• +251115526653
  • info@etsugar.com
  • Phillips Building, Chad St, Addis Ababa, Ethiopia
ፋብሪካዎች
ጣና በለስ ቁጥር 1 ስኳር ፋብሪካ

ጣና በለስ ቁጥር 1 ስኳር ፋብሪካ

በአማራ ክልል አዊ ዞን ጃዊ ወረዳ በሚገኘው የጣና በለስ ስኳር ልማት ፕሮጀክት ሊገነቡ በዕቅድ ተይዘው ከነበሩ ሦስት ስኳር ፋብሪካዎች አንዱ የሆነው ይህ ፋብሪካ የተቋቋመው በ2003 ዓ.ም. ነው፡፡ ፋብሪካው ከአዲስ አበባ በ650 ኪ.ሜ እንዲሁም ከባህርዳር በግልገል በለስ በ225 ኪ.ሜ ርቀት አስፋልት መንገድ ላይ ይገኛል፡፡

ፕሮጀክቱ ሲታቀድ ለሶስቱም ፋብሪካዎች በ75 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሚለማ የሸንኮራ አገዳ መሬት እንዲኖረው ታሳቢ ተደርጎ የተጀመረ ሲሆን የዚህ ፋብሪካ ግንባታ ሥራ ተጠናቆ ግንቦት 29 ቀን 2013 ዓ.ም በይፋ በመመረቅ የሙከራ ምርት የጀመረው የጣና በለስ ቁጥር 1 ስኳር ፋብሪካ በ25 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሚለማ የሸንኮራ አገዳ የሚጠቀም ፋብሪካ ነው፡፡ ሁለተኛው ምዕራፍ የፋብሪካ ግንባታ ሲጠናቀቅም በቀን 12 ሺህ ቶን አገዳ የመፍጨት አቅም ይኖረዋል፡፡

የቀድሞው ስኳር ኮርፖሬሽን (የአሁኑ የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ) የጣና በለስ ቁጥር 1 ፋብሪካን በ18 ወራት አስገንብቶ ወደ ስራ ለማስገባት በ2004 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (METEC) ጋር ውል ገብቶ ነበር፡፡ ይሁንና የፋብሪካ ግንባታ ሥራው ከመጠናቀቂያ ጊዜው ከ7 ዓመታት በላይ በመጓተቱ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የፋብሪካ ግንባታ ውሉ በ2010 ዓ.ም. በመንግሥት ውሳኔ ነው እንዲቋረጥ የተደረገው፡፡ ውሉ እስኪቋረጥ ድረስ የፋብሪካ ግንባታው 65 % ብቻ ነበር የደረሰው፡፡

የፋብሪካውን ቀሪ የግንባታና ተያያዥ ተጨማሪ ሥራዎችን አጠናቆ ወደ ምርት ለማስገባት በቀድሞው ስኳር ኮርፖሬሽን እና “ካምሲ” /China CAMC Engineering Co., Ltd. (CAMCE)/ በተባለ የቻይና ኩባንያ መካከል ታህሳስ 2011 ዓ.ም የግንባታ ውል የተፈረመ ሲሆን ለዚህም መንግሥት በአሜሪካ እና በኢትዮጵያ ምንዛሬ በአጠቃላይ  የ95 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል፡፡ በዚህ መሰረት የቻይናው የግንባታ ተቋራጭ ካምሲ የፋብሪካውን ግንባታ አጠናቆ በ2013 ዓ.ም ሥራ ለማስጀመር ከፍተኛ ርብርብ አድርጎና የመጀመሪያው ምዕራፍ የፈብሪካ ግንባታ ሥራ ተጠናቆም ግንቦት 29 ቀን 2013 ዓ.ም በክቡር የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) ተመርቆ ፋብሪካው ወደ ሙከራ ምርት ገብቷል፡፡

ጣና በለስ ቁጥር አንድ ስኳር ፋብሪካ በሙሉ የማምረት አቅሙ ላይ ሲደርስ በዲዛይኑ መሰረት የተጣራ (ሪፋይንድ) ስኳር ከማምረቱም ባሻገር 45 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያመነጭ ታሳቢ ተደርጓል፡፡ ከዚህ ውስጥ 16 ሜጋ ዋት ለፋብሪካው ኦፕሬሽን ተጠቅሞ ቀሪውን 29 ሜጋዋት ወደ ብሔራዊ ግሪድ በመላክ ገቢ ያስገኛል ተብሎ ከመጠበቁ በተጨማሪ ከፍተኛ መጠን ያለው ሞላሰስ እና ኤታኖል የማምረት አቅም ይኖረዋል፡፡

ጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ  ቁጥር 495/2014 ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ ከተደረጉት አምስት ስኳር ፋብሪካዎች መካከል አንደኛው ነው፡፡

የመስኖ መሠረተ ልማት ግንባታ

ለፋብሪካው የሸንኮራ አገዳ ልማት የሚሆን የመስኖ ውሃ የተጠለፈው ከበለስ ወንዝ ሲሆን በአጠቃላይ በፕሮጀክቱ 30 ኪ/ሜ ርዝመት ያለውና 60 ሜ/ኩ (cubic meter) ውሃ በሰከንድ ማስተላለፍ የሚችል የወንዝ መቀልበሻ (ዊር) ፣ መቆጣጠሪያ፣ የደለል ማስወገጃ እና የዋና፣ መካከለኛ እና አነስተኛ ቦይ ግንባታ ሥራዎች ተጠናቀው አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ ከተወሰኑ ማሳዎች በስተቀር አብዛኛው የእርሻ ማሳ ውሃ የሚያገኘው በኦቨርሄድ ኢሪጌሽን (በስፕሪንክለር) የመስኖ ዘዴ ነው፡፡

በእስካሁኑ የመስኖ መሰረተ ልማት ሒደት ለፋብሪካ የሸንኮራ አገዳ ልማት ከሚያስፈልገው አጠቃላይ 40 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት ውስጥ 16,146 ሄ/ር መሬት ውሃገብ ተደርጓል፡፡

የሸንኮራ አገዳ ልማት

እስከ ሰኔ 2014 ዓ.ም በአገዳ የተሸፈነ መሬት 13,147 ሄ/ር ሲሆን፣ ፋብሪካው በወቅቱ ባለመድረሱ በጣም ያረጀ የአገዳ ማሳ ተገልብጦና ወደ ራቱን ተቀይሮ 4,374 ሄ/ር መሬት እንክብካቤ እየተደረገለት የሚገኝ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 3,893 ሄ/ር የለማ የሸንኮራ አገዳ ወደ ፋብሪካ ለማቅረብ ዝግጁ ሆኖ ይገኛል፣ ይህም አገዳ በለስ ቁጥር 1 ስኳር ፋብሪካ ከሙከራ ምርት ወደ መደበኛ ምርት በሚያደርገው ሽግግር ወቅት በግብዓትነት እንዲቀርብ ተደርጓል፡፡

ተጓዳኝ ምርት

ፕሮጀክቱ ከአገዳ ልማት ጎን ለጎን ተጓዳኝ ምርቶችን በማምረት ላይ ሲሆን፣ እስካሁን ሙዝ በ24.5 ሄ/ር፣ ማንጎ በ23 ሄ/ር፣ ብርቱካን በ80 ሄ/ር፣ ፓፓያ 2.6 ሄ/ር፣ ዘይቱና 0.44 ሄ/ር እና አቮካዶ 0.42 ሄ/ር በድምሩ በ125.72 ሄ/ር መሬት ላይ ተጓዳኝ ምርቶችን የማልማት ሥራ ተከናውኗል፡፡

የቤቶች ግንባታ

በፕሮጀክቱ 1 ሺህ 703 መኖሪያ ቤቶች እና 20 አገልግሎት መስጫ ተቋማት ተገንብተው አብዛኛዎቹ አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው፡፡

የማኅበረሰብ ተጠቃሚነት

በፋብሪካው አካባቢ ከሚገኙ 67,151 የአካባቢው ማኅበረሰብ አባላት ጋር በልማቱ ጥቅምና ፋይዳ ዙሪያ በተለያዩ ጊዜያት ውይይቶች በመደረጋቸው ልማቱን የጋራ ለማድረግ የሚያግዙ ሥራዎችን ለማከናወን ጥረቶች ተደርገዋል፡፡

የቀድሞው ስኳር ኮርፖሬሽን (የአሁኑ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ) በመደበው በጀት ለልማቱ ተነሽ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ት/ቤቶች፣ ጤና ተቋማት፣ መለስተኛና ጥልቅ የመጠጥ ውሃ ጉድጓድ፣ መንገድ እና ሌሎች የማህበራዊና የመሰረተ ልማት አገልግሎት መስጫ ተቋማት ተገንብተው አገልግሎት ላይ ውለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ለልማቱ ተነሽዎች ለሀብት ንብረት፣ ለቋሚ ተክል እና ለእምነት ተቋማት ግምት ካሳ 152,600.000 ሚሊዮን ብር ክፍያ ተፈጽሟል፡፡

የሥራ ዕድልን በተመለከተም ፕሮጀክቱ ከተጀመረ አንስቶ በፋብሪካው፣ በኮንትራክተሮች እንዲሁም በጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት አማካይነት ለ3,754 የአካባቢው ወጣቶችና ዜጎች ቋሚ፣ ኮንትራትና ጊዜያዊ የሥራ ዕድሎች ተፈጥረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም 42 የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ተደራጅተው የሥራ ትስስር ተፈጥሯል፡፡

በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ በኩል ለህብረተሰቡ ተሳትፎ እና የልማት ሥራዎች ብር 287 ሚሊዮን 680 ሺህ 068 ብር ወጪ ተደርጓል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *