• +251115526653
  • info@etsugar.com
  • Phillips Building, Chad St, Addis Ababa, Ethiopia
ዜናዎች
ቋሚ ኮሚቴው ከሠራተኛውና ከተቋሙ ማኔጅመንት ጋር ተወያየ

ቋሚ ኮሚቴው ከሠራተኛውና ከተቋሙ ማኔጅመንት ጋር ተወያየ

* ማዕከላዊ የስኳር መጋዘን እና የዋና መስሪያ ቤት ሕንጻ ግንባታን ጎብኝቷል

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት የልማት ድርጅቶች አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ ከኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ሠራተኞችና ከተቋሙ ከፍተኛ አመራር ጋር ውይይት አድርጓል፡፡ ቋሚ ኮሚቴው ቃሊቲ የሚገኘውን የስኳር ማዕከላዊ መጋዘንና በግንባታ ላይ የሚገኘውን የግሩፑን የወደፊት ዋና መስሪያ ቤት የሕንጻ ግንባታ ሂደትን ጎብኝቷል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊ ሠራተኞች ቋሚ ኮሚቴው ተቋሙ ካለበት የገንዘብ እጥረት፣ የጸጥታ ችግር፣ የመሠረተ ልማት ገንቢ ተቋማት ተናበው አለመስራት እና ከመሬት ይዞታ ጋር ተያይዘው ያሉ ችግሮችን በመፍታት ረገድ እገዛ ሊያደርግ እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡

ተቋሙ ካለበት ችግር ለመውጣት በራሱ ከሚያደርገው ጥረት በተጨማሪ ቋሚ ኮሚቴው በመሠረተ ልማት ዝርጋታ እና ጸጥታን በማስጠበቅ ረገድ ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡

የግሩፑ መሠረታዊ ሠራተኛ ማሕበር ሊቀመንበር አቶ ጋዲሳ ደሳለኝ ማህበሩ የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ውጤታማነት በቀጥታ የሠራተኛውን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ በመሆኑ በዕቅድ ዝግጅት እና አፈጻጸም ግምገማ ላይ በንቃት እንደሚሳተፍ አብራርተዋል፡፡

የስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ የሠራተኞች መሠረታዊ ማሕበር ከእቅድ ዝግጅትና አፈጻጸም ግምገማ በተጨማሪ በሠራተኞች ቅጥር፣ እድገትና ዝውውርና በመሳሰሉት አስተዳደራዊ ጉዳዮችም ከተቋሙ ጋር በቅርበት እንደሚሰራ አቶ ጋዲሳ አስረድተዋል፡፡

ለረዥም ጊዜያት የዘለቁ ችግሮች ተቋሙን ወደኋላ ሲጎትቱት መቆየታቸውን የተናገሩት ሊቀመንበሩ በተቋሙ የስራ አመራር ቦርድ ድጋፍና ተቋሙ በጀመራቸው የሪፎርም ሥራዎች አማካይነት ከችግሮቹ ለመውጣት ጥረት በመደረግ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መሐመድ አብዶ ከሠራተኞች ጋር በነበረው ውይይት ማጠናቀቂያ ላይ በሰጡት አስተያየት ሠራተኛው ከራሱ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ይልቅ በባለቤትነትና በቁጭት ተቋሙን ለመለወጥ የሚያስችሉ ጥያቄዎችን ሲያነሳ በመስማታቸው ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል፡፡

ከሠራተኛው ለተነሱት ጥያቄዎች ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመነጋገር በተቻለ መጠን መፍትሔ እንዲያገኙ ቋሚ ኮሚቴው እንደሚሰራ አብራርተዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ከግሩፑ ማኔጅመንት ጋር በነበረው ውይይትም ተቋሙን ወደውጤታማነት ለመመለስ ሠራተኛውና ማኔጅመንቱ በአንድ ዓይነት አመለካከትና አረዳድ ላይ እንደሚገኝ መገንዘባቸውን የቋሚ ኮሚቴው አባላት በውይይቱ ማጠቃለያ በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል፡፡

ሠራተኛው ከኢኮኖሚያዊና የጥቅማ ጥቅም ጥያቄዎችን ከማንሳት ይልቅ ተቋሙን ከችግር ለማውጣት ከተለያዩ አካላት ለተቋሙ ሊደረግ ስለሚገባው ድጋፍ ከማኔጅመንቱ ባልተናነሰ ማንሳቱ ለተቋሙ ያለውን ተቆርቋሪነት አመላካች ነው ብለዋል የቋሚ ኮሚቴው አባላት፡፡

በማህበሩ፣ በሠራተኛውና በማኔጅመንቱ መካከል ያለው ጥምረት ገንቢና የሚበረታታ መሆኑንና ለሌሎችም የልማት ድርጅቶች አርዓያ መሆኑን ኮሚቴው አንስቶ በእንዲህ ያለ የአመለካከትና የአስተሳሰብ አንድነት ተቋሙ ረጅም በማይባል ጊዜ ውስጥ ካለበት ችግር መውጣት እንደሚችል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

በተያያዘ ዜና ቋሚ ኮሚቴው ቃሊቲ የሚገኘውን የስኳር ማዕከላዊ መጋዘንና በግንባታ ላይ የሚገኘውን የግሩፑን የወደፊት ዋና መስሪያ የሕንጻ ግንባታ ሂደትን ጎብኝቷል፡፡

በማዕከላዊ መጋዘን ጉብኝት ወቅት የግብይት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታፈሰ አሰፋ ከፋብሪካ አንስቶ እስከ ተጠቃሚዎች ያለውን የስኳር ስርጭት ሰንሰለት ምን እንደሚመስል ሰፊ ገለጻና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የዋና መስሪያ ቤት ሕንጻ ግንባታን የተመለከተው ቋሚ ኮሚቴው ተቋሙ ተጨማሪ ሀብት ለመፍጠርና ገቢ ለማግኘት እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ የሚበረታታ መሆኑንና ግንባታውም በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ እንደሚገኝ መረዳቱን አስታውቋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *