ጣና በለስ ቁጥር 2 ስኳር ፋብሪካ

በስኳር ኮርፖሬሽንና በኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (METEC) መካካል ሰኔ 2004 ዓ.ም. በተፈረመ የማሻሻያ ኮንትራት መሰረት የፋብሪካው ግንባታ በ18 ወራት ውስጥ ተጠናቆ ወደ ምርት እንደሚገባ ታሳቢ ተደርጎ ነበር፡፡ ይሁንና በከፍተኛ የግንባታ መጓተት ምክንያት በመንግሥት ውሳኔ ከሜቴክ ጋር የነበረው ኮንትራት በ2009 ዓ.ም. እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡ ውሉ ሲቋረጥ በስኳር ኮርፖሬሽን የውጪ አማካሪ የተረጋገጠው የፋብሪካው የግንባታ ሥራ አፈጻጸም 25% ነበር፡፡

በአሁኑ ወቅት አንድ ሀገር በቀል የልማት ድርጅት ፋብሪካውን ለመግዛት ፍላጎት ያሳየ ሲሆን፣ ከስምምነት ላይ ከተደረሰም ፋብሪካው ወደ ግል ይዞታነት የሚሸጋገር ይሆናል፡፡

የጣና በለስ ስኳር ልማት ፕሮጀክት የመስኖ መሠረተ ልማት ግንባታ

ለፕሮጀክቱ የሸንኮራ አገዳ ልማት የሚሆን የመስኖ ውሃ የተጠለፈው ከበለስ ወንዝ ሲሆን፤ በአጠቃላይ በፕሮጀክቱ 30 ኪ/ሜ ርዝመት ያለውና 60 ሜ/ኩ (cubic metre) ውሃ በሰከንድ ማስተላለፍ የሚችል የወንዝ መቀልበሻ (ዊር)፣ መቆጣጠሪያ፣ የደለል ማስወገጃ እና የዋና ቦያ ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ ከተወሰኑ ማሳዎች በስተቀር አብዛኛው የ–እርሻ ማሳ ውሃ የሚጠጣው በኦቨር ሄድ ኢሪጌሽን (በስፕሪንክለር) የመስኖ ዘዴ ነው፡፡

  • 16,146 ሄ/ር ማሳ ውሃ ገብ ተደርጓል፤

የአገዳ ልማት

  • በአጠቃላይ በፕሮጀክቱ 13 ሺ 248 ሄክታር መሬት በአገዳ ተሸፍኗል፤

የቤቶች ግንባታ

  • በአጠቃላይ በፕሮጀክቱ 1 ሺ 469 መኖሪያ ቤቶች እና 20 አገልግሎት መስጫ ተቋማት ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡
የማህበረሰብ ተጠቃሚነት

በፕሮጀክቱ አካባቢ ከሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በልማቱ ጥቅምና ፋይዳ ዙሪያ በተለያዩ ጊዜያት ውይይቶች በመደረጋቸው ልማቱን የጋራ ለማድረግ የሚያግዙ ሥራዎችን ለማከናወን ተችሏል፡፡ በዚህም ተግባር ለልማቱ ተነሽ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ት/ቤቶች፣ ጤና ተቋማት፣ መካካለኛ የመጠጥ ውሃ ተቋማት፣ መንገድ እና ሌሎች የመሰረተ ልማትና የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ተገንብተው አገልግሎት ላይ ውሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ለሀብት ንብረት፣ ለቋሚ ተክል እና ለእምነት ተቋማት ግምት ካሳ  152.6 ሚሊዮን ብር ክፍያ ተፈጽሟል፡፡ የሥራ ዕድልን በተመለከተም ፕሮጀክቱ ከተጀመረ አንስቶ በፕሮጀክቱ፣ በኮንትራክተሮች እንዲሁም በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች አማካይነት ለ91 ሺ 493 የአካባቢው ወጣቶችና ዜጎች ቋሚ፣ ኮንትራትና ጊዜያዊ የሥራ ዕድሎች ተፈጥረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም 1,253 የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ተደራጅተው የሥራ ትስስር ተፈጥሯል፡፡

በአጠቃላይ በስኳር ኮርፖሬሽን ለህብረተሰቡ ተሳትፎ እና የልማት ሥራዎች 178.68 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል፡፡