
እውቅና በተገኘባቸው የስልጠና መስኮች መደበኛ ስልጠና በማስጀመሪያና በስኳር ኢንዱስትሪ ምርምር ፍኖተ ካርታ ዙሪያ የምክክር ወርክሾ ተካሄደ
አካዳሚው በምዘና ማዕከልነት እንዲሰራም ዕውቅና ተሰጥቶታል
የኢትዮጵያ ስኳር አካዳሚ እውቅና ባገኘባቸው የስልጠና መስኮች መደበኛ ስልጠና በማስጀመሪያ እና በስኳር ኢንዱስትሪ ምርምር ፍኖተ ካርታ ዙሪያ የምክክር ወርክሾ ኅዳር 27 ቀን 2017 ዓ.ም በአዳማ ከተማ ተካሄደ፡፡
የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ክቡር አቶ ወዮ ሮባ የመሩትን የምክክር መድረክ በእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸው የከፈቱት በግሩፑ የምርምርና ሥልጠና ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አባይነህ ባዘዘው ናቸው፡፡
የምርምርና ስልጠና ዘርፍ እውቅና ባገኘባቸው የስልጠና መስኮች መደበኛ ስልጠና ለመስጠት የተከናወኑ በርካታ ሥራዎች በምክክር መድረኩ በዝርዝር ቀርበው ሰፊ ውይይትና ምክክር ተደርጎባቸዋል፡፡ በምክክር መድረኩ የግሩፑ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የስኳር ፋብሪካዎች ዋና ሥራ አስኪያጆች፣ የምርምርና ስልጠና ዘርፍ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘም በኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ የምርምርና ስልጠና ዘርፍ የተዘጋጀ የአስር ዓመት የስኳር ምርምር ፍኖተ ካርታ ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
በሌላ በኩል በምክክር ወርክሾፑ የኢትዮጵያ ስኳር አካዳሚ እውቅና ያገኘባቸው የስልጠና መስኮችን በመመዘን ረገድ በማዕከልነት እንዲሰራ ፈቃድ የተሰጠው መሆኑ ተመልክቷል፡፡
የውይይት መድረኩን የመሩት የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ በሰጡት አቅጣጫ በስኳር ልማት ዘርፍ የምርምር ስራ በአለምአቀፍ ደረጃ ለዘርፉ ዕድገት ቁልፍ ሚና እንዳለው አመልክተው ዘርፉ በፍኖተ ካርታው ሊደርስበት ላስቀመጠው የግብ ስኬት ግሩፑ ደረጃ በደረጃ እና አቅም በፈቀደው ሁኔታ ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን አመልክተው የቀረበው ፍኖተ ካርታ ይበልጥ እንዲዳብር ተጨማሪ መድረክና ሰፊ ውይይት እንደሚያስፈልግ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አያይዘውም የስኳር አካዳሚው እውቅና ባገኘባቸው የስልጠና መስኮች መደበኛ ስልጠና ለመጀመር መከናወን የሚገባቸውን ልዩ ልዩ ስራዎች ማጠናቀቅና በግሩፑ ደረጃም ከሰው ኃይል ምልመላና ዕድገት ጋር መመሪያዎችንና መመዘኛዎችን ከዚሁ አንፃር ማስተካከል እንደሚገባ አሳስበው የውይይት መድረኩ ተጠናቋል፡፡
ወንጂ የሚገኘው የኢትዮጵያ ስኳር አካዳሚ በስኳር ልማት ዘርፍ ከኢፌዴሪ የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና መደበኛ ስልጠና እንዲሰጥ ፈቃድ ያገኘው ነሐሴ 10 ቀን 2016 ዓ.ም መሆኑ ይታወሳል፡፡








