• +251115526653
  • info@etsugar.com
  • Phillips Building, Chad St, Addis Ababa, Ethiopia
ፋብሪካዎች
ወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ

ወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ

ወንጂ/ሸዋ ስኳር ፋብሪካ በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ አቅራቢያ ከአዲስ አበባ 110 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ በሀገራችን የስኳር ፋብሪካ ታሪክ ፋና ወጊ የሆነው የመጀመርያ የሆነው የወንጂ ስኳር ፋብሪካ በ1946 ዓ.ም. ግንባታው ተጠናቆ ማምረት የጀመረ ሲሆን፣ የሸዋ ስኳር ፋብሪካ ደግሞ እዛው ወንጂ ላይ በ1955 ዓ.ም. ተመርቆ ስራ የጀመረ ሌላኛው ስኳር ፋብሪካ ነው፡፡ ሁለቱም ስኳር ፋብሪካዎች ኤች ቪ ኤ በተባለ የሆላንድ ኩባንያ የተገነቡና በኩባንያውና በመንግሥት የጋራ ባለቤትነት በሽርክና የተቋቋሙ ነበሩ፡፡

በአንድ አስተዳደር ስር እየተዳደሩ ስኳር ያመርቱ የነበሩት ሁለቱ አንጋፋ ፋብሪካዎች በእርጅና ምክንያት ሥራቸውን እስካቆሙበት ጊዜ ማለትም ወንጂ እስከ 2004 ዓ.ም. እንዲሁም ሸዋ እስከ 2005 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ የነበራቸው አማካይ አመታዊ ስኳር የማምረት አቅም 75 ሺህ ቶን ወይም 750 ሺህ ኩንታል ነበር፡፡

ነባሩን የወንጂ/ሸዋ ስኳር ፋብሪካ በአዲስና ዘመናዊ ፋብሪካ ለመተካት የማስፋፊያ ፕሮጀክት በፋብሪካ እና በእርሻ ዘርፍ ተከናውኖ እና አዲስ ፋብሪካ የመገንባት ስራው በ2005 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ተጠናቆ በ2006 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ ፋብሪካው ስራ ጀመረ፡፡ አዲሱ ስኳር ፋብሪካ የተገነባው ነባሮቹ በሚገኙበት የኦሮሚያ ክልል ምስራቅ አርሲ ዞን ዶዶታ ወረዳ ቢሾላ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነው፡፡

ከአዲስ አበባ በ110 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኘው ይህ ፋብሪካ በመጀመሪያ ምዕራፍ በቀን 6 ሺህ 250 ቶን አገዳ በመፍጨት በዓመት ከ1 ሚሊዮን 749 ሺህ 46 ኩንታል በላይ ስኳር የማምረት አቅም አለው፡፡ ወደፊት የማምረት አቅሙን በሂደት በማሳደግም በቀን ወደ 12 ሺህ 500 ቶን አገዳ እየፈጨ ዓመታዊ የስኳር ምርት መጠኑን እስከ 2 ሚሊዮን 207  ሺህ ኩንታል እንደሚያሳድግ ታሳቢ ተደርጎ የተገነባ ነው፡፡

ይህ ዘመናዊ የስኳር ፋብሪካ ወደፊት የኢታኖል ፋብሪካ ሲኖረውም ሞላሰስ ከተሰኛው ተረፈ ምርቱ 10 ሺህ ሜትር ኪዩብ ኢታኖል ያመርታል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ወደፊት በዓመት እስከ 12 ሚሊዮን 800 ሺህ ሊትር የሚደርስ ኤታኖል ለማምረት የሚያስችል የኤታኖል ፋብሪካ ለመገንባት ታቅዷል፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ረገድም 31 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት 11 ሜጋ ዋቱን ለራሱ ተጠቅሞ፣ ቀሪውን 20 ሜጋ ዋት ለብሔራዊ የኃይል ቋት እያስገባ ይገኛል፡፡

የፋብሪካው የአገዳ እርሻ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ዋቄ ጢዮ፣ዶዶታ እና ወለንጪቲ ተብለው በሚታወቁ አካባቢዎች እየተካሄደ ይገኛል፡፡ የእርሻ ማስፋፊያ ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ አዲሱ ፋብሪካ የአገዳ አብቃይ ገበሬ ማኅበራት ማሳን ጨምሮ በአጠቃላይ 16 ሺ ሄክታር የሸንኮራ አገዳ መሬት ይኖረዋል ተብሎ ታሳቢ ተደርጓል፡፡

በፋብሪካው በአጠቃላይ ከለማው 12 ሺ 800 ሄክታር የሸንኮራ አገዳ መሬት ውስጥ 7 ሺ ሄክታሩ በፋብሪካው አካባቢ በሚገኙ በ31 የሸንኮራ አገዳ አብቃይና አቅራቢ ማኀበራት በታቀፉ 9 ሺ 319 አርሶ አደሮች  የለማ ነው፡፡ በዚህም አባላቱ በሚያገኙት ከፍተኛ ገቢ ከልማቱ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

ፋብሪካው ለአርሶ አደሮቹ በመስኖ የለማ መሬት በማዘጋጀት፣ የምርጥ ዘር አቅርቦት በማመቻቸት፣ ሙያዊና ቴክኒካዊ ድጋፍ በመስጠት አገዳ አብቃይ አርሶ አደሮቹ ሸንኮራ አገዳ አልምተው ለፋብሪካው በመሸጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሯል፡፡

በወንጂ ስኳር ፋብሪካ አካባቢ ለሚኖሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ከ13.48 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ  ወጪ  የተለያዩ ማኅበራዊ ተቋማት ተገንብቶላቸው ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ በተጨማሪም ከ6,491 በላይ የአካባቢው ማኅበረሰብ አባላት የቋሚ፣ ኮንትራትና ጊዚያዊ የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡

ወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ  ቁጥር 496/2014 ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ ከተደረጉት አምስት ስኳር ፋብሪካዎች መካከል አንደኛው ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *