• +251115526653
  • info@etsugar.com
  • Phillips Building, Chad St, Addis Ababa, Ethiopia
ዜናዎች
ግሩፑ ራሳቸውን ችለው ከወጡ ስኳር ፋብሪካዎች ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ

ግሩፑ ራሳቸውን ችለው ከወጡ ስኳር ፋብሪካዎች ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ

የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ራሳቸውን ችለው ከወጡ ስኳር ፋብሪካዎች ጋር በምርምር፣ ስልጠና እና ቴክኖሎጂ ሽግግር በጋራ መስራት  የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ሐምሌ 5 ቀን 2016ዓ.ም ተፈራረመ፡፡

ስምምነቱ ራሳቸውን ችለው የወጡት ስኳር ፋብሪካዎች (ወንጂ ሸዋ፣ መተሐራ፣ ፍንጫኣ፣ ጣና በለስ እና ከሰም ስኳር ፋብሪካዎች) በምርምር፣ ስልጠና እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ረገድ ከግሩፑ ጋር የሚኖራቸውን ግንኙነት ህጋዊ መሰረት ያለው፣ ውጤታማና ቀጣይነት ያለው፣  እንዲሁም በመተማመን ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ያግዛል፡፡

ስምምነቱ የስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ እና ራሳቸውን ችለው የወጡት አምስቱ ስኳር ፋብሪካዎች የሠው ሃይልን፣ መሠረተ ልማትን እና ግብአትን በማቀናጀት ውጤታማ የምርምርና ስልጠና አቅም በመፍጠር የፋብሪካዎቹን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እንዲሁም ዘርፉን ትርፋማና ተወዳዳሪ ለማድረግ ቅንጅታዊ አሰራር ለመፍጠር ያስችላል፡፡

የመግባቢያ ስምምነቱን በተመለከተ ውይይት በተደረገበት ወቅት ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ክቡር አቶ ወዮ ሮባ የግሩፑን የምርምርና ስልጠና ዘርፍ በሸንኮራ አገዳ ምርምር ረገድ አገራዊ የልህቀት ማዕከል ለማድረግ በርካታ ተግባራት በመከናወን ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

አምስቱ ስኳር ፋብሪካዎች ራሳቸውን ችለው ከወጡበት ከመጋቢት 2004ዓ.ም ጀምሮ የምርምር ሥራዎች መቆራረጥ በመስተዋሉ ይህንን ችግር ለማስተካከል እና አቅጣጫ ለማስያዝ የመግባቢያ ስምምነቱ ያለው ጠቀሜታ የጎላ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የግሩፑ የምርምርና ስልጠና ዘርፍ በፋብሪካዎቹ ከሚገኙ የምርምር ጣቢዎች ጋር በጋራ ካልሰራ አገራዊ ተልዕኮውን መወጣት ያዳግተዋል ያሉት ክቡር ዋና ስራ አስፈጻሚው ከዚህ አንጻር ስምምነቱ እንደአገር ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ ይረዳል ብለዋል፡፡

የምርምርና ስልጠና ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አባይነህ ባዘዘው በበኩላቸው የመረጃ ልውውጥ ክፍተት፣ የጅምር የምርምር ሥራዎች ቀጣይነት ማጣት እንዲሁም የተጠናቀቁ የምርምር ሥራዎች ተግባራዊ ያለመደረግ ችግሮች በመታየታቸው  በፋብሪካዎች የሚገኙ የምርምር የስራ ክፍሎች ከማዕከሉ ጋር ያላቸው የሥራ ፍሰት ተመጋጋቢ ይሆን ዘንድ የግንኙነት መስመር አስፈላጊ መሆኑን በማንሳት ጥያቄዎች ሲቀርቡ ነበር ብለዋል፡፡

የምርምርና ስልጠና ማዕከሉ የጋራ ተቋም በመሆኑ ስምምነቱ በአደረጃጀት ምክንያት ክፍተት እንዳይፈጠር ያግዛል ብለዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የተገኙት የአምስቱ ስኳር ፋብሪካዎች ዋና ሥራ አስኪያጆችና ተወካዮች ስምምነቱ ሥራቸውን በእጅጉ እንደሚረዳ፣ ለምርታማነታቸው እገዛ እንደሚያደርግ እንዲሁም እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ስምምነቱን በግሩፑ በኩል ክቡር ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ወዮ ሮባ ሲፈርሙ የመተሐራ ስኳር ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አብዱልአዚዝ ዩሱፍ፣ የፊንጫኣ ስኳር ፋብሪካ ሥራ አስኪያጂ አቶ መንግስቱ ኃይለማርያም፣ የጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አበበ ይሁኔ፣ የከሰም ስኳር ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ታፈሰ ሻታ እንዲሁም የወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጂ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢዩኤል ላላንጎ ፋብሪካዎቻቸውን በመወከል ፈርመዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *