የፕላንት እና ፕሮሰስ ጉባኤ ተካሄደ

ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ተቋርጦ የቆየው የፕላንት እና ፕሮሰስ ጉባኤ /Plant & Process Conference በአዳማ ከተማ በኤክስኪዩቲቭ ሆቴል ከሐምሌ 18-19/2011 ዓ.ም. ድረስ ተካሂዷል፡፡

ለሁለት ቀናት በተካሄደው በዚህ ጉባኤ 227 ተሳታፊዎች የተገኙ ሲሆን፣ የ10 ዓመታት የሸንኮራ አገዳ ልማትና የፋብሪካ የምርትና ምርታማነት አፈጻጸምን የሚያሳዩ ጽሁፎች በፕረዘንቴሽን መልክ ቀርበው መፍትሔ አመላካች ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር የሸንኮራ አገዳ ልማት የአምስት ዓመት እንዲሁም የፋብሪካ የሦስት ዓመት ፍኖተ ካርታዎች ለውይይት ቀርበው አስተያያት ተሰጥቶባቸዋል፡፡

በጉባኤው የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወዮ ሮባ ጉባኤው የተዘነጉ መልካም አሠራሮችንና ወደ ስኬት የሚያሸጋግሩንን የሥራ ባህሎች የምንመልስበት የለውጥ እርምጃችን አንዱ አካል ነው ብለዋል፡፡

ከአሁን ቀደም ይህን መሰል ጉባኤ በየአመቱ በመደበኛ ሁኔታ እየተካሄደ ችግሮችን በመፍታት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያግዙ የሃሳብ ልውውጦች ይንሸራሸሩበት እንደነበር ያስታወሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ከዚህ በኋላ ጉባኤው በየአመቱ በመደበኛ ሁኔታ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል፡፡

ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉም በአሁኑ ወቅት ኢንደስትሪውን ከውድቀት ለመታደግና ወደሚታወቅበት የሥራ ባህልና ዝና ለመመለስ ዘጠኝ ዋና ዋና ግቦችን ያካተተ የአሠራር ማሻሻያ/reform ተቀርጸ እየተተገበረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በጉባኤው ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የስኳር ኮርፖሬሽን የሥራ አመራር ቦርድ አባል ፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው በበኩላቸው እንደተናገሩት፣ ባለፉት ዓመታት የስኳር ኢንደስትሪውን ወደ ችግር ውስጥ እንዲገባ ካደረጉት አበይት ምክንያቶች ውስጥ የአዳዲስ የስኳር ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ከመጀመሩ አስቀድሞ በቂ የአዋጪነት ጥናት አለመደረጉ፣ የመሰረተ ልማት አውታሮች አለመዘርጋት፣ የመፈጸምና የማስፈጸም አቅም ማነስ፣ ለክረምት ጥገና የሚያስፈልጉ መለዋወጫዎች በወቅቱና በሚፈለገው መጠን አለመቅረባቸው፣ የለውጥ መሳሪያዎችን በሚፈለገው ልክ ተጠቅሞ ለውጥን አለማስቀጠልና የፋይናንስ እጥረት በዋናነት ይጠቀሳሉ ብለዋል፡፡

በተለይም የፋብሪካዎችን ዓመታዊ የዕቅድ አፈጻጸም በቁልፍ የምርት መለኪያዎች (production & productivity parameters) ገምግሞ የማሻሻያ እርምጃዎችን በየጊዜው ያለመውሰድ ችግር በዘርፉ እድገት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን ጠቁመዋል፡፡

 ንግግራቸውን በመቀጠልም “ዘርፉን ካሉበት ውስብስብ ተግዳሮቶች አላቆ በሀገሪቷ ኢኮኖሚ ውስጥ የጎላ ድርሻ እንዲያበረክት ለማስቻል ከመቼውም ጊዜ በላይ በቁጭትና በላቀ ተስፋ ርብርብ የምናደርግበት ጊዜ አሁን መሆኑን ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት የለብንም፡፡” ብለዋል፡፡

ከዚህ አንጻር በማይቋረጥ የምርምር ሥራ፣ በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እና ፈጣንና ቀጣይ ለውጥን በሚያመጡ አሠራሮች በመታገዝ ኢንዱስትሪውን ምርታማ፣ ትርፋማና ተወዳዳሪ በማድረግ ቀድሞ ወደሚታወቅበት ዝናው መመለስ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ዘርፉን ከውድቀት ለመታደግና ሁለንተናዊ ለውጥ ለማምጣት ከተያዙ ግቦች አንዱ ይህ ኢንደስትሪውን ወደቀድሞው የሥራ ባህል ሊመልስ እንደሚችል ተስፋ የተጣለበት የPlant & Process ጉባኤ መሆኑን እናምናለን ያሉት ፕሮፌሰሩ፣ የጉባኤውን ዓላማ ለማሳካት የስኳር ኮርፖሬሽን እና የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በንግግራቸው ማጠቃለያም ኢንደስትሪው የተጋረጡበትን ችግሮች ተሻግሮ ወደ ስኬት እንዲደርስ የኮርፖሬሽኑ የሥራ አመራር ቦርድ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡

በመጨረሻም ለጉባኤው መሳካት የተለያየ ድጋፍ ያደረጉ ድርጅቶች የተዘጋጀላቸውን የምስጋና የምስክር ወረቀት ከኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ እጅ ተቀብለዋል፡፡

Related posts

Leave a Comment