
በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይና በአስር ዓመቱ አገራዊ ዕቅድ ላይ ውይይት ተካሄደ
የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ዋና መስሪያ ቤት አመራር አባላትና ሠራተኞች በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይና በአስር ዓመቱ የልማት ዕቅድ ላይ ነሐሴ 26 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትሕ ቢሮ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውይይት አድርገዋል፡፡
ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የግሩፑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ክቡር አቶ ወዮ ሮባ በዕለቱ ለተቋሙ አመራር አባላትና ሠራተኞች ለውይይት የሚቀርቡት ሁለት ሰነዶች መሆናቸውን አመልክተው በሰነዶቹ ዙሪያ ሕዝብን የማወያየትና ግብረመልስ መሰብሰብ ሥራ በመላ አገሪቱ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
በውይይቱ ላይ በአማራ ክልል ያለውን ነባራዊ ሁኔታ የተመለከተ ሰነድ በአቶ ታፈሰ አሰፋ የግብይት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ እና በህግና ኢንሹራንስ መምሪያ ሥራ አስኪያጅ በአቶ ፋሲል ገብረማርያም ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
በሰነዱ የአማራ ክልል ሕዝብ ለሚያነሳቸው የተለያዩ ጥያቄዎች መንግስት ምላሽ ለመስጠት በመስራት ላይ ቢሆንም ጽንፈኛው ኃይል የሕዝቡን ጥያቄ ተገን በማድረግ የፖለቲካ ስልጣን ለመያዝ በማሰብ ነፍጥ በማንሳቱ ይህንን ሁኔታ ለመቀልበስ በክልሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ ተብራርቷል፡፡
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሠረት የተቋቋመው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ በክልሉ በወሰዳቸው የማስተካከያ እርምጃዎች ክልሉ ቀድሞ ወደነበረበት ሠላም በመመለስ ላይ እንደሚገኝም በሰነዱ ተመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ክቡር አቶ ወዮ ሮባ በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ ባደረጉት ንግግር በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚስተዋሉ የጸጥታ ችግሮች እንደአገር ለመቀጠል አዳጋች መሆናቸው ስለማይቀር ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ሠላም እንዲከበር የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል፡፡ በመንግስት በኩልም ምንምጊዜም ችግሮችን በሰላም ለመፍታት ዝግጁነት እንዳለ አስገንዝበዋል፡፡
በአማራ ክልል የሚስተዋለው ችግር ጽንፈኛው ኃይል በትጥቅ ታግዞ በአቋራጭ ስልጣን ለመያዝ የሚደረግ ትግል መሆኑን መገንዘብ ይገባል ያሉት ክቡር ዋና ሥራ አስፈጻሚው አሁን ባለው ዓለም ዓቀፋዊና አገራዊ ነባራዊ ሁኔታ ይህ የማይቻል መሆኑን መገንዘብ ይገባል ብለዋል፡፡
ያልተመለሱ የሕዝብ ጥያቄዎች በሙሉ መመለስ እንደሚገባቸው ያስገነዘቡት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጥያቄዎቹን ለመመለስ ጊዜና ሐብት የሚፈልጉ መሆናቸውን መረዳት አስፈላጊ ነው መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ሠራተኛውም በአገሪቱ ሠላም እንዲሰፍን ግጭቱን ከሚያባብሱ አካላት መራቅ እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያን የአስር ዓመት አገራዊ ዕቅድን በተመለከተ በአቶ ዮሴፍ በጋሻው የዕቅድ ልማትና ስጋት አስተዳደር መምሪያ ሥራ አስኪያጅ በኩል በመንግስት የተዘጋጀ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
በውይይቱ ላይ ከ2013 እስከ 2015 ባሉት ዓመታት የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት የኮሮና ወረርሽኝን፣ ግጭቶችን፣ የአበዳሪ ተቋማትንና በምጣኔ ሀብት የበለጸጉ አገሮች ተጽዕኖን ተቋቁሞ ከሰሐራ በታች ከሚገኙ አገራት የተሻለ ዕድገት ማስመዝገቡ ተገልጷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከፍተኛ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መሳብ መቻሉም ነው የተገለጸው፡፡