ወልቃይት ስኳር ልማት ፕሮጀክት

የፕሮጀክቱ ጽ/ቤት ከአዲስ አበባ በ1 ሺ 30 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በትግራይ ክልል በምዕራባዊ ዞን ወልቃይት ወረዳ ይገኛል፡፡ በ40 ሺ ሄክታር መሬት ላይ የሚለማ የሸንኮራ አገዳን በግብዓትነት ተጠቅሞ በቀን 24 ሺ ቶን አገዳ የመፍጨት አቅም ያለው ይህ ፋብሪካ CAMC በተባለ የቻይና ኩባንያ እየተገነባ ነው፡፡

በዚህ መሰረት ፋብሪካው በሁለት ምዕራፍ እየተገነባ ሲሆን፣ ሙሉ የማምረት አቅሙ ላይ ሲደርስ በዓመት 4 ሚሊዮን 840 ሺ ኩንታል ስኳር እና 41 ሚሊዮን 654 ሊትር ኢታኖል ያመርታል ተብሎ ታሳቢ ተደርጓል፡፡

ፕሮጀክቱ ለአገዳ ልማት የሚያስፈልገውን የመስኖ ውሃ አቅርቦት ከተከዜ፣ ከቃሌማ እና ከዛሬማ ወንዞች የሚያገኝ ይሆናል፡፡

የመስኖ መሠረተ ልማት ግንባታ

  • 5 ቢሊየን ሜትር ኩብ ውሃ የመያዝ አቅም ያለው “የሜይ-ዴይ” ግድብ በዛሬማ ወንዝ ላይ እየተገነባ ነው፡፡ ግድቡ ሲጠናቀቅ 840 ሜትር ስፋት እና 135.5 ሜትር ቁመት ይኖረዋል፤
  •  ከግድብ ግንባታው ጎን ለጎን በጠብታ መስኖ 7 ሺ ሄ/ር መሬት ለማልማት NETAFIM ከተባለ የእስራኤል ኩባንያ የመስኖ መሠረተ ልማት ሥራ ተቋራጭ ጋር ውል ተገብቶ ሥራው ተጀምሯል፤
  • የ10 ኪ/ሜትር የዋና ቦይ (Main canal) ግንባታ ተጠናቋል
  •  3 ሺ ሄ/ር መሬት ከቃሌማ ወንዝ በፓምፕ ጠልፎ በsprinkler ለማልማት የግንባታ ሥራው እየተከናወነ ነው፤የመስኖ ውሃው እስከሚደርስ ድረስም የጥጥ ልማት እየተካሄደ ይገኛል፤
  • 260 ሄ/ር መሬት ለዘር አገዳ ውሃ ገብ ሆኗል፤

የአገዳ ልማት

  • ውሃ ገብ ከሆነው መሬት ውስጥ 140 ሄክታሩ ላይ የዘር አገዳ ተተክሏል፤

የቤቶች ግንባታ

  • 1,066 መኖሪያ ቤቶችና 53 የአገልግሎት መስጫ ብሎኮች ተገንብተው ለአገልግሎት ቀርበዋል፡፡

የማህበረሰብ ተጠቃሚነት

የአካባቢው ህብረተሰብ ልማቱ በሚፈጠረው የሥራ እድል ተሳታፊና ተጠቃሚ መሆን እንዲችል የመለስተኛ ሙያ ክህሎት ሥልጠናዎች ተሰጥተውት ለ84 ሺ 659 የአካባቢው ወጣቶችና ዜጎች ቋሚ፣ ኮንትራትና ጊዜያዊ የሥራ ዕድሎች ተፈጥሮላቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም 161 የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች እንዲደራጁና በሥራ እንዲተሳሰሩ ድጋፍ ተደርጓል፡፡

በሌላ በኩል በልማቱ ምክንያት ተነሺ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የሃብት ንብረት ግምት ካሳ እና የምርት ማካካሻ ካሳ ክፍያ ተፈጽሟል፡፡ ከዚህ ባሻገር በፕሮጀክቱ ክልል ውስጥ ይኖሩ ለነበሩና በመጀመሪያው ዙር ወደ ቆራሪት ሰፈራ መንደር መልሰው ለተቋቋሙ 2 ሺ 621 የህብረተሰብ ክፍሎች ስምንት የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት (ት/ቤቶች፣ የሰውና እንስሳት ህክምና መስጫ ተቋማት፣ የአርሶ አደሮች ማሰልጠኛ ወዘተ)፣ 14 የመጠጥ ውሃ ተቋማትና 62 ኪሎ ሜትር መንገድ ተገንብቶላቸው አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡

በአጠቃላይ በስኳር ኮርፖሬሽን ለህብረተሰቡ ተሳትፎ እና የልማት ሥራዎች 407.68 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል፡፡