• +251115526653
  • info@etsugar.com
  • Phillips Building, Chad St, Addis Ababa, Ethiopia
ዜናዎች
የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ እንደ ንግድ ተቋም

የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ እንደ ንግድ ተቋም

 

የቀድሞው ስኳር ኮርፖሬሽን በሕግ ፈርሶ የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ እንደ አንድ የንግድ ተቋም በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሚኒስተሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 500/2014 ሲቋቋም የስኳር ፋብሪካዎች እና ፕሮጀክቶች ላይ መሠረታዊ የአደረጃጀት ለውጥ አስከትሏል

በዚሁ መሠረታዊ የአደረጃጀት ለውጥ መሠረትም አምስት ስኳር ፋብሪካዎች ማለትም ወንጂ/ሸዋ፣ መተሐራ፣ ከሰም፣ ፊንጫኣ እና ጣና በለስ ስኳር ፋብሪካዎች እራሳቸውን ችለው እንዲቋቋሙና በእራሳቸው ሥራ አመራር ቦርድ እንዲመሩ ተደርጓል፡፡  በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ስር እንዲተዳደሩ የተደረጉት ደግሞ ወደ ምርት የገቡትንና በፕሮጀክት ደረጃ ታሳቢ የተደረጉትን የኦሞ ኩራዝ ቁጥር ሁለት እና ሦስት እንዲሁም የአርጆ ዲዴሳ ስኳር ፋብሪካዎች ሲሆኑ ግሩፑ ግንባታቸው በተለያዩ ደረጃዎች ላይ ደርሶ ተቋርጠው የሚገኙ የኦሞ ኩራዝ ቁጥር አንድ ፣ ኦሞ ኩራዝ ቁጥር አምስት፣ ተንዳሆ እና ወልቃይት የስኳር ፕሮጀክቶችንም እያስተዳደረ ይገኛል፡፡

የተደረገው አደረጃጀት ለውጥም ከዋናው መስሪያ ቤት የጀመረ ሲሆን በዚህም የምርምርና ልማት ዘርፍን ጨምሮ በዋና መስሪያ ቤት በግሩፑ ስር በሚገኙ ፋብሪካዎችና ፕሮጀክቶች ከ46 በመቶ በላይ የሆነ የሰው ኃይል እንዲቀነስ ተደርጓል፡፡ በተመሳሳይም በግሩፑ ስር በሚገኙ ፕሮጀክቶችም ለሥራ ከሚያስፈልገው በላይ ያለ የሰው ኃይል እንዲቀነስ ተደርጓል፡፡ ለዚህ ገፊው ምክንያትም ምርታማነት በመቀነሱ እና በውጤታማነት ደረጃ ሲታይም አዋጭ ባለመሆኑ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ በአመዛኙ የንግድ ተቋም ሆኖ በአዲስ ተልዕኮና አደረጃጀት እንደመመስረቱም ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ተቋሙ አትራፊ ሆኖ መቀጠል የሚችልበትን ሁኔታ ዕውን የሚያደርጉ በርካታ የለውጥ እርምጃዎችን ወስዷል፡፡ በዚሁ መሠረትም፡-

  • ተቋሙ ተልዕኮውን ለመከወን የሚያስችለውን አዲስ አደረጃጀት ቀርፆ እና በተመጠነ የሰው ኃይል ተደራጅቶ በመስራት ላይ ይገኛል፣
  • በኦሞ ኩራዝ በፕሮጀክት ደረጃ የሚገኙትን የኦሞ ኩራዝ ቁጥር ሦስት ስኳር ፋብሪካንና ግንባታው ተቋርጦ የሚገኘውን የኦሞ ኩራዝ ቁጥር አንድ ስኳር ፕሮጀክትን የሀብት አስተዳደር ውጤታማነትን ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ በአንድ አስተዳደር ስር እንዲመራ ተደርጓል፣
  • የኦሞ ኩራዝ ሁለት ስኳር ፋብሪካ እና ግንባታው ተቋርጦ የሚገኘው የኦሞ ኩራዝ ቁጥር አምስት ስኳር ልማት ፕሮጀክት ከርቀታቸው አንጻር በአንስ አስታዳደር ማደራጀት በለመቻሉ እያንዳንዳቸው ለየብቻ እንዲደራጁ በማድረግ የተመጠነ የሰው ኃይል እንዲኖራቸው አድርጓል፣
  • ግሩፑን አንደ ንግድ ተቋም አትራፊ ሆኖ እንዲቀጥል የሚያስችሉ ከ13 በላይ መመሪያዎችና ከ12 በላይ ማኑዋሎች ተዘጋጅተውና በስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ሥራ አመራር ቦርድ ጽድቀው ሥራ ላይ እንዲውሉ ተደርጓል፣
  • ከሰባት ዓመት በፊት ባጋጠመ ድርቅ ሳቢያ የሸንኮራ አገዳ ማሳው በመውደሙና ይህንኑ ተከትሎ ሥራ ያቆመው የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ከፍተኛ ዘረፋ እና ወድመት የደረሰበት በመሆኑ ከ500 በላይ የፋብሪካውን ሠራተኞች እንደየሙያቸው በሌሎች ስኳር ፋብሪካዎችና ፕሮጀክቶች በመመደብ ቀሪዎችን ከ1ሺህ ሁለት መቶ ሰማንያ አምስት በላይ ሠራተኞች በአለው የአሰራር ሕግ መሠረት የማስጠንቀቂያ ጊዜ በመስጠት አሰናብቷል፣
  • ከኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ መመስረት ጋር በተያያዘ በተከናወነ የሪፎርም ሥራም አዋጭ ያልሆኑ ፕሮጀክቶች  እንዲቆሙ ከመንግስት እና ከቦርድ በተሰጠው አቅጣጫ መሠረት የአዋጭነት ግምገማ ተደርጎ ካለው የሀብት እና ኤኮኖሚያዊ አዋጭነት ውስንነት የተነሳ የወልቃይት፣ ኦሞ አንድ፣ ኦሞ አምስት እና  የተንዳሆ ስኳር ፕሮጀክቶች  አዋጭ ባለመሆናቸው ለጊዜው እንዲቆሙ በግሩፑ ማኔጅመንትና በስራ አመራር ቦርድ  ተወስኗል፣
  • በተያያዘም በፕሮጀክት ደረጃ የነበረውና በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በነበረው ጦርነት ምክንያት ሥራው የተቋረጠው የወልቃይት ስኳር ልማት ፕሮጀክትን በተመለከተ የፕሮጀክቱን ሥራ ለማስቀጠል ባለመቻሉ ከዋናው መስሪያ ቤት (ከቀድሞው ስኳር ኮርፖሬሽን) የተውጣጡ የሥራ ኃላፊዎች በአካባቢው የጸጥታ ችግር በነበረበት ሁኔታ በአራት የፕሮጀክት ሳይቶች በመገኘትና የፕሮጀክቱ ሠራተኞች እንዲመዘገቡ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ጥሪ በማድረግ በአካል ተገኝተው መመዝገብ የቻሉትን በተለያዩፋብሪካዎችና ፕሮጀክቶች የመመደብ ሥራ ተሰርቷል፡፡ አሁን ላይም በተለያዩ ስኳር ፋበሪካዎችና ፕሮጀክቶች ተመድበው በስራ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይሁንና በወቅቱ ተገኝተው ያልተመዘገቡት እንዲመዘገቡ የሚያስገነዝብ ማስታወቂያ በተለያዩ መንገዶች የተላለፈ ሲሆን ይሀን ያልፈጸሙት ደግሞ በራሳቸው ፈቃድ ሥራቸውን እንደለቀቁ እንደሚቆጠር ተላልፎ በነበረው ማስታወቂያ መሰረት በወቅቱ እንዲሰናበቱ ተደርጓል፡፡

በኋላም መስሪያ ቤቱ (የቀድሞው ስኳር ኮርፖሬሽን) በሕግ ፈርሶ በአዲስ ስያሜና ተልዕኮ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ በአዲስ መልክ መደራጀቱን ተከትሎ የወልቃይት ፕሮጀክትን! በሚከታተሉ ሦሥት ሰዎች ብቻ እንዲደራጅ በኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ማኔጅመንትና በስራ አመራር ቦርድ ተወስኖ ተግባራዊ ተደርጓል፡፡

በፌዴራል መንግስት በኩልም በአገሪቷ ካሉት ስኳር ፋብሪካዎችና ፕሮጀክቶች መካከል ስምንት ፋብሪካዎችና ፕሮጀክቶች ወደግል ባለሀብቶች እንዲዛወሩ ለማድረግ በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል ለባለሀብቶች ጥሪ ተደርጎ ወደግል የማዛወሩ ሥራ በሂደት ላይ ይገኛል፡፡

1 thought on “የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ እንደ ንግድ ተቋም

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *