ኦሞ ኩራዝ ቁጥር 5 ስኳር ፋብሪካ

በደቡብ ኦሞ ዞን ኛንጋቷም ወረዳ የሚካለለው የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 5 ስኳር ፋብሪካ ከአዲስ አባባ በ954 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ JJIEC በተባለ የቻይና ኩባንያ ከህዳር 2009 ዓ.ም ጀምሮ በሁለት ምዕራፍ እየተገነባ የሚገኘው ይህ ፋብሪካ፣ በሙሉ አቅሙ ወደ ምርት ሲገባ በቀን 24 ሺ ቶን አገዳ ይፈጫል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት የመስኖ መሠረተ ልማት ግንባታ

በፕሮጀክቱ በዋናነት የኦሞ ወንዝን መሠረት በማድረግ 100 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ሸንኮራ አገዳ ለማልማት የሚያስችል መጠነ ሰፊ የመስኖ መሰረተ ልማት ግንባታ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

ጊዜያዊ ግድብ/Coffer Dam

ለፕሮጀክቱ ውሃ ለማቅረብ በኦሞ ወንዝ ላይ ጊዜያዊ ግድብ (ኮፈር ዳም) ተገንብቶ አገልግሎት በመስጠት ላይ ነው፡፡

የዋና ቦይ ግንባታ 

በኦሞ ኩራዝ የሸንኮራ አገዳ ለማልማት ከኦሞ ወንዝ በስተግራ (left bank) የ55 ኪ.ሜ ዋና ቦይ (main canal) የመሰረተ ልማት ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረ ሲሆን፣ በተመሳሳይ በቀኝ በኩል (right bank) እየተገነባ ከሚገኘው 134 ኪ.ሜ የዋና ቦይ (main canal) ግንባታ ውስጥ 43 ኪሎ ሜትሩ ተጠናቆ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ እንዲሁም የቀሪው 91 ኪ.ሜ የዋና ቦይ ቁፋሮ ተጠናቆ የስትራክቸር ስራ ይቀራል፡፡

በአጠቃላይ በኦሞ ኩራዝ መስኖ ልማት ፕሮጀክት የተጀመረውን የዋና ቦይ የመሰረተ ልማት ግንባታና ሌሎች ተያያዥ ሥራዎችን ሙሉ በሙሉ አጠናቆ ወደ ሥራ ለማስገባት 22.3 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል፡፡

የሸንኮራ አገዳ ልማት

በፕሮጀክቱ እስካሁን 30 ሺህ ሄክታር መሬት ውሃ ገብ ማድረግ የተቻለ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 16 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ሸንኮራ አገዳ ተተክሏል፡፡

የቤቶች ግንባታ

በአጠቃላይ በፕሮጀክቱ 1,140 የመኖሪያ ቤቶች እና 52 አገልግሎት መስጫ ብሎኮች ተገንብተው   አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡