ጣና በለስ ስኳር ልማት ፕሮጀክት

ፕሮጀክቱ በአማራ ክልል አዊ ዞን ጃዊ ወረዳ ላይ የተቋቋመ ሲሆን፣ የፕሮጀክቱ ጽ/ቤትም ፋንዲቃ ከምትባለው የጃዊ ወረዳ ከተማ አጠገብ ከአዲስ አበባ በ650 ኪ.ሜ እንዲሁም ከባህር ዳር በ225 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡

በዚህ ፕሮጀክት እያንዳንዳቸው በቀን 12 ሺ ቶን አገዳ የመፍጨት አቅም ያላቸው ሁለት ስኳር ፋብሪካዎች በኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (METEC) ግንባታቸው ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም፣ በከፍተኛ የግንባታ መጓተት ምክንያት በስኳር ኮርፖሬሽንና በሜቴክ መካከል በ2004 ዓ.ም. ተደርሶ የነበረው የጣና በለስ ቁጥር 1 እና 2 ስኳር ፋብሪካዎች የግንባታ ውል እንደ ቅደም ተከተላቸው በ2010 ዓ.ም. እና 2009 ዓ.ም. በመንግሥት ውሳኔ እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡

የፋብሪካዎቹ ቀሪ የግንባታ ሥራዎች ተጠናቀው ወደ ምርት ሲገቡ በ40 ሺ ሄክታር መሬት ላይ የሚለማን የሸንኮራ አገዳ በግብዓትነት ይጠቀማሉ፡፡ ለሸንኮራ አገዳ ልማት የሚውለው የመስኖ ውሃ የሚገኘው በበለስ ወንዝ ላይ በተገነባ የውሃ መቀልበሻ ዊር አማካይነት ነው፡፡

ፋብሪካዎቹ ሙሉ የማምረት አቅማቸው ላይ ሲደርሱ እያንዳንዳቸው በዓመት 2 ሚሊዮን 420 ሺ ኩንታል ስኳር እና 20 ሚሊዮን 827 ሺ ሊትር ኢታኖል የማምረት አቅም ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ፋብሪካዎቹ የተጣራ (ሪፋይንድ) ስኳር ለማምረት ዲዛይን ከመደረጋቸው ባሻገር እያንዳንዳቸው 45 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመጨንት አቅም ሊኖራቸው እንደሚችል ታሳቢ ተደርጓል፡፡ ከዚህ አኳያ እያንዳንዱ ፋብሪካ 20 ሜጋ ዋት ለኦፕሬሽን ተጠቅሞ ቀሪውን 25 ሜጋ ዋት ወደ ብሔራዊ ግሪድ በመላክ ገቢ ያስገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ጣና በለስ ቁጥር 1 ስኳር ፋብሪካ

በስኳር ኮርፖሬሽንና በኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (METEC) መካካል ሰኔ 2004 ዓ.ም. በተፈረመ የማሻሻያ ኮንትራት መሰረት የፋብሪካው ግንባታ በ18 ወራት ውስጥ ተጠናቆ ወደ ምርት እንደሚገባ ታሳቢ ተደርጎ ነበር፡፡ ይሁንና በከፍተኛ የግንባታ መጓተት ምክንያት በመንግሥት ውሳኔ ከሜቴክ ጋር የነበረው ኮንትራት በ2010 ዓ.ም. እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡ ውሉ ሲቋረጥ በስኳር ኮርፖሬሽን የውጪ አማካሪ የተረጋገጠው የፋብሪካው የግንባታ ሥራ አፈጻጸም 65% ነበር፡፡

በቀጣይ የፋብሪካው ቀሪ የግንባታ ሥራ ልምድ ባለውና በተመረጠ የውጭ ሀገር ኮንትራክተር የሚጠናቀቅ ይሆናል፡፡ የፋብሪካው ግንባታ ተጠናቆ በሙሉ አቅሙ ወደ ምርት ሲገባ በቀን 12 ሺ ቶን አገዳ ይፈጫል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ጣና በለስ ቁጥር 2 ስኳር ፋብሪካ

በስኳር ኮርፖሬሽንና በኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (METEC) መካካል ሰኔ 2004 ዓ.ም. በተፈረመ የማሻሻያ ኮንትራት መሰረት የፋብሪካው ግንባታ በ18 ወራት ውስጥ ተጠናቆ ወደ ምርት እንደሚገባ ታሳቢ ተደርጎ ነበር፡፡ ይሁንና በከፍተኛ የግንባታ መጓተት ምክንያት በመንግሥት ውሳኔ ከሜቴክ ጋር የነበረው ኮንትራት በ2009 ዓ.ም. እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡ ውሉ ሲቋረጥ በስኳር ኮርፖሬሽን የውጪ አማካሪ የተረጋገጠው የፋብሪካው የግንባታ ሥራ አፈጻጸም 25% ነበር፡፡

በአሁኑ ወቅት አንድ ሀገር በቀል የልማት ድርጅት ፋብሪካውን ለመግዛት ፍላጎት ያሳየ ሲሆን፣ ከስምምነት ላይ ከተደረሰም ፋብሪካው ወደ ግል ይዞታነት የሚሸጋገር ይሆናል፡፡

የጣና በለስ ስኳር ልማት ፕሮጀክት የመስኖ መሠረተ ልማት ግንባታ

ለፕሮጀክቱ የሸንኮራ አገዳ ልማት የሚሆን የመስኖ ውሃ የተጠለፈው ከበለስ ወንዝ ሲሆን፤ በአጠቃላይ በፕሮጀክቱ 30 ኪ/ሜ ርዝመት ያለውና 60 ሜ/ኩ (cubic metre) ውሃ በሰከንድ ማስተላለፍ የሚችል የወንዝ መቀልበሻ (ዊር)፣ መቆጣጠሪያ፣ የደለል ማስወገጃ እና የዋና ቦያ ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ ከተወሰኑ ማሳዎች በስተቀር አብዛኛው የ–እርሻ ማሳ ውሃ የሚጠጣው በኦቨር ሄድ ኢሪጌሽን (በስፕሪንክለር) የመስኖ ዘዴ ነው፡፡

  • 16,146 ሄ/ር ማሳ ውሃ ገብ ተደርጓል፤

የአገዳ ልማት

  • በአጠቃላይ በፕሮጀክቱ 13 ሺ 248 ሄክታር መሬት በአገዳ ተሸፍኗል፤

የቤቶች ግንባታ

  • በአጠቃላይ በፕሮጀክቱ 1 ሺ 469 መኖሪያ ቤቶች እና 20 አገልግሎት መስጫ ተቋማት ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡
የማህበረሰብ ተጠቃሚነት

በፕሮጀክቱ አካባቢ ከሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በልማቱ ጥቅምና ፋይዳ ዙሪያ በተለያዩ ጊዜያት ውይይቶች በመደረጋቸው ልማቱን የጋራ ለማድረግ የሚያግዙ ሥራዎችን ለማከናወን ተችሏል፡፡ በዚህም ተግባር ለልማቱ ተነሽ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ት/ቤቶች፣ ጤና ተቋማት፣ መካካለኛ የመጠጥ ውሃ ተቋማት፣ መንገድ እና ሌሎች የመሰረተ ልማትና የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ተገንብተው አገልግሎት ላይ ውሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ለሀብት ንብረት፣ ለቋሚ ተክል እና ለእምነት ተቋማት ግምት ካሳ  152.6 ሚሊዮን ብር ክፍያ ተፈጽሟል፡፡ የሥራ ዕድልን በተመለከተም ፕሮጀክቱ ከተጀመረ አንስቶ በፕሮጀክቱ፣ በኮንትራክተሮች እንዲሁም በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች አማካይነት ለ91 ሺ 493 የአካባቢው ወጣቶችና ዜጎች ቋሚ፣ ኮንትራትና ጊዜያዊ የሥራ ዕድሎች ተፈጥረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም 1,253 የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ተደራጅተው የሥራ ትስስር ተፈጥሯል፡፡

በአጠቃላይ በስኳር ኮርፖሬሽን ለህብረተሰቡ ተሳትፎ እና የልማት ሥራዎች 178.68 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል፡፡

Related posts

Leave a Comment