋብሪካን በተመለከተም፣ “ጄጄአይሲ/JJIEC” የሚባል የቻይና ኩባንያ የፋብሪካውን ቀሪ የግንባታ ሥራዎች እንዲያካሂድ ስምምነት ላይ ለመድረስ ኩባንያው ያቀረባቸው የቴክኒክና የፋይናንስ ሠነዶች በስኳር ኮርፖሬሽን በመገምገም ላይ ይገኛሉ፡፡ የቀረቡት ሠነዶች አዋጪ ሆነው ከተገኙም በቅርቡ በኮርፖሬሽኑና በጄጄአይሲ መካከል ውል ተገብቶ ኩባንያው ሥራ እንዲጀምር ይደረጋል፡፡

በአጠቃላይ እነዚህ ሁለት ስኳር ፋብሪካዎች ወደ ምርት ሲገቡ አሁን በሥራ ላይ የሚገኙ ስኳር ፋብሪካዎችን (ወንጂ ሸዋ፣ መተሐራ፣ ፊንጫአ፣ ከሰም፣ ተንዳሆ፣ አርጆ ዲዴሳ፣ ኦሞ ኩራዝ ቁጥር 2 እና ኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3) ቁጥር ወደ 10 ያሳድጋሉ፡፡ ከዚህ ባሻገር የሀገር ውስጥ የስኳር ፍላጎትን በራስ አቅም ለማሟላትና ምርቱን ወደ ውጪ ለመላክ የተያዘውን ግብ ከማሳካት አኳያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ፡፡

ላለፉት ስድስት ዓመታት በ“ሜቴክ” ግንባታቸው ሲካሄድ የነበረው የጣና በለስ ቁጥር 1 እና የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 1 ስኳር ፋብሪካዎች የግንባታ አፈጻጸም እንደ ቅደም ተከተላቸው 65.79 በመቶና 80 በመቶ ላይ የደረሰ ሲሆን፣ የሁለቱ ፋብሪካዎች ቀሪ ሥራዎች ተጠናቀው ፋብሪካዎቹ በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ ሲገቡ እያንዳንዳቸው በቀን ከ8 ሺህ እስከ 10 ሺህ ኩንታል ስኳር ያመርታሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከስኳር ምርት ጎን ለጎንም ኤታኖል የማምረትና የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት ከፍተኛ አቅም ይኖራቸዋል፡፡

የጣና በለስ ቁጥር አንድ ስኳር ፋብሪካ ቀሪ የግንባታ ሥራዎችን የሚያካሂደው “ካምስ/CAMCE” የወልቃይት ስኳር ፋብሪካን በመገንባት ላይ ሲሆን፣ የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 1 ስኳር ፋብሪካ ቀሪ የግንባታ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ ፍላጎቱን የገለጸው “ጄጄአይሲ/JJIEC” ደግሞ የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 5 ስኳር ፋብሪካ ግንባታ የሥራ ተቋራጭ ነው፡፡

Related posts

Leave a Comment