• +251115526653
  • info@etsugar.com
  • Phillips Building, Chad St, Addis Ababa, Ethiopia
ፋብሪካዎች
ፊንጫአ ስኳር ፋብሪካ

ፊንጫአ ስኳር ፋብሪካ

የፊንጫአ ስኳር ፋብሪካ ከአዲስ አበባ በስተሰሜን ምዕራብ 350 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በኦሮሚያ ክልል በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን በአባይ ጮመን ወረዳ በፊንጫአ ሸለቆ ውስጥ ልዩ ስሙ አገምሳ ተብሎ በሚጠራ ቦታ ላይ ይገኛል፡፡

የፊንጫአ ሸለቆ ለስኳር ኢንዱስትሪ ተስማሚ ሆኖ በመገኘቱ ቡከርስ አግሪካልቸራል ኢንተርናሽናል ሊሚትድ በተባለ የእንግሊዝ ኩባንያ ከ1970 ዓ.ም. ጀምሮ የቦታው አዋጭነት፣ የመሬቱ አቀማመጥና የአፈር ይዘት ሁኔታ ላይ ዝርዝር ጥናት ተካሂዶ አዋጭነቱ ተረጋገጦ የተጀመረ ፋብሪካ ነው፡፡

የአፍሪካ ልማት ባንክና የአፍሪካ ልማት ፈንድ፣ የስዊድን፣ የአውስትራሊያና የስፔን መንግሥታት እንዲሁም የሀገር ውስጥ ባንኮች የፋይናንስ ምንጮች መሆናቸው ተረጋግጦ የፕሮጀክቱ ግንባታ ሥራ ጥር ወር 1981 ዓ.ም. ተጀመረ፡፡

ከፊንጫአ ወንዝ በስተምዕራብ እና ምስራቅ የሚገኘውን ቦታ ጨምሮ የፊንጫአ ስኳር ፋብሪካ ጠቅላላ ይዞታ (ኮማንድ ኤሪያ) 67 ሺ 98 ሄክታር ነው፡፡ የፊንጫአ ሸለቆ ውስጥ በማለፍ ለሃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫነት ከዋለ በኋላ ሸለቆውን ከሁለት ከፍሎ ወደ ሰሜን በመጓዝ ከአባይ ወንዝ ጋር በሚቀላቀለው የፊንጫአ ወንዝ በስተምዕራብ ክፍል (ዌስት ባንክ) ያለውን 6 ሺ 476.72 ሄክታር መሬት በሸንኮራ አገዳ በማልማት እና የፋብሪካ ተከላ በማከናወን ነበር ፋብሪካው የካቲት 1990 ዓ.ም. የሙከራ ምርት እንዲጀምርና ከ1991 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ ወደ መደበኛ የማምረት ሥራ ውስጥ እንዲገባ የተደረገው፡፡

የአካባቢው ከፍታ ከባህር ወለል በላይ ከ1 ሺ 350 እስከ 1 ሺ 600 ሜትር ይደርሳል፡፡ በሸለቆው ውስጥ ያለው ከፍተኛው የሙቀት መጠን 31 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሲሆን፣ ዝቅተኛው 15 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ይሆናል፡፡ ዓመታዊ የዝናብ መጠኑም በአማካይ 1 ሺህ 300 ሚሊ  ሊትር ይጠጋል፡፡ ይህም የተፈጥሮ ሁኔታ የፊንጫአ ስኳር ፋብሪካ አካባቢን “ለምለም በረሃ” በሚል ልዩ ስም እንዲታወቅ አድርጎታል፡፡

ፋብሪካው ኢታኖል አምርቶ ከቤንዚል ጋር ተደባልቆ ለተሸከርካሪዎች በነዳጅነት እንዲውል ከሚሰጠው አገልግሎት በተጨማሪ ለሌሎች ኢንዱስትሪዎችም በግብዓትነት በማቅረብ ለሀገራችን ኢኮኖሚ ጉልህ ድርሻ በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡

የፋብሪካው አጠቃላይ የማስፋፊያ ፕሮጀክት

የፊንጫአ ስኳር ፋብሪካ አጠቃላይ የማስፋፊያ ፕሮጀክት የተጀመረው በ1998 ዓ.ም. ነው፡፡ በማስፋፊያ ፕሮጀክቱ በአገዳ ልማት በኩል በዌስት ባንክ 8 ሺ 300 ሄክታር በአገዳ የተሸፈነ መሬት እና የኢስት ባንክና ነሼ አካባቢዎችን በማከል ወደ 21 ሺ ሄክታር መሬት ለማሳደግ የታቀደ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 7 ሺ ሄክታር በኢስት ባንክ እንዲሁም 4 ሺ 670 ሄክታር በነሼ አካባቢ ይገኛል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን የፋብሪካውን አገዳ የመፍጨት አቅም በማሳደግ አመታዊ የስኳር ምርቱን ከ1.1 ሚሊዮን ኩንታል ወደ 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል እንዲሁም የኤታኖል ምርቱን ከ8 ሚሊዮን ሊትር ወደ 20 ሚሊዮን ሊትር ከፍ ለማድረግ ታቅዶ የማስፋፊያ ሥራው ተካሄደ፡፡

የፋብሪካው ማስፋፊያ ፕሮጀክት ስራ ተጠናቆ ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ማምረት ሂደት ውስጥ የገባ ሲሆን፣ በእርሻ ማስፋፊያ ሥራም ከ19 ሺ ሄክታር መሬት በላይ በአገዳ ለመሸፈን ተችሏል፡፡

በዚህ የማስፋፊያ ፕሮጀክት በቀን 6 ሺ 600 ቶን አገዳ በመፍጨት በዓመት 1 ሚሊዮን 600 ሺ ኩንታል ጥራቱን የጠበቀ ነጭ ስኳር የማምረት አቅም ያለው አንድ ተጨማሪ የስኳር ፋብሪካ ተገንብቷል፡፡ ይህ ደግሞ በመሉ አቅሙ ማምረት ሲችል ነባሩ ፋብሪካ ካለው አቅም ጋር ተዳምሮ አጠቃላይ የሚመረተውን አመታዊ የስኳር መጠን 2 ሚሊዮን 700 ሺ ኩንታል እንደሚያደርሰው ይጠበቃል፡፡

ለመኖሪያ መንደሮችና ለፋብሪካው አገልግሎት የሚውል የኃይል አቅርቦትን በተመለከተም ፋብሪካው በመሰረታዊነት የራሱን የኃይል ምንጭ ቀደም ሲልም በመጀመሪያው ምዕራፍ ከተተከለ ሁለት ባለ 3.5 ሜጋ ዋት የእንፋሎት ተርባይን ያሟላ ነበር፡፡ በማስፋፊያ የተገነባው ሁለት ባለ 12 ሜጋ ዋት የእንፋሎት ተርባይን ሲጨመርም በድምሩ 31 ሜጋ ዋት ማመንጨት ችሏል፡፡ ከዚህ ውስጥ ለፋብሪካው እና ለመስኖ ፓምፖች እንዲሁም ለሠራተኛ መኖሪያ መንደሮች እና ለልዩ ልዩ አገልግሎት መስጫ ተቋማት 21 ሜጋ ዋት የሚያስፈልግ ሲሆን፣ ቀሪውን 10 ሜጋ ዋት ደግሞ ወደ ብሔራዊ የኃይል ቋት እየላከ ይገኛል፡፡

ፊንጫኣ ስኳር ፋብሪካ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ  ቁጥር 498/2014 ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ ከተደረጉት አምስት ስኳር ፋብሪካዎች መካከል አንደኛው ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *