
ወልቃይት ስኳር ልማት ፕሮጀክት
የፕሮጀክቱ ጽ/ቤት ከአዲስ አበባ በ1 ሺ 30 ኪ.ሜ ርቀት ወልቃይት ወረዳ ይገኛል፡፡ፕሮጀክቱ ከእርሻ ልማቱ ጋር በተገናኘ በ40 ሺ ሄክታር መሬት ላይ የሚለማ የሸንኮራ አገዳን በግብዓትነት ተጠቅሞ በቀን 24 ሺ ቶን አገዳ የመፍጨት አቅም ያለው ይህ ፋብሪካ CAMC በተባለ የቻይና ኩባንያ እየተገነባ ነበር፡፡
በዚህ መሰረት ፋብሪካው በሁለት ምዕራፍ እየተገነባ የነበረ ሲሆን በአገራችን ሰሜናዊ ክፍል ከተፈጠረው የጸጥታ ችግር ጋር ተያይዞ የፕሮጀክት ሥራው በአሁኑ ወቅት ተቋርጦ ይገኛል፡፡ የፕሮጀክት ሥራው እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስም የፋብሪካ፣ የግድብ እና የመስኖ አውታር ግንባታ ሥራው ወደ 80 በመቶ ደርሶ የነበረ ፕሮጀክት ነው፡፡ የፋብሪካው የግንባታ ሥራ ተጠናቆ ሙሉ የማምረት አቅሙ ላይ መድረስ ቢችል በዓመት 4 ሚሊዮን 840 ሺ ኩንታል ስኳር እና 41 ሚሊዮን 654 ሊትር ኢታኖል ያመርታል ተብሎ ታሳቢ ተደርጎ የተጀመረ ፕሮጀክት ነው፡፡
በፕሮጀክቱ በሁለት ምዕራፍ ተከፍሎ ሲከናወን የነበረው የፋብሪካ ግንባታ ሥራ የፋብሪካ ቁጥር አንድ 93% እንዲሁም የፋብሪካ ቁጥር ሁለት 85% ደርሶ ነበር፡፡ የፋብሪካ ግንባታ ሥራው ተጠናቆ ወደፊት ወደ መደበኛ ምርት ሲገባ ለአገዳ ልማት የሚያስፈልገውን የመስኖ ውሃ አቅርቦት ከተከዜ፣ ከቃሌማ እና ከዛሬማ ወንዞች እንዲያገኝ ታሳቢ ተደርጎ የተገነባ ነው፡፡
የመስኖ መሠረተ ልማት ግንባታ
3.5 ቢሊየን ሜትር ኩብ ውሃ የመያዝ አቅም ይኖረዋል ተብሎ የታቀደው “የሜይ-ዴይ” ግድብ የአገራችን ሰሜናዊ ክፍል ጦርነት እስኪቀሰቀስ ድረስ በዛሬማ ወንዝ ላይ ሲገነባ የቆዬ ሲሆን ግድቡ ወደፊት ሲጠናቀቅም 840 ሜትር ስፋት እና 152 ሜትር ቁመት ይኖረዋል፤
ከግድብ ግንባታው ጎን ለጎን በጠብታ መስኖ 7 ሺ ሄ/ር መሬት ለማልማት NETAFIM ከተባለ የእስራኤል ኩባንያ የመስኖ መሠረተ ልማት ሥራ ተቋራጭ ጋር ውል ተገብቶ የፕሮጀክት ሥራው እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስ የሸንኮራ አገዳ ልማቱ ሲከናወን የቆዬ በመሆኑ የ10 ኪሎ ሜትር የዋና ቦይ ግንባታ በፕሮጀክቱ ተጠናቆ ነበር፡፡
በተጨማሪም 3 ሺ ሄ/ር መሬት ከቃሌማ ወንዝ በፓምፕ ተጠልፎ በስፕሪንክለር የመስኖ ዘዴ የአገዳ ልማቱን ለማከናወን የግንባታ ሥራው ሲከናወን የነበረ ሲሆን የመስኖ ውሃው እስከሚደርስ ድረስም በፕሮጀክቱ የጥጥ ልማት ሲከናወን ነበር፡፡ እንዲሁም በ260 ሄ/ር መሬት ላይ የመስኖ መሰረተ ልማቱን በማጠናቀቅ የዘር አገዳ ልማት ሲያከናውን ነበር፡፡
የቤቶች ግንባታ
ፕሮጀክቱ 1,038 መኖሪያ ቤቶችና 57 የአገልግሎት መስጫ ብሎኮች ተገንብተው ለአገልግሎት በቅተው የነበረበት ፕሮጀክት ነው፡፡
የማህበረሰብ ተጠቃሚነት
የአካባቢው ህብረተሰብ ልማቱ በሚፈጥረው የሥራ እድል ተሳታፊና ተጠቃሚ መሆን እንዲችል የመለስተኛ ሙያ ክህሎት ሥልጠናዎች ተሰጥተው ለ84 ሺ 659 የአካባቢው ወጣቶችና ዜጎች ፕሮጀክቱ እስኪቋረጥ ድረስ የቋሚ፣ ኮንትራትና ጊዜያዊ የሥራ ዕድሎች ተፈጥሮላቸው ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪም 161 የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች እንዲደራጁና በሥራ እንዲተሳሰሩ ድጋፍ ተደርጎም ነበር፡፡
በሌላ በኩል በልማቱ ምክንያት ተነሺ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የሃብት ንብረት ግምት ካሳ እና የምርት ማካካሻ ካሳ ክፍያ ተፈጽሞላቸዋል፡፡ በመጀመሪያው ዙር ወደ ቆራሪት ሰፈራ መንደር ለተቋቋሙ 2 ሺ 621 የህብረተሰብ ክፍሎች ስምንት የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት (ት/ቤቶች፣ የሰውና እንስሳት ህክምና መስጫ ተቋማት፣ የአርሶ አደሮች ማሰልጠኛ ወዘተ)፣ 14 የመጠጥ ውሃ ተቋማትና 62 ኪሎ ሜትር መንገድ ተገንብቶላቸው የፕሮጀክት ሥራው እስኪቋረጥ ድረስ አገልግሎት እንዲያገኙ ሲደረግ ቆይቷል፡፡
በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ በኩል በፕሮጀክቱ አከባቢ ለሚኖረው ህብረተሰብ የልማት ሥራዎች የዋለ 407.68 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል፡፡