
ምርምርና ልማት ዘርፍ
በሀገራችን በስኳር ኢንዱስትሪ የምርምር ሥራ የተጀመረው ኤች.ቪ.ኤ በተባለ የሆላንድ ኩባንያ እ.ኤ.አ. በ1951 ነበር። የምርምር ክፍሉ ዋናው ማዕከል በአምስተርዳም ሆኖ በወቅቱ በኢትዮጵያ ለሚገኙ የስኳር ፋብሪካዎች ጠንካራ ድጋፍ ይሰጥ ነበር፡፡
ኩባንያው በወንጂ ሸንኮራ አገዳ መትከልና ስኳር ማምረት ሲጀምር እ.ኤ.አ. ከ1958 አንስቶ በስኳር ኢንዱስትሪ ሥልጠና ይሰጥ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ኋላ ላይ የፋብሪካዎቹን ወደ መንግሥት ይዞታነት መሸጋገር ተከትሎ የምርምር ሥራው በተለያዩ አደረጃጀቶች ሲመራ ቆይቶ 2003 ዓ.ም ወዲህ የስኳር ኮርፖሬሽን በአዋጅ ቁጥር 192/2003 ሲቋቋም ለምርምርና ሥልጠና ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት የሚከተሉትን አበይት ተግባራት ተከናውነዋል፡፡
ምርትና ምርታማነትን ማሳደግና የማምረቻ ወጪን መቀነስ የሚያስችል እንዲሁም ችግር ፈቺነትን መሰረት ያደረገ ምርምር (applied research) በማካሄድ ጥቅም ላይ የዋሉ ቴክኖሎጂዎችን ማፍለቅ ተችሏል፤
- የአመራረት ቅልጥፍናን ለማሻሻል የተገኘው የምርምር ውጤት በእያንዳንዱ ስኳር ፋብሪካና ማሳ ላይ በአግባቡ እንዲውል የማስረጽ ሥራ ተሰርቷል፤
- በአመራረት ሥርአት ላይ የሚከሰቱ ችግሮችን በመለየት የማስተካከያ እርምጃዎች (optimization) እንዲወሰዱ የቴክኒክና የምክር አገልግሎት ተሰጥቷል፤
- ሥራ ላይ የዋሉ የምርምር ውጤቶች ለኢንዱስትሪው ያስገኙትን ፋይዳ እና በአካባቢው ላይ ያደረሱትን ተጽዕኖ በመገምገም አዳዲስ የምርምር አቅጣጫዎችና ስትራቴጂዎች ተነድፈዋል፤
- ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ፣ በሽታ የሚቋቋሙ፣ ከፍተኛ የስኳር ይዘት ያላቸውና ቶሎ የሚደርሱ የሸንኮራ አገዳ ዝርያዎችን እንዲሁም የተሻሻሉ የሸንኮራ አገዳና የስኳር አመራራት ዘዴዎችና ቴክኖሎጂዎችን ለፋብሪካዎችና ፕሮጀክቶች በማስተዋወቅ ሥራ ላይ እንዲውሉ ተደርጓል፤
- በኦፕሬሽን ላይ የነበሩ ቴክኖሎጂዎች ደረጃቸው (ስታንዳርድ) ሳይጓደል ትግበራቸው የሚቀጥልበትን አሠራር በመቀየስ ምርጥ ተሞክሮዎችን ለመቀመርና ለማስተግበር ተሞክሯል፤
- በስኳር ቴክኖሎጂ የተለያዩ የምርምር ውጤቶችን በማውጣት የስኳር ብክነትን (Sugar loss) እና የማምረቻ ጊዜ ብክነትን (Down time) በመቀነስ የስኳር ግኝት አቅምን (Overall recovery) የመጨመር ሥራዎች ተከናውነዋል፤
- ከስኳር ተረፈ ምርቶችና ከኤታኖል ተያያዥ ምርቶችን ለማምረት የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን ማፍለቅና ማላመድ ተችሏል፤
- ኢንዱስትሪውን በሠለጠነና ውጤታማ በሆነ የሰው ኃይል ለመደገፍ የሚያስችሉ ሥልጠናዎች ለባለሙያዎች ተሰጥተዋል፤
ከአዲስ አበባ በ110 ኪ.ሜ ርቀት ወንጂ ላይ የሚገኘው የምርምርና ልማት ዘርፍ እነዚህን ተግባራት የበለጠ በብቃት ለመወጣት በ2008 ዓ.ም. በአዲስ መልክ ተደራጅቷል፡፡
በዚህ መሰረት ዋና ማዕከሉ በወንጂ ሸዋ፣ መተሐራ፣ ፊንጫአ፣ አርጆ ዲዴሳ፣ ከሰም፣ ጣና በለስ፣ ኦሞ ኩራዝ 2 እና 3 ስኳር ፋብሪካዎች የምርምር ጣቢያዎችን አቋቁሞ የሸንኮራ አገዳ፣ የዝርያ ልማት እና የስኳር ቴክኖሎጂ ምርምሮችን በማካሄድ ላይ የሚገኝ ሲሆን በተንዳሆ ስኳር ፋብሪካና በወልቃይት ስኳር ልማት ፕሮጀክት የነበሩት የምርምር ጣቢያዎች የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካና የወልቃይት ስኳር ፕሮጀክት ሥራ ከማቆማቸው ጋር ተያይዞ የጣቢያዎቹ ሥራ ተቋርጦ ይገኛል፡፡
በአሁኑ ወቅት የኢንዱስትሪውን ተወዳዳሪነት ለማረጋገጥና ከአካባቢ ጋር ተስማሚ የሆኑ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በአስተማማኝ ደረጃ ለማቅረብ የሚያስችሉ ሶስት ፍኖተ ካርታዎችን (በባዮሪፋይነሪ፣ በስኳር ቴክኖሎጂ እና በደቂቅ ዘአካላት) በማዘጋጀት ወደ ትግበራ ተገብቷል፡፡