
የግሩፑ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች አረንጓዴ አሻራቸውን አኖሩ
- ግሩፑ ከወረዳ 10 መስተዳድር ጋር በመሆን አስር ሺህ ችግኞችን የመትከል መርሐግብሩን አስጀምሯል
የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ አስር አፍሪካ ህብረት ትምህርት ቤት አጠገብ በሀገር አቀፍ ደረጃ “የምትተክል አገር፤ የሚያጸና ትውልድ” በሚል መሪ ቃል በመካሄድ ላይ የሚገኘውን ዓመታዊውን የአረግጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የግሩፑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የክቡር አቶ ወዮ ሮባ ተወካይና የሰርቪስ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አብርሐም ደምሴ ባደረጉት ንግግር የግሩፑ ሠራተኞች ቀደም ሲል በልዩ ልዩ ስፍራዎች አረንጓዴ አሻራቸውን ያኖሩ እንደነበር አውስተው የዚህ ዓመቱ መርሐ ግብር የተተከሉ ችግኞችን ለመንከባከብ አመቺ እና ለተቋሙ ዋና መስሪያ ቤት ቅርብ በሆነ ስፍራ በመከናወኑ ከወረዳው ጋር በመነጋገር በእንክብካቤውም ረገድ የሚጠበቅበትን ይወጣል ብለዋል፡፡
የተተከሉት ችግኞች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ አብርሐም የግሩፑ ሠራተኞችም በመኖሪያ አካባቢያቸውና በቤታቸው በተመሳሳይ ሁኔታ ችግኞችን በመትከል አካባቢን ከመለወጥ ባለፈ በገቢም ራሳቸውን መደጎም እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡
በግሩፑ ስሩ በሚገኙ የስኳር ፋብሪካዎች የአካባቢ ጥበቃ ሥራ በቋሚነት የሚሰራ ዋና ተግባር ቢሆንም በየዓመቱ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን በማስመልከት በፋብሪካዎቹ ችግኞችን የመትከል ሥራ እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡
የወረዳው የብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ከበደ በበኩላቸው ከወረዳው ጋር በመቀናጀትና ለ2016 ዓ.ም ለአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር በተዘጋጀ ስፍራ በመገኘት የግሩፑ የሥራ መሪዎችና ሠራተኞች በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብሩ በንቃት በመሳተፋቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡