ፕሮጀክቶች

ኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት

የኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በደቡብ ኦሞ ዞን (ሰላማጎ እና ኛንጋቶም ወረዳዎች)፣ በቤንች ማጂ ዞን (ሱርማ እና ሜኢኒትሻሻ ወረዳዎች) እና በካፋ ዞን (ዴቻ ወረዳ) የተመረጡ አካባቢዎች እየተካሄደ የሚገኝ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው፡፡

በፕሮጀክቱ ስር እየተገነቡ ከሚገኙ አራት የስኳር ፋብሪካዎች በተሽከርካሪ ለመድረስ ከአዲስ አበባ በሆሳዕና – አርባ ምንጭ – ጂንካ መስመር ከ825-954 ኪሎ ሜትር ወይም ከአዲስ አበባ በሻሸመኔ – አርባ ምንጭ – ጂንካ መንገድ ከ859-988 ኪሎ ሜትር መጓዝን ይጠይቃል፡፡ በአየር ትራንስፖርት ከሆነ ደግሞ ከአዲስ አበባ ጂንካ ለአንድ ሰዓት ያህል በመብረር ከጂንካ ፋብሪካዎቹ ያሉበት ድረስ ከ80-220 ኪሎ ሜትር በተሽከርካሪ መጓዝ የግድ ይላል፡፡

በፕሮጀክቱ በ100 ሺ ሄክታር መሬት ላይ የሚለማ የሸንኮራ አገዳ ተጠቅመው በቀን 60 ሺ ቶን አገዳ የመፍጨት አቅም ያላቸው አራት ስኳር ፋብሪካዎች እየተገነቡ ሲሆን፣ በሙሉ አቅማቸው ማምረት ሲጀምሩ ሶስቱ እያንዳንዳቸው በቀን 12 ሺ ቶን አገዳ በመፍጨት በዓመት 2 ሚሊዮን 500 ሺ ኩንታል ስኳር እና እያንዳንዳቸው በዓመት 28 ሚሊዮን ሊትር ኤታኖል ያመርታሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ እንዲሁም እያንዳንዳቸው ከሚያመነጩት 45 ሜጋ ዋት ውስጥ 29 ሜጋ ዋቱን ወደ ብሔራዊ ቋት ይልካሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በተመሳሳይ አንደኛው ፋብሪካ በቀን 24 ሺ ቶን አገዳ በመፍጨት በዓመት 5 ሚሊዮን ኩንታል ስኳር እና 56 ሚሊዮን ሊትር ኤታኖል እንደሚያመርት ታሳቢ ተደርጓል፡፡ በተጨማሪ ከሚያመነጨው 90 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል ውስጥ 32ቱን ለራሱ ተጠቅሞ 58 ሜጋ ዋቱን ወደ ብሔራዊ ቋት እንደሚልክ ይጠበቃል፡፡

ከእነዚህ አራት ስኳር ፋብሪካዎች ውስጥ በቻይናው ኮምፕላንት ኩባንያ የተገነቡት የኦሞ ኩራዝ ቁጥር ሁለት እና ቁጥር ሦስት ስኳር ፋብሪካዎች ወደ ምርት ገብተዋል፡፡ የተቀሩት የቁጥር አንድና አምስት ስኳር ፋብሪካዎች በግንባታ ላይ ናቸው፡፡

የኢንቨስትመንት ወጪ

በኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት እየተገነቡ ለሚገኙ አራት ስኳር ፋብሪካዎች እስከ መጋቢት 30/2010 ዓ.ም ድረስ ለካፒታል ኢንቨስትመንት (ለመስኖ መሰረተ ልማት፣ ለመሬት ዝግጅት፣ ለአገዳ ልማት፣ ለቤቶች ግንባታ፣ ለፋብሪካ ግንባታ ወዘተ)፣ ለፕሮጀክቶች ቅድመ ኦፕሬሽንና ለሥራ ማስኬጃ 34.8 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ወጪ ተደርጓል፡፡

የማህበሰብ ተጠቃሚነት

  • ስኳር ኮርፖሬሽን ስኳር ከማምረት ባሻገር በኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት አካባቢ የሚኖረውን የአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ ኑሮ ለማሻሻልና በዘላቂነት የልማት ተጠቃሚነቱን በማረጋገጥ ቀጣናዊ ትራንስፎርሜሽን ለማምጣት እንዲቻል በርካታ የህዝብ ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ሊያረጋግጡ የሚችሉ መጠነ ሰፊ ሥራዎችን ከደቡብ ብ/ብ/ህ ክልል መንግሥት ጋር በመቀናጀት ሲሰራ ቆይታል፡፡
  • በዚህ መሰረት ኮርፖሬሽኑ የመስኖ መሰረተ ልማት ወጪን ሳይጨምር ለአካባቢው ማህበረሰብ ተጠቃሚነት 86 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል፡፡ ይህ በመሆኑም ከ50 በላይ የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትና የመሰረተ ልማት አውታሮች (ት/ቤት፣ ጤና ኬላ፣ የኮሚዩኒቲ ፖሊሲንግ ጽ/ቤት፣ የቀበሌ ጽ/ቤት፣ የህብረት ስራ ማህበር ጽ/ቤት፣ ወፍጮ ቤት፣ የእንስሳት ጤና ኬላ፣ ንጹህ መጠጥ ውሃ፣ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች፣ በመስኖ የለማ መሬት ወዘተ) ተገንብተው ለማህበረሰቡ አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው፡፡

የካሳ ክፍያ

  • በኮፈር ዳም የመስኖ ግድብ ምክንያት የንብ ቀፎ እና ሰብላቸው ለተነካባቸው አርብቶ አደሮች የንብ ቀፎ ግምት እና የምርት ማካካሻ ካሳ 1 ሚሊዮን 141 ሺህ 165 ብር ክፍያ ተፈጽሟል፡፡

የህዝብ ውይይቶችና ሞብላይዜሽን

  • በልማቱ አካባቢ ከሚገኘው የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በልማቱ ጥቅሞችና ፋይዳ ዙሪያ በተለያየ ጊዜ ለተደረጉ ውይይቶች 2 ሚሊዮን 584 ሺ 309.30 ብር ወጪ ተደርጓል፡፡

የክህሎት ስልጠና

የአካባቢው ህብረተሰቡ ልማቱ በሚፈጠረው የስራ እድል ተሳታፊና ተጠቃሚ መሆን እንዲችል ለመለስተኛ ሙያ ክህሎት ሥልጠናዎች ብር 2 ሚሊዮን 866 ሺህ 658 ብር ወጪ ተደርጓል፡፡

የሥራ ዕድል

ፕሮጀክቱ ከተጀመረ ከ2003 ዓ.ም. አንስቶ በፕሮጀክት፣ በኮንትራክተሮች እንዲሁም በጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት በቋሚ፣ በኮንትራትና ጊዜያዊነት ከ110 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የአካባቢው ወጣቶችና ዜጎች የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ሲሆን፣ በሌላ በኩል ከ300 በላይ የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማትን አደራጅቶ ወደ ሥራ ለማስገባት ተችሏል፡፡

ሸንኮራ አገዳ አብቃይና አቅራቢ ማኅበራት (አውትግሮወር)

በፕሮጀክቱ አካባቢ የሚገኙትን አርብቶ አደሮች በዘላቂነት የልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ በአራት ማኅበራት ለተደራጁ 2 ሺ 205 አባ/እማ ወራዎች ለእያንዳንዳቸው በመስኖ የለማ 0.75 ሄ/ር መሬት በመስጠት በድምሩ 1 ሺ 653.75 ሄ/ር መሬት ላይ ሸንኮራ አገዳ አልምተው ለፋብሪካው በሽያጭ እንዲያቀርቡ ሁኔታዎች እየተመቻቸላቸው ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ባገኙት መሬት በቆሎና የመሳሰሉ ሰብሎችን አምርተው መጠቀም ጀምረዋል፡፡ በዚህም ወደ ከፊል አርሶ አደርነት ሽግግር ላይ ይገኛሉ፡፡

በግንባታ ላይ የሚገኙ ፋብሪካዎች/ፕሮጀክቶች

ፋብሪካ ሸንኮራ አገዳ የመፍጨት አቅም /በቀን፣ በቶን የሚገኝበት ክልል ለሸንኮራ አገዳ የሚውል መሬት/በሄክታር
ኦሞ ኩራዝ ቁጥር 1 12,000 ደቡብ ብ/ብ/ህ 20,000
ኦሞ ኩራዝ ቁጥር 5 24,000 ደቡብ ብ/ብ/ህ 40,000
ጣና በለስ 1 12,000 አማራ 20,000
ጣና በለስ 2 12,000 አማራ 20,000
ወልቃይት 24,000 ትግራይ 40,000