145 ሚሊየን ብር ይወጣበት የነበረ ቦይለር በራስ አቅም ተጠገነ

በፊንጫኣ ስኳር ፋብሪካ 145 ሚለየን ብር ለጥገና የተጠየቀበት ቦይለር በራስ አቅም ተጠገነ፡፡

በፈንጫኣ እና በመተሐራ ስኳር ፋብሪካዎች ከፍተኛ የቦይለር ባለሙያዎች የተጠገነው የፋብሪካው ቦይለር ቁጥር 3 የጥገና ጨረታ ወጥቶበት የነበረ ሲሆን፣ በወቅቱ ተጫራቾች ያቀረቡት ዋጋ ከፍተኛ በመሆኑ እና ለጥገና የጠየቁት ጊዜም በመርዘሙ የፋብሪካው ማኔጅመንት የፊንጫኣ ስኳር ፋብሪካ እና የመተሐራ ስካር ፋብሪካ የቦይለር ባለሙያዎች እንዲጠግኑት ውሳኔ አሳልፎ እንደነበር የፊንጫኣ ፋብሪካ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል በላከልን መረጃ አስታውሷል፡፡

በዚህ መሰረት የሁለቱ ፋብሪካዎች የቦይለር ባለሙያዎች ከጥቅምት 30 ጀምሮ ለ40 ቀናት ባደረጉት ርብርብ የጥገና ሥራው ታህሣስ 10/2012 ዓ.ም ተጠናቆ ቦይለሩ የኃይል ምርት እንዲጀምር ተደርጓል፡፡

ከ50 በላይ ባለሙያዎች በተሳተፉበት በዚህ የጥገና ሥራ የሚያስፈልገው ዋነኛው የቦይለር ፓይፕ ከመተሐራና ከአርጆ ዲዴሳ ስኳር ፋብሪካዎች መገኘቱን የደረሰን መረጃ ይጠቁማል፡፡

የእድሳት ሥራው በተያዘለት ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅ የፋብሪካው የማኔጅመንት አባላትና የሥራ ክፍሎች ከፍተኛ ትብብርና ድጋፍ እንዳደረጉም ለማወቅ ተችሏል፡፡

የተጠገነው ቦይለር እሳት ሲለኮስ የፋብሪካው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ደረጄ ጉርሜሳ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር “በራስ አቅም፣ በአነስተኛ ወጪና በአጭር ጊዜ ውስጥ ይህን የመሰለ ሙሉ የእድሳት ሥራ ማከናወን ከቻልን ወደፊት የስኳር ኢንዱስትሪውን ብሩህ የለውጥና እድገት ጊዜ እውን ማድረግ እንችላለን” ብለዋል፡፡

ከመተሐራ ስኳር ፋብሪካ በጥገናው የተሳተፉት አቶ አረፈዓይኔ ንጉሤ በበኩላቸው የስራው ክብደት በሠራተኞች ጥንካሬና አንድነት እንደቀለለ ተናግረዋል፡፡

በተያያዘ ዜና የቦይለር ቁጥር 4 የጥገናና የማሻሻያ ሥራን ሙሉ በሙሉ በራስ አቅም ለማከናወን መታቀዱን የፋብሪካው ሕዝብ ግንኙነት ከፍል ዘግቧል፡፡

Related posts