• +251115526653
  • info@etsugar.com
  • Phillips Building, Chad St, Addis Ababa, Ethiopia
ዜናዎች
የኅዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት ፋብሪካውን ጎበኙ

የኅዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት ፋብሪካውን ጎበኙ

የኅዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ አባላት የወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካን ጎበኙ፡፡

በቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ ኮሬ የሚመራው የልዑካን ቡድን ፋብሪካውን ባለፈው ሣምንት ሲጎበኝ በኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ የማኔጅመንት አባላት እና በፋብሪካው ከፍተኛ አመራሮች ገለፃ ተደርጎላቸዋል፡፡

ለልዑካን ቡድኑ አባላት የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የፋብሪካው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጀማል አማን የስኳር ኢንዱስትሪውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ ከሸንኮራ አገዳ ልማት ጋር ተያይዞ በአገዳ አብቃይ ማኅበራት በኩል ፋብሪካው እያጋጠሙት ያሉትን ችግሮች አውስተው በአገዳ አብቃይ ገበሬ ማኅበራት ሥር የነበሩና ከልማቱ የወጡትን የሸንኮራ አገዳ መሬቶች የኅብረት ሥራ ማኅበሩን በማጠናከር ከአካባቢው መስተዳደር አካላት ጋር በጋራ በመሆን እና ነባሩን ስትሪንግ ኮሚቴ በማጠናከር መስራት እንዲቻል ማነቆ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ምክር ቤቱ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

ዋና ሥራ አስኪያጁ ከዚህም ሌላ ፋብሪካው በተጓዳኝ ስለሚያመርተው ስንዴ፣ ቦሎቄ እና ሌሎች ሰብሎች እንዲሁም እየተካሔደ ስላለው የፋብሪካው የክረምት መደበኛ ጥገና ማብራሪያ ሰጥተው በኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ ሰብሳነት ውይይት ተደርጎበታል፡፡

በውይይቱ ወቅት ከልዑካን ቡድኑ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች የስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ ተወካይ እና የኮርፖሬት ጉዳዮች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዘመድኩን ተክሌ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ አቶ ዘመድኩን በማብራርያቸውም የመለዋወጫ እጥረትን አስመልክተዉ በአብዛኛዉ የመለዋወጫ ችግር በሁሉም ፋብሪካዎች የሚታይ መሆኑን እና ለፋብሪካዎች ከዉጪ የሚገቡ መለዋወጫዎችን በሃገር ዉስጥ በማምረት ወደ ስራ ለማስገባት ከቻይና ባለሃብቶች ጋር ለመስራት ጥረቶች መደረጋቸውን አመልክተዋል፡፡ አያይዘውም የሸንኮራ አብቃይ አርሶአደሮች በሚፈለገዉ ልክ ከስኳር ኢንዱስትሪዉ ማግኘት የሚገባቸዉን ጥቅም እያገኙ ነዉ ማለት እንደማይቻልና ፋብሪካዎች ስኳርን ቢያመርቱም የመሸጫ ዋጋውን የሚወስነዉ መንግሥት በመሆኑ ተወዳዳሪ መሆን እንዳልቻሉ ጠቁመው ምክር ቤቱ የበኩሉን ሁለንተናዊ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

ከመስክ ጉብኝቱ ማግስት በቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጆ እና ምክትላቸው ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ ሰብሳቢነት በአዳማ ከተማ በተደረገ ስብሰባ የልዑካን ቡድኑ አባላት በኅዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኩል ለኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ እና ለፋብሪካው የሚፈለገውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል ሲል የፋብሪካው የኅዝብ ግንኙነት እና ተሳትፎ አገልግሎት ዘግቧል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *