• +251115526653
  • info@etsugar.com
  • Phillips Building, Chad St, Addis Ababa, Ethiopia
ዜናዎች
ፋብሪካው ምርታማነቱን ማሳደግ የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም በማከናወን ላይ ይገኛል

ፋብሪካው ምርታማነቱን ማሳደግ የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም በማከናወን ላይ ይገኛል

  • ፕሮጀክቶች ፋብሪካውን ከ55 ሚሊዮን ብር ወጪ አድነውታል

በኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 2 ስኳር ፋብሪካ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ ሁለት ፕሮጀክቶችን በራሱ አቅም በማከናወን ላይ እንደሚገኝ አስታወቀ፡፡

የፋብሪካው ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ፈለቀ ቶማ እንደገለጹት በለውጥ ሥራዎች ዝርዝር ውስጥ የተካተቱና በ2017 የክረምት ጥገና ወቅት ተግባራዊ ሊደረጉ ዕቅድ የተያዘላቸውና የፋብሪካውን ምርታማነት ለማሳደግ የሚረዱ ሁለት ፕሮጀክቶችን በራሳችን አቅም ተግባራዊ በማድረግ ላይ እንገኛለን ብለዋል፡፡

አንደኛው ፕሮጀክት ቀደም ብሎ ከፋብሪካው ጋር መተከል የነበረበት ነገር ግን ሳይተከል የቀረው የወፍጮ ሮተር ስክሪን የተሰኘ ፕላንት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ማግማ ፓምፕ ላይ ይገጥም የነበረውን ችግር ለመቅረፍ እየተከናወነ የሚገኝ ፕሮጀክት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሮተር ስክሪን ፕላንት ለውጭ ኮንትራክተሮች ቢሰጥ 40 ሚሊዮን ብር አካባቢ ወጪ ያስወጣ ነበር ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ ከፋብሪካው ባለሙያዎች ጋር በተደረገ ምክክርና መግባባት ከዲዛይን ጀምሮ እስከ ተከላ ድረስ ያለው ሂደት በራስ አቅም በመሰራት ላይ ይገኛል፡፡

ፕሮጀክቱ በአሁን ሰዓት 80 በመቶ የሚሆነው ሥራው የተጠናቀቀ መሆኑን ዋና ሥራ አስኪያጁ ገልጸው በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት የሲቪል ሥራው ከተጠናቀቀ በኋላ የተከላ ሥራው ተከናውኖ ኮሚሽን ማድረግ ይጀመራል ብለዋል፡፡

ሁለተኛው ፕሮጀክት በ2016ዓ.ም በፋብሪካው ላይ ከፍተኛ የምርትና የጊዜ ብክነት ያስከተለው የኢንጀክሽን መስመርና የቢ ማግማ ፓምፕ ሥራ ሲሆን ይህም በፋብሪካው ባለሙያዎች በመከናወን ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በውጭ ኮንትራክተር ቢሰራ አስከ 15 ሚሊዮን ብር ወጪ ያስወጣ ነበር ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ ፕሮጀክቱ በራስ አቅም ተግባራዊ በመደረጉ በ2018 የምርት ዘመን በከፍተኛ ሁኔታ የጊዜና የምርት ብክነትን ያስቀራል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡