
ኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 ስኳር ፋብሪካ
የኦሞ ወንዝን በሚያዋስኑ በካፋና ቤንች ማጂ ዞኖች የሚገኘው የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 ስኳር ፋብሪካ ከአዲስ አባባ 874 ኪ.ሜ ይርቃል፡፡ ፋብሪካው ጥቅምት 4 ቀን 2011 ዓ.ም. በኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ ተመርቆ ሥራ ጀምሯል፡፡
የፋብሪካው ግንባታ በይፋ የተጀመረው መጋቢት 2 ቀን 2008 ዓ.ም ከቻይና ልማት ባንክ በተገኘ ከ8 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ነው፡፡ ኮምፕላንት በተባለ የቻይና ኩባንያ የተገነባው ይህ ፋብሪካ በዲዛይኑ መሠረት በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር በቀን 12,000 ኩንታል ስኳር የማምረት አቅም ያለው ግዙፍ ፕሮጀክት ነው፡፡ እጅግ ዘመናዊ ከመሆኑ አንጻርም የአለም ገበያ ፍላጎትን መሰረት በማድረግ ጥሬ ስኳር (Raw sugar)፣ ነጭ ስኳር (Plantation white sugar) እና የተጣራ ስኳር (Refined sugar) ማምረት ይችላል፡፡
የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 ስኳር ፋብሪካ ወደ ሥራ መግባት ስኳር የሚያመርቱትን ፋብሪካዎች ቁጥር ወደ ስምንት (ወንጂ ሸዋ፣ መተሐራ፣ ፊንጫአ፣ ከሰም፣ ጣና በለስ፣ አርጆ ዲዴሳ፣ ኦሞ ኩራዝ ቁጥር 2 እና 3) አድርሶታል፡፡
በፋብሪካው ከ2 ሺህ 588 በላይ ዜጎች የቋሚ፣ ኮንትራትና ጊዚያዊ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ሲሆን 419 አነስተኛ ማኅበራት ተደራጅተው በንግድና ሌሎች ተያያዥ የሥራ መስኮች የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸው ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡