• +251115526653
  • info@etsugar.com
  • Phillips Building, Chad St, Addis Ababa, Ethiopia
ዜናዎች
በለውጡ ሂደት የተመዘገቡ ስኬቶችን ይበልጥ ለማጎልበት ሠራተኛው የማይተካ ሚና እንዳለው ተገለጸ

በለውጡ ሂደት የተመዘገቡ ስኬቶችን ይበልጥ ለማጎልበት ሠራተኛው የማይተካ ሚና እንዳለው ተገለጸ

የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ሠራተኛ በአገሪቱ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተመዘገቡ ስኬቶችን በሚገባ ተገንዝቦ ስኬቶቹን የበለጠ ለማጎልበት የማይተካ ሚና እንዳለው ተገለጸ፡፡

ይህ የተገለጸው መጋቢት 28 ቀን 2015ዓ.ም “ድሎችን የማጽናትና ፈተናዎችን የመሻገር ወቅታዊና ታሪካዊ የሠራተኛው ተልዕኮ” በሚል ርዕስ በተዘጋጀ ሰነድ ላይ በኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ዋና መስሪያ ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውይይት በተደረገበት ወቅት ነው፡፡

የግሩፑ ሠራተኛ ባለፉት አምስት ዓመታት የተመዘገቡ ስኬቶችን ተገንዝቦና ስኬቶቹን የበለጠ አጠናክሮ ለማስቀጠል ግብዓት መስጠትና ራሱን የስኬቱ አካል ማድረግ እንደሚገባውም ነው በውይይቱ ወቅት የተነሳው፡፡

ለውይይት የተዘጋጀውን መነሻ ሰነድ ያቀረቡት የግብይት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታፈሰ አሰፋ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ሠራተኛው የመንግስትን ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ተገንዝቦ በብቃት ለመፈጸም እንዲችል የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት መፍጠር ይጠበቅበታል፡፡

ሠራተኛው አገሪቱን እየገጠማት ያለውን ውስጣዊና ውጫዊ ተግዳሮቶችን በብቃት ተሻግሮ አገራዊ ርዕይን ከግብ ለማድረስ መስራት እንደሚኖርበት ነው አቶ ታፈሰ የጠቆሙት፡፡

አገሪቱ ባሳለፈቻቸው አምስት የለውጥ ዓመታት የፖለቲካ ምህዳሩ መስፋቱን፣ ምጣኔ ሀብቱን ከፍጹም ውድቀት መታደግ መቻሉን፣ ልማትና እድገትን ማስቀጠል መቻሉን፣ የአገሪቱን ሉዓላዊነትና አንድነት ማስከበር መቻሉን፣ ውጤታማ ዲፕሎማሲያዊ ተግባራት መከናወናቸውንና ማህበራዊ ትስስርና የዜጎችን ክብር ከፍ ያደረጉ ተግባራት መከናወናቸውን አብራርተዋል፡፡

በለውጥ ዓመታቱ ከላይ የተዘረዘሩት ስኬቶች ቢመዘገቡም በርካታ ተግዳሮቶች መኖራቸውንም አቶ ታፈሰ ገልጸዋል፡፡ ከነዚህም መካከል አቅምን አሟጦ ያለመጠቀም፣ የተጠያቂነት ማነስ፣ የሠራተኛው የሥነ ምግባር ብልሹነት፣ የኑሮ ውድነት፣ ሥራ አጥነት፣ በተደጋጋሚ የሚከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎች፣ ያልሰለጠነ የፖለቲካ ባህልና ከታሪክ የተወረሱ አሉታዊ ጎኖችና ሌሎችም መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ከነዚህ ፈተናዎች ለመውጣት ሥራ አጥነትን መቀነስ፣ የኑሮ ውድነት ጫናን ለመቅረፍ መረባረብ፣ አገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል እንደሚገባም ነው ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው የገለጹት፡፡

ለውይይት መነሻነት በተዘጋጀው ሰነድ ላይ ለቀረቡ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ምላሽና ማጠቃለያ የሰጡት የግሩፑ የሰርቪስ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አብርሃም ደምሴ በበኩላቸው አገር ግንባታ ለአንድ የተወሰነ አካል ብቻ የተሰጠ ባለመሆኑ በአገር ግንባታው ሂደት የግሩፑ ሠራተኛም የራሱን አስተዋጽዖ ማድረግ ይጠበቃበታል ብለዋል፡፡

በተጨባጭ መረጃና ማስረጃ ላይ ተመስርቶ በየደረጃው ተጠያቂነትን ለማስፈን እርምጃዎች መወሰድ መጀመራቸውን የጠቆሙት አቶ አብርሃም ይህ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስረድተዋል፡፡

ተጠያቂነትን ይበልጥ ለማስፋትም መንግስት የሽግግር ጊዜ ፍትሕ ስርዓት ለመዘርጋት እየሰራ መሆኑንም ገልልጸዋል፡፡

የኑሮ ውድነት ጫና ውስጣዊና ውጫዊ መንስኤዎች እንዳሉት የጠቆሙት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው ችግሩን ለመቅረፍ መንግስት ከሚወስዳቸው የማስተካከያ እርምጃዎች በተጨማሪ ሠራተኛው ህገ ወጥ ደላሎችን፣ ምርት የሚደብቁ ሕገ ወጦችን፣ ኮንትሮባንዲስቶችና የምጣኔ ሀብት አሻጥር የሚፈጥሩ ሕገ ወጦችን በመጠቆም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ሠራተኛ ለአገሪቱ የውስጥ ጥንካሬ የሚያግዝ ግብዓት በመስጠት የጥንካሬው አካል መሆን ይገባዋል ያሉት አቶ አብርሃም ከዚህ ባሻገር ሠራተኛው በተሰማራበት የሙያ መስክ የሚሰጠውን አገልግሎትና የሚያመርተውን ምርት ብዛትና ጥራት ለማሳደግ ጠንክሮ በመስራት የግሩፑን ዕቅድ ለማሳካት ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባውም አስገንዝበዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *