
የግሩፑ የምርምርና ስልጠና ዘርፍ አመታዊ የምርምር ሥራዎች ግምገማ ተጠናቀቀ
በሃገር አቀፍ ደረጃ ከመስከረም 28 እስከ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ለ3 ተከተታይ ቀናት ወንጂ በሚገኘው የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ የምርምርና ስልጠና ዘርፍ የስኳር አካዳሚ ሲካሄድ የቆየው አመታዊ የምርምር ሥራዎች ግምገማ (National Research Review) በዛሬው ዕለት ተጠናቋል፡፡
በመድረኩም 7 የተጠናቀቁ የምርምር ውጤቶች እና 11 አዳዲስ የምርምር ፕሮፖዛሎች በአግሮኖሚ፣ በሰብል ጥበቃ፣ በዝርያ ማሻሻያ፣ በአፈር ሣይንስ፣ በመስኖ ምህንድስና እና በስኳር ቴክኖሎጂ የምርምር መስኮች ቀርበው የተገመገሙ ሲሆን በዚህም በዘርፉ ከፍተኛ እውቀትና ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች ከኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዮት፣ ከአዳማ ዮኒቨርሲቲ፣ ከስኳር ፋብሪካዎች እና ከስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ዋና መ/ቤት በተጋባዥነት ተገኝተው በመድረኩ ለቀረቡት የምርምር ሥራዎች አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶችን አበርክተዋል፡፡
የቀረቡት የምርምር ሥራዎችም ምርትና ምርታማነትን በማሻሻልም ይሁን የማምረቻ ወጪን ከመቀነስ አንፃር ለስኳር ኢንዱስትሪው ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክቱ በግምገማው ተመልክቷል፡፡
በመጨረሻም የምርምርና ስልጠና ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ አባይነህ ባዘዘው በመድረኩ የተሣተፉትን አካላት ካመሰገኑ በኋላ በቀጣይም ዘርፉ የበለጠ ተጠናክሮ እንደሚሰራ እና ለኢንዱስትሪው አጋዥ ሆኖ እንዲቀጥል ሁሉም ባለሙያ የበኩሉን አስተዋፅኦ ሊያበረክት እንደሚገባ በማሳሰብ የግምገማ መድረኩ ተጠናቋል፡፡