• +251115526653
 • info@etsugar.com
 • Phillips Building, Chad St, Addis Ababa, Ethiopia

የስኳር ኢንዱስትሪ በኢትዮጵያ

በሀገራችን ዘመናዊ የስኳር ኢንዱስትሪ የተጀመረው የኢትዮጵያ መንግሥት ኤች ቪ ኤ (HVA) ከተባለ የሆላንድ ኩባንያ ጋር የአክስዮን ስምምነት ከፈረመበት ከ1943ዓ.ም አንስቶ ነው፡፡ ኩባንያው 5 ሺ ሄክታር የሸንኮራ አገዳ ማልሚያ መሬት ተረክቦ ሥራውን የጀመረው ከአዲስ አበባ 110 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በወንጂ ከተማ ሲሆን፣ በቅድሚያ የወንጂ ስኳር ፋብሪካን ገንብቶ መጋቢት 11 ቀን 1946ዓ.ም ስራ አስጀምሯል፡፡ ፋብሪካው በወቅቱ በቀን 1 ሺ 400 ኩንታል ስኳር እያመረተ ምዕዙን ስኳር እና ባለ 10 ሳንቲም እሽግ ስኳር ለገበያ ያቀርብ ነበር፡፡

በወቅቱ የወንጂ አካባቢ በዓለማችን ከፍተኛ ምርት ከሚያስመዘግቡና ለስኳር ምቹ ከሆኑ አካባቢዎች አንዱ ስለነበር ከወንጂ ስኳር ፋብሪካ ምስረታ ጋር ተያይዞ የወንጂ ከረሜላ ፋብሪካ ሰኔ 1953ዓ.ም ተቋቁሞ ደስታ ከረሜላ ለገበያ ማቅረብ ጀመረ፡፡

የወንጂ ስኳር ፋብሪካ ሥራ ከጀመረ ከዘጠኝ ዓመት በኋላ በ1955ዓ.ም እዛው ወንጂ ላይ የተቋቋመው የሸዋ ስኳር ፋብሪካ በቀን 1 ሺ 700 ኩንታል ስኳር ያመርት ነበር፡፡

ወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ በሚል የጋራ መጠሪያ በአንድ አስተዳደራዊ መዋቅር ስር ይተዳደሩ የነበሩት ሁለቱ አንጋፋ ፋብሪካዎች አንድ ላይ በዓመት 750 ሺ ኩንታል ስኳር ገደማ ያመርቱ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የወንጂ እና ሸዋ ስኳር ፋብሪካዎች ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ካገለገሉ በኋላ በእርጅና ምክንያት እንደ ቅደም ተከተላቸው በ2004ዓ.ም እና በ2005ዓ.ም መጨረሻ የተዘጉ ሲሆን፣ በምትካቸው አዲስ ዘመናዊ ፋብሪካ ተገንብቶ ከ2005ዓ.ም ጀምሮ ስኳር እያመረተ ይገኛል።

በኢትዮጵያ የስኳር አዋጭነትን የተረዳው የሆላንዱ ኩባንያ በተመሳሳይ የመተሐራ ስኳር ፋብሪካን ከአዲስ አበባ 200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው መርቲ ከተማ ሰኔ 26 ቀን 1957ዓ.ም በአክሲዮን መልክ በመመስረት በ1962ዓ.ም ፋብሪካውን ሥራ አስጀመረ፡፡

ይሁንና እነዚህ ፋብሪካዎች በ1967ዓ.ም በሀገሪቱ በተደረገው የመንግሥት ለውጥ ምክንያት ሙሉ በሙሉ በመንግሥት ይዞታ ስር ወደቁ፡፡ ይህን ተከትሎ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሕግ ክፍል ማስታወቂያ ቁጥር 58/1970 የተቋቋመው የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ወንጂ ሸዋ እና መተሐራ ስኳር ፋብሪካዎችን ጨምሮ አዲስ ከተማና አስመራ ከረሜላ ፋብሪካዎችን እንዲያስተዳድር ተደረገ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከስኳር ልማት ጋር በተያያዘ በፊንጫአ ሸለቆ በ1967ዓ.ም በተካሔደ የመጀመሪያ ደረጃ ጥናት አካባቢው ለስኳር ምርት አዋጭ ሆኖ ተገኘ፡፡ ይህን ተከትሎም ለአገሪቱ ሦስተኛ የሆነውን የፊንጫአ ስኳር ፋብሪካ ለመገንባት ጠለቅ ያለ ጥናት እንዲካሔድ ተወስኖ ቡከርስ አግሪካልቸራል ኢንተርናሽናል ሊሚትድ በተባለ የእንግሊዝ ኩባንያ አማካይነት ከ1970ዓ.ም ጀምሮ ዝርዝር ጥናት ተካሔደ፡፡

በፋይናንስ እጥረት ሳቢያ ተጓቶ የነበረው የፋብሪካው ግንባታ በ1981ዓ.ም፤ የሸንኮራ አገዳ ተከላ ስራው ደግሞ በ1984ዓ.ም ተጀመረ፡፡ ከስምንት ዓመት በኋላ የፋብሪካው ግንባታ ተጠናቆ በ1991ዓ.ም የፊንጫኣ ስኳር ፋብሪካ ወደ መደበኛ የማምረት ስራ ተሸጋገረ፡፡

ከቀደምቶቹ ስኳር ፋብሪካዎች በተሻለ ዘመናዊ የሆነውን የፊንጫአ ስኳር ልማት ፕሮጀክት የፋብሪካና ኤታኖል ግንባታ ያከናወኑት ኤፍ.ሲ.ሼፈርና አሶሽየትስ የተባለ የአሜሪካ ኩባንያና በእርሱ ስር የፋብሪካውን ተከላ ያካሔደው ድዌቶ ኢንተርናሽናል የተባለ የደች ኩባንያ ሲሆኑ፣ በግንባታው በርካታ የሀገር በቀል ድርጅቶች ተሳትፈዋል፡፡

ልማቱ በዚህ መልክ እየተካሔደ ባለበት ወቅት አራት ፋብሪካዎችን ያስተዳድር የነበረው የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ከ14 ዓመታት ቆይታ በኋላ በ1984ዓ.ም በሕግ ፈረሰ፡፡ በምትኩም በደንብ ቁጥር 88/1985 መተሐራ ስኳር ፋብሪካ፤ በደንብ ቁጥር 89/1985 ወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካና በደንብ ቁጥር 199/86 ፊንጫኣ ስኳር ፋብሪካ እራሳቸውን የቻሉ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሆነው እንዲቋቋሙ ተደረገ፡፡

ኋላም ለስኳር ፋብሪካዎቹ የጋራ አገልግሎት እንዲሰጥ የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ድጋፍ ሰጪ ማዕከል አክስዮን ማኅበር በሶስቱ ስኳር ፋብሪካዎች፣ በልማት ባንክ እና በመድን ድርጅት በአክስዮን መልክ ህዳር 1990ዓ.ም ተቋቋመ፡፡ ከዓመታት በኋላም በማዕከሉ ምትክ የኢትዮጵያ ስኳር ልማት ኤጀንሲ በአዋጅ ቁጥር 504/98 ተመስርቶ የስኳር ፋብሪካዎቹን በመቆጣጠር፣ በፕሮጀክት ልማት፣ በምርምር፣ በስልጠናና በግብይት ረገድ ድጋፍ ሲሰጥ ቆየ፡፡

በዚህ ጊዜ ውስጥ የኢፌዲሪ መንግሥት የስኳር ልማቱን ለማስፋፋት በማቀድ በአፋር ክልል የተገነባውን አራተኛውን የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ በደንብ ቁጥር 122/98 አቋቋመ፡፡ ፋብሪካው በ50 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሚለማ የሸንኮራ አገዳን በግብዓትነት እንዲጠቀም ታሳቢ ተደርጎ የተገነባ ሲሆን፣ በዓመት 3 ሚሊዮን  ኩንታል ስኳር እና 30 ሚሊዮን ሊትር ኤታኖል የማምረት አቅም ያለው ግዙፍ ፕሮጀክት ነው፡፡ በዚህ መሰረት የፋብሪካው የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ ተጠናቆ ወደ ምርት ገብቶ የነበረ ቢሆንም በአካባቢው በ2010 ዓ.ም ባጋጠመ ድርቅ ሳቢያ የፕሮጀክት ሥራው ተቋርጦ ይገኛል፡፡

የቀድሞው ስኳር ኮርፖሬሽን ምሥረታ   

የስኳር ልማት እንቅስቃሴው በዚህ መልክ ከቀጠለ በኋላ ከጥቅምት 19 ቀን 2003ዓ.ም ጀምሮ የኢትዮጵያ ስኳር ልማት ኤጀንሲ እንዲፈርስ ተደርጎ በምትኩ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 192/2003  የቀድሞው ስኳር ኮርፖሬሽን ተቋቋመ፡፡ የኢትዮጵያ ስኳር ኢንደስትሪ ግሩፕ በመጋቢት 2014ዓ.ም እስከተቋቋመበት እና ኮርፖሬሽኑ በሕግ እስከፈረሰበት ጊዜ ድረስ  ኮርፖሬሽኑ በስራ አመራር ቦርድ የሚተዳደር ሆኖ፣ የኢፌዲሪ አስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 916/2008 መሰረት ተጠሪነቱ ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ሆኖ ቆይቶ ነበር፡፡

የስኳር ኢንዱስትሪ ንኡስ ዘርፍ ስትራተጂያዊ ማዕቀፍ

 የሀገራችን ኢንዱስትሪ በኢኮኖሚው ውስጥ የመሪነቱን ሚና እንዲጫወት የላቀ አስተዋጽኦ ካላቸው ትላልቅ ፕሮጀክቶች መካከል የስኳር ልማት አንዱ ነው። ኢትዮጵያ ይህን የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለማስፋፋትና ምርታማነቱን ለማሳደግ የሚያስችል ከፍተኛ የሰው ኃይልና የተፈጥሮ ሃብት አላት፡፡

በተለይም ሀገሪቱ ለሸንኮራ አገዳ ልማት ተስማሚ አየር ንብረት፣ በመስኖ ሊለማ የሚችልና በጥናት የተረጋገጠ እስከ 1.4 ሚሊዮን ሔክታር የሚደርስ ሰፊ የእርሻ መሬት እንዲሁም በቂ ውሃ ያላት በመሆኑ ዘርፉ ካለፉት 12 ዓመታት ጀምሮ የበለጠ ትኩረት እንዲሰጠው ተደርጓል፡፡ ከዚህ ባሻገር መንግሥት በወንጂ ሸዋ፣ መተሐራ እና ፊንጫአ ስኳር ፋብሪካዎች ብቻ ለረጅም ዓመታት ያህል ተወስኖ የቆየውን የስኳር ኢንዱስትሪ በደቡብ ብ/ብ/ሕ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በኦሮሚያ፣ በአፋር፣ በአማራ እና በትግራይ ክልሎች ሲያስፋፋ ቆይቷል፡፡

በዚህ መሰረት በአማራና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በጣና በለስ ስኳር ልማት ፕሮጀክት በ50ሺ ሄክታር መሬት የሚለማን የሸንኮራ አገዳ በግብዓትነት የሚጠቀሙ እያንዳንዳቸው በቀን 12ሺ ቶን አገዳ መፍጨት የሚችሉ ሁለት የስኳር ፋብሪካዎች ለመገንባት ዕቅድ በመያዝ የጣና በለስ ቁጥር አንድ ስኳር ፋብሪካን የግንባታ ሥራ አጠናቆ በ2013 ዓ.ም ግንቦት ወር መጨረሻ ላይ በተጨማሪም በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች በደቡብ ኦሞ፣ ቤንች ማጂ እና ካፋ ዞኖች በኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት በ100 ሺህ ሄክታር መሬት የሚለማን ሸንኮራ አገዳ በግብዓትነት የሚጠቀሙ እያንዳንዳቸው በቀን 12 ሺህ ቶን አገዳ መፍጨት የሚችሉ ሦስት ፋብሪካዎችን እንዲሁም በቀን 24 ሺህ ቶን አገዳ የመፍጨት አቅም ያለውን አንድ ፋብሪካ በጠቅላላው አራት የስኳር ፋብሪካዎችን ለመገንባት ታቅዶ የፋብሪካዎቹን ግንባታ በማካሔድ ኦሞ ኩራዝ ቁጥር ሁለት እና ኦሞ ኩራዝ ቁጥር ሦስት ስኳር ፋብሪካዎች ግንባታቸው ተጠናቆ ወደ ምርት የገቡ ሲሆን ግንባታቸው በተለያየ  ደረጃ የሚገኘው የኦሞ ኩራዝ ቁጥር አንድ እና አምስት ስኳር ፋብሪካዎች የግንባታ ሂደት ከፋይናንስ ግኝት ጋር በተያያዘ ለጊዜው ተቋርጦ ይገኛል፡፡

በተመሳሳይ በትግራይ ክልል በወልቃይት ስኳር ልማት ፕሮጀክት በ50ሺህ ሄክታር መሬት የሚለማን የሸንኮራ አገዳ ተጠቅሞ በቀን 24ሺህ ቶን አገዳ መፍጨት የሚችል የስኳር ፋብሪካ ግንባታ ተጀምሮና የግድብና የመስኖ አውታር ግንባታው ሰማንያ በመቶ ደርሶ የነበረ ቢሆንም  ከሰሜኑ የአገራችን የጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ ግንባታው ተቋርጦ ይገኛል፡፡

ምንም እንኳ ኢንዱስትሪው ከግማሽ ምዕተ አመት በላይ እድሜ ያስቆጠረ ቢሆንም፣

 • ኢንዱስትሪው በሚፈለገው ፍጥነት አለማደግ፣
 • ሀገሪቱ በተከታታይ እያስመዘገበች ካለችው ፈጣን የኢኮኖሚያዊ እድገት ጋር ተያይዞ የህብረተሰቡ የስኳር ፍላጐት በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መምጣት፣
 • ነባር የስኳር ፋብሪካዎች የሚያመርቱት የስኳር መጠን እያደገ የመጣውን የሀገር ውስጥ ፍላጎት ማርካት አለመቻል፣
 • የሕዝብ ቁጥር ማደግ እና
 • ስኳርን በግብዓትነት የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎች በከፍተኛ ሁኔታ ከመስፋፋት ጋር ተያይዞ የስኳር ፍላጎትና አቅርቦት ሊጣጣም አልቻለም፡፡

በመሆኑም አገሪቷ ለስኳር ልማት ያላትን ዕምቅ አቅም በተገቢው ደረጃ ጥቅም ላይ ለማዋል መንግስት አምስት ስኳር ፋብሪካዎችን በአዋጅ ቁጥር 500/2014 ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ ያደረገ ሲሆን እነርሱም ወንጂ ሸዋ፣መተሐራ፣ ከሰም፣ ጣና በለስ እና ፊንጫኣ ስኳር ፋብሪካዎች ናቸው፡፡

ሀገራዊ የስኳር አቅርቦት

አሁን ያለው አጠቃላይ ሀገራዊ የስኳር አቅርቦት መጠን በዓመት ከ5ሚሊየን እስከ 6 ሚሊየን ኩንታል ያህል ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ባለፉት ዓመታት በዓመት ከ3 እስከ 4 ሚሊዮን ኩንታል የሚደርስ ስኳር በሀገር ውስጥ የተመረተ ሲሆን፣ በፍላጎትና በአቅርቦት መካከል ያለው ከ1 ሚሊየን እስከ 2 ሚሊየን ኩንታል  የሚደርስ ስኳር በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገር ውስጥ በየዓመቱ እየገባ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን የአንድ ሰው አመታዊ የስኳር ፍጆታ ከ10 ኪሎ ግራም በላይ እንደሚደርስ ቢገመትም፣ እየቀረበ ያለው መጠን ግን 6 ኪሎ ግራም ያህል ነው፡፡

ከዚህ አንጻር መንግሥት የስኳር ፍላጎትና አቅርቦትን ለማጣጣም በየአመቱ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እያስገባ በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡

ይሁንና ክፍተቱን ለመሙላት ስኳር ከውጭ መግዛት ዘላቂ መፍትሔ ባለመሆኑና በዚህ ሁኔታም መቀጠል ስለማይቻል ከመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን አንስቶ በሀገራችን ከፍተኛ ትኩረት ከተሰጣቸው የማኑፋክቸሪንግ የኢንዱስትሪ ዘርፎች አንዱ የስኳር ኢንዱስትሪ ንዑስ ዘርፍ ሊሆን ችሏል፡፡ በዚህ መሰረት መንግሥት፡-

 • የስኳር ፍላጎትና አቅርቦትን ለማጣጣም፣
 • በዘርፉ ሰፊ የስራ እድል በመፍጠር የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል፣
 • በተለይም በልማቱ አካባቢዎች የሚኖሩ ሕዝቦችን ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ፣
 • የአገሪቱን የስኳር ፍላጎት በሀገር ውስጥ ምርት ለማሟላት እና
 • በቀጣይም ምርቱን ወደ ውጭ በመላክ የስኳር ልማት ዘርፉ ለአገሪቱ የውጪ ምንዛሪ ማስገኘት ይችል ዘንድ የተለያዩ የፖሊሲ ማሻሻያ እርምጃችን በመውሰድ ላይ ይገኛል፡፡

የማህበረሰብ ተጠቃሚነት

 • ልማቱን ተከትሎ 255 የማኅበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት (ትምህርት ቤት፣ ጤና ተቋማት፣ ወፍጮ ወዘተ)  እና የመሰረተ ልማት አውታሮች (ንጹህ መጠጥ ውሃ፣ መንገድ ወዘተ) ተገንብተው የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች ተጠቃሚ በመሆን የኑሮ ደረጃቸው መሻሻል ጀምሯል፤
 • ለአካባቢው ተወላጆች ልጆች ቅድሚያ በመስጠትና በትራክተር ኦፕሬተርነት፣ በግምበኛነት፣ በአናጺነት፣ በጥበቃና በመሳሰሉት ሙያዎች በማሰልጠን በየፕሮጀክቶቹ ተመድበው እንዲሰሩ ተደርጓል፤
 • የአካባቢው ወጣቶች በጥቃቅንና አነስተኛ ማኅበራት ተደራጅተው በልማቱ ስራ ውስጥ እንዲሳተፉና ገቢ እንዲገኙ ድጋፍ ተደርጓል፤
 • በመስኖ የለማ መሬት ለአካባቢው ነዋሪዎች አመቻችቶ በማስረከብ በተለይም በስኳር ልማት ፕሮጀክቶች አካባቢ የሚገኘው ማህበረሰብ እንደ በቆሎ የመሳሰሉ ሰብሎችን አምርቶ እንዲጠቀም ተደርጓል፡፡ በቀጣይም ማህበረሰቡ በዘላቂነት ሸንኮራ አገዳ አልምቶ ለፋብሪካ እንዲያቀርብ ለማስቻል ለወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ አገዳ አብቅለው ከሚያቀርቡ አርሶ አደሮች (አውት ግሮወርስ) ልምድ እንዲያገኙ ተደርጓል፤
 • ከ2003ዓ.ም እስከ ሐምሌ 2014ዓ.ም ለማኅበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት፣ለመሠረተልማት፣ ለካሳ፣ ለሙያ ሥልጠና እና ሌሎች መሠል ተግባራት1.2 ቢሊየን ብር ያህል ወጪ ተደርጓል እንዲሁም
 • ልማቱ ከተጀመረ ከ2003ዓ.ም ወዲህ ለ450ሺህ ያሕል ዜጎች የቋሚ፣የጊዜአዊ እና የኮንትራት የሥራ ዕድሎች ተፈጥረዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *