• +251115526653
  • info@etsugar.com
  • Phillips Building, Chad St, Addis Ababa, Ethiopia
ፕሮጀክቶች
ተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ

ተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ

በአዋሽ ተፋሰስ ዝቅተኛ አካባቢ በአፋር ክልል በሁለት ምዕራፍ በሚለማ በ50 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሚለማ የሸንኮራ አገዳን በግብዓትነት የሚጠቀመው የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ከአዲስ አበባ በ670 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ በግዙፍነቱ ከተቀሩት ነባር ስኳር ፋብሪካዎች የሚለየው ይህ ፋብሪካ ከሀገሪቱ መዲና አዲስ አበባ በስተምስራቅ ወደ ጅቡቲ የሚወስደውን መንገድ ተከትሎ ከጅቡቲ ወደብ በ300 ኪ.ሜ ርቅት ላይ ይገኛል፡፡ ይህም ወደፊት የፋብሪካውን ምርት ወደ ውጭ ለመላክ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ተብሎ ይታመናል፡፡

በ1998 ዓ.ም. የፕሮጀክት ሥራው የተጀመረው የግዙፉ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ይዞታ የመስኖ ውኃ ግድቡን ጨምሮ በሚሌ፣ በዱብቲ፣ በአሳኢታ እና በአፋምቦ ወረዳዎች ውስጥ ይገኛል፡፡ OIA (Overseas Infrastructure Alliance) በተባለ የህንድ ኩባንያ የተገነባው ይህ የመጀመሪያው ምዕራፍ ፋብሪካ የሙከራ ምርት ከጀመረበት ጥቅምት 2007 ዓ.ም ጀምሮ በአካባቢው ከተከሰተው ድርቅ እና በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሔደ ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ ሥራው እስኪቋረጥ ድረስ በሙከራ የምርት ሒደት ላይ ይገኝ ነበር፡፡

ምቹ ሁኔታዎች ኖረው ወደፊት ፋብሪካው ሙሉ የማምረት አቅሙ ላይ ሲደርስ በቀን 13 ሺ ቶን አገዳ በመፍጨት በዓመት 3 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ ስኳር ያመርታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በተጨማሪም ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር ከሚያመነጨው 60 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ውስጥ 38 ሜጋ ዋቱን ለራሱ በመጠቀም ቀሪውን ለብሔራዊ የኃይል ቋት በማስገባት እንዲሁም 27 ሚሊዮን ሊትር ያህል ኤታኖል በማምረት ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውን እንደሚያረጋግጥ ይታመናል፡፡

ለመጀመሪያው ምዕራፍ ፋብሪካ የሚቀርበውና በ25 ሺ ሄክታር መሬት ላይ የሚለማው የሸንኮራ አገዳ በፋብሪካው የሚለማ ሲሆን፣ በሁለተኛው ምዕራፍ ሊገነባ ለታቀደውና በቀን 13 ሺህ ቶን አገዳ ለሚፈጨው ፋብሪካ የሚቀርብ በተጨማሪ 25 ሺህ ሔክታር መሬት ላይ የሚለማው የሸንኮራ አገዳ ደግሞ በአካባቢው በሚገኙ አገዳ አብቃይና አቅራቢ አርብቶ አደሮች (አውትግሮወር) የሚለማ ይሆናል ተብሎ ታሳቢ ተደርጓል፡፡

ፋብሪካው ምርት እስካቋረጠበት ጊዜ ድረስ የአገዳ ልማቱ ይከናወን የነበረው በአዋሽ ወንዝ ላይ በተገነባው የተንዳሆ ግድብ አማካይነት ነው፡፡ ከ1.86 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ በላይ የመያዝ አቅም ያለው ይህ ግድብ 60 ሺ ሄክታር መሬት የማልማት አቅም አለው፡፡

ፋብሪካው በመስኖ የሚለማ መሬት ለአካባቢው አርብቶ አደሮች በማመቻቸቱም አርብቶ አደሩ ወደ ከፊል አርሶ አደርነት መሸጋገር የቻለበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሎ ነበር፡፡

የመስኖ መሠረተ ልማት ግንባታ

ከ42 ኪ/ሜ በላይ የዋና ቦይና ተያያዥ ስትራክቸሮች ግንባታ ተከናውኗል፤

22,835 ሄ/ር መሬት ውሃ ገብ ተደርጓል፤

  የአገዳ ልማት

ፋብሪካው በድርቅ ምክንያት ሥራ እስኪያቆም ድረስ 17,683 ሄክታር መሬት በአገዳ ተሸፍኖ ነበር፤

  የቤቶች ግንባታ

8,997 የመኖሪያ ቤቶች እና 146 አገልግሎት መስጫ ብሎኮች ተገንብተው አገልግሎት ሲሰጡ ቆይተዋል፤

  የማኀበረሰብ ተጠቃሚነት

የፕሮጀክቱ ሥራ እስከ ተቋረጠበት ጊዜ ድረስ በፕሮጀክቱ፣ በኮንትራክተሮች እንዲሁም በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች አማካይነት 77,035 ለሚሆኑ ዜጎች በቋሚ፣ በኮንትራትና በጊዜያዊነት የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸው ነበር፡፡ 84 የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችም ተደራጅተው በሥራ ላይ ነበሩ፡፡

እንዲሁም በአካባቢው የሚገኙ አርብቶ አደሮችን የልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ በዱብቲ 1,667 አባላት ያሏቸውና ህጋዊ ሰውነት ያገኙ 16 የሸንኮራ አገዳ አምራቾች መሰረታዊ የህብረት ሥራ ማህበራት ከፋብሪካው ጋር በአውትግሮወር ሞዳሊቲ ትስስር በመፍጠር ሸንኮራ አገዳ በማምረት ላይ የነበሩ ሲሆን ለህብረተሰቡ ተሳትፎ እና የልማት ሥራዎች የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ 1.60 ሚሊዮን ብር ገደማ ወጪ ተደርጓል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *