• +251115526653
  • info@etsugar.com
  • Phillips Building, Chad St, Addis Ababa, Ethiopia
ዜናዎች
የጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ ያስገነባዉን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በማሰመረቅ ስራ አስጀመረ

የጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ ያስገነባዉን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በማሰመረቅ ስራ አስጀመረ

የፋብሪካዉ ዋና ስራ አስኪያጀ አቶ አበበ ይሁኔ፣ የጃዊ ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ ወርቁ እና የፋብሪካዉ ዘርፍ ሰራተኛ ማህበር ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን አሰፋ ከተማሪ ተወካዮች ጋር በመሆንና ችቦ በመለኮስ ትምህርት ቤቱ በይፋ ተመርቆ ስራ መጀመሩን ያበሰሩ ሲሆን በምረቃ ፕሮግራሙ ጥሪ የተደረገላቸዉ የጃዊ ወረዳ ሴክተር መስሪያ ቤት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች፣የፋብሪካዉ አመራርና ሰራተኞች እንዲሁም የአካባቢዉ ማህበረሰብ ተወካዮች በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ተገኝተዋል፡፡

በዕለቱ የግንባታ ሂደቱን ሲቆጣጠር የነበረዉ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አዕምሮ ዉባለ የትምህርት ቤቱን የግንባታ ሂደት የተመለከተ ሪፖርት አቅርበው ዉይይት የተደረገበት ሲሆን በውይይቱም የትምህርት ቤቱ ግንባታ ለረጅም ጊዜ ሲጎተት እንደቆየ እና ተቋራጭ ድርጀቱ በጥራት ማጎደልና በአፈጻጸም ችግር ኮንትራቱን እንዲያቆርጥ ተደርጎ በፋብሪካው የውስጥ አቅም ግንባታውን በማጠናቀቅ ወደ ሥራ ማስገባት መቻሉ ተመልክቷል፡፡

ኮሚቴዉ ልዩ ልዩ የገቢ ማስገኛ ዘዴዎችን በማመቻቸትና ከፋብሪካዉ አመራር አካላት ጋር በመነጋገር በጥሬ ገንዘብ ከ 8 መቶ ሽህ ብር በላይ ማግኘት መቻሉንና የፋብሪካዉ አመራሮችን ጨምሮ የቋሚና ሲዝናል ሰራተኞችን በማሰተባበር ደግሞ ከ4 መቶ ሽህ ብር በላይ እንዲሁም ከዘርፍ ሰራተኛ ማህበር 1 መቶ ሽህ ብር በማሰባሰብ በአጠቃላይ ከ1.3 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ሥራ ማስኬጃ ካፒታል ትምህርት ቤቱ ወደ ስራ መግባቱ ታውቋል፡፡

በተጨማሪም ፋብሪካዉ በትምህርት ቤቱ ግንባታ ወቅት የልዩ ልዩ ቁሳቁስ እና የማሽነሪ እገዛዎችን በማድረግ በገንዘብ ሲሰላ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ እገዛ ማድረጉ ተመልክቷል፡፡ የፋብሪካ ግንባታ ሥራ ተቋራጩ የቻይናው ኩባንያ (ካምሴ) በበኩሉ ግምቱ ከ45 ሺህ ብር በላይ የሚገመት የአይነት ድጋፍ ማድረጉን እና በአጠቃላይ ከ3.3 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የግንባታ ሥራ ማጠናቀቁ ታውቋል፡፡

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙትና በትምህርት ቤቱ ግንባታ ወቅት በልዩ ልዩ መልኩ ድጋፍ ሲያደርጉ የነበሩ የተማሪ ወላጆችና የፋብሪካዉ ሰራተኞች የት/ቤቱ ግንባታ መጠናቀቅ ከዚህ ቀደም የነበረዉን የትምህርት አሰጣጥ ጥራት የበለጠ በማሻሻል ተማሪዎች ዉጤታማ እንዲሆኑ ያግዛቸዋል ብለዋል፡፡

የፋብሪካዉ ዋና ስራ አሰኪያጀ አቶ አበበ ይሁኔ በበኩላቸዉ የዚህ ትምህርት ቤት ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት መብቃቱ በአካባቢያቸን ያሉንን አቅሞች ለይተን ከተጠቀምንባቸዉ የተሻለ ስራ ለሀገርና ለአከባቢዉ ማህበረሰብ መስራት እንደምንችል ያየንበት ተግባር ነዉ ብለዋል፡፡ አያይዘውም የትምህርት ቤት ግንባታው የፋብሪካዉን ሰራተኛ ብቻ ሳይሆን የአካባቢዉን ማህበረሰብም ተጠቃሚ የሚያደረግ እንደሆነና ፋብሪካዉ ወደዚህ አካባቢ መምጣቱ ለማህበረሰቡ ከሚያበረክታቸዉ ትሩፋቶች ዉስጥ ተጠቃሽ መሆኑን አዉስተዋል፡፡ በፋብሪካዉ በኩል ትምህርት ቤቱ የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጥ ማኛዉንም ድጋፍ አቅም በፈቀደ መልኩ እንደሚያደረግ ገልጸው በዚህ አጭር ጊዜ ዉስጥ ግንባታዉ ተጠናቆ ለአገልግሎት በመብቃቱ እንኳን ደስ አላቸሁ ብለዋል ፡፡

በመጨረሻም የጃዊ ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ ወርቁ ጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ ስታንዳርዱን የጠበቀ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በመገንባት ወደ ስራ ማስገባቱ እንዳስደሰታቸዉ ገልጸዉ መንግስትም የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ ረገድ ከፍተኛ ሚና ይወጣል ብለዋል፡፡ የወረዳዉ ትምህርት ጽ/ቤት መምህራንን ከመመደብ ጀምሮ የትምህርት ግብዓቶችን ከዚህ በፊት ሲያሞላ መቆየቱን አቶ አዲሱ አስታዉሰዉ በቀጣይም ትምህርት ቤቱን ሞዴል ለማድረግ ከሰኳር ፋብሪካ አመራርና ስራተኞች ጋር በጋራ ጠንክረን እንሰራለን ማለታቸውን ጠቅሶ የዘገባው የፋብሪካው የሕዝብ ግንኙነትና ተሳትፎ ክፍል ነው፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *